አዲስ አበባ በምርጫ የጥሞና ጊዜ እና የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ድባብ መካከል
ቅዳሜ፣ ግንቦት 22 2018
አርሰናል በፍጹም ቅጣት ምት በፓሪ ሳንጃርሞ ከመሸነፉ በፊት የምርጫ የጥሞና ጊዜ እና የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ የፈጠረው ስሜት በአዲስ አበባ ሲጋጩ የዶቸ ቬለው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ታዝቧል። ነጋሽ ወደ አዲስ አበባ ያቀናው የኢትዮጵያን ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ለመዘገብ ነው።
በዋና ከተማዋ ባደረገው ቅኝት የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ መመልከት የሚፈልጉ ነዋሪዎች በቡድን በቡድን ጨዋታው በሚተላለፍባቸው ቦታዎች ሲሰበሰቡ ታዝቧል። ይሁንና የእግር ኳስ ወዳጆች ከዚህ ቀደም በአደባባይ ባሳዩት ስሜት ምክንያት የጸጥታ አስከባሪዎች ቁጥጥር ሲያደርጉ ተመልክቷል።
የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የተደረገው አዲስ አበባን ጨምሮ ኢትዮጵያ ለሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ በጥሞና ጊዜ ላይ በምትገኝበት ወቅት ነው። የጥሞና ጊዜው የሚከለክለው በዋናነት ከምርጫ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ነው።
ነጋሽ መሐመድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በአዲስ አበባ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከታትሏል። በጋዜጣዊ መግለጫው ሰብሳቢዋ 54,057,861 ድምጽ ሰጪዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመዝገቡን ተናግረዋል። በምርጫው የ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 10,438 ዕጩዎች ቀርበዋል።
ምርጫውን ወደ 55 የሚሆኑ የአገር ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ይታዘባሉ። የአፍሪካ ኅብረት 59 ታዛቢዎች እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 26 ታዛቢዎች እንደሚያሰማሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ መናገራቸውን ነጋሽ ዘግቧል።
ከነጋሽ መሐመድ ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማይቀፉን ይጫኑ