1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአማራ ፋኖ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ ሥራ ስለማወኩ መረጃ እንዳልደረሰው ምርጫ ቦርድ ገለፀ

ሰለሞን ሙጬ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 22 2018

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ከአርብ እስከ ማክሰኞ በአማራ ክልል ከአምቡላንስ በስተቀር የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንደማይኖር አሳስቧል። ከመንግሥት ጋር ዉጊያ ላይ ያለው ይህ ኃይል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቁሳቁስ ስርጭት ሥራ ላይ የፈጠረው እክል ስለመኖሩ የተጠየቁት የቦርዱ ሰብሳቢ "ከምርጫ ቦርድ ሠራተኛ ቆመናል የሚል ሪፖርት የለም" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/5EZcl
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ስለ ምርጫው ሂደት እና ዝግጅት ገለፃ ተደርጓል ብለዋል። ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የአማራ ፋኖ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ ሥራዉን ስለማወኩ የደረሰው መረጃ እንደሌለ ምርጫ ቤርድ ገለፀ

ከትናንት ግንቦት 21 ጀምሮ እስከ መጪው ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በአማራ ክልል ከአምቡላንሶች ውጪ የትኛውም የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳደረግ በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር የትጥቅ ግጭት ውስጥ የገባው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ አሳስቧል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ይህንን ጥሪ አጥጥሎ ውድቅ አድርጎታል። እንዲያም ሆኖ አሽከርካሪዎች በአንዳንድ የአማራ ከተሞች ላይ የእንቅስቃሴ እክል እንደተፈጠረባቸው መግለጣቸው ተጠቅሶ የጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ ላይ ያለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥሪው በቦርዱ ወሳኝ የቁሳቀስ ሥርጭት ሥራዎች ላይ እክል ፈጥሮ እንደሆን ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ላይ የተጠየቁት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ፣ ከሠራተኞቻቸው ችግር ገጥሞናል የሚል የቀረበላቸው "ሪፖርት" እንደሌለ መልሰዋል።

"የምርጫ ቦርድ ሠራተኛ፣ ምርጫ አስፈጻሚን በተመለከተ ቆመናል የሚል ሪፖርት ስለሌለኝ አላውቀውም።"

የምርጫ ቁሳቁስ ሥርጭት ምን ይመስላል?

የቦርዱ ሰብሳቢ እስከ ትናንት አርብ ድረስ በአማራ ክልል በአምስት፣ በጋምቤላ ክልል በአራት የምርጫ ክልሎች ቁሳቁስ አለመድረሱን ግን አሳውቀዋል። ከነዚህ ውጪ ግን በሌሎች ሁሉም የምርጫ ክልሎች በሙሉ ቁሳቁስ መሰራጨቱን አመልክተዋል። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች የትግራይ ሙሉ በሙሉ 38ቱ እና የአማራ 8 የምርጫ ክልሎች ሰኞ ምርጫ የማይደረግባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው።

"ባሉን ምርጫ ክልሎች በሙሉ የቁሳቁስ ሥርጭት ተካሂዷል። በአማራ ወደ አምስት ምርጫ ክልል፣ በጋምቤላ ወደ አራት ምርጫ ክልል ሲቀር ሙሉ በሙሉ ባሉ ምርጫ ክልሎች የቁሳቁስ ሥርጭት ደርሷል።"

የመራጮች ቁጥር ስለመጨመሩ

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዳሉት በዩቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በወታደራዊ ጦር ሠፈሮች ውስጥ በተደረጉ የመራጬች ምዝገባ ሥራዎች ምክንያት አጠቃላይ ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡት መራጬች ቁጥር ወደ 54 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። በእርግጥም ቦርዱ አስቀድሞ እንዳለው የሕግ ጥሰት ተገኝቶባቸው ምዝገባቸው ሙሉ በሙሉ የታገደባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ስላሉና በእነዚያ ስፍራዎች መራጮች በድምፅ መስጫው ዕለት ወይም ሰኞ ድጋሚ እየተመዘገቡ ድምፅ ስለሚሰጡ አሁንም የመራጮች ቁጥር ከዚህ ከፍ ሊል ይችላል።

"በአጠቃላይ የመራጮች ቁጥር ወደ 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 ይደርሳል።"

የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ሪፖርት ማድረጊያ ሥርዓት ስለመዘርጋቱ - 6214 አጭር የስልክ ጥሪ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት "የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ሪፖርት ማድረጊያ ሥርዓት" አዘጋጅቷል። 6214 በተባለ አጭር የስልክ ጥሪ ማዕከል ማንም ሰው የትኛውንም አይነት ትክክል ያልሆነ ክስተት ሲመለከት ደውሎ ማሳወቅ ይችላል ተብሏል።

"የክስተቶች ሪፖርት ሊሆን ይችላል፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባል፣ በፖለቲካ ፓርቲ፣ በዜጎች፣ በመራጮች የትኛውም አይነት ክስተት ሪፖርት የሚደረግበት ነው።"

 ዶቼ ቬለ ይህ 6214 የተባለው የአጭር ቁጥር የጥሪ ማዕከል እንደተባለው በትክክል አገልግሎት ይሰጥ እንደሆን ዛሬ ቅዳሜ ደውለን አረጋግጠናል።

ቦርዱ አዲስ አበባ ተቀማጭ ለሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ስለ ምርጫው ገለፃ አድርጓል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ለምን ያህሉ እንደሆነ ቁጥራቸውን በግልጽ ባይጠቅሱም በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ስለ ምርጫው ሂደት እና ዝግጅት ገለፃ ተደርጓል ብለዋል። ይህም ብቻ አይደለም "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው" ብለው የገለጿቸዉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በድምፅ መስጫው ዕለት ተዘዋውረው ለማየት ጥያቄ በማቅረባቸው "የታዛቢነት ሳይሆን የእንግድነት"  ፈቃድ ወስደዋል።

55 የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ወስደው ምርጫውን እንደሚታዘቡ ተጠቅሷል። ከውጪ ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት - ኢጋድ እና የአፍሪካ ሕብረት ምርጫውን እንደሚታዘቡ ይፋ አድርገዋል። በትናንቱ መግለጫ ላይ የተገኘው የዶቼ ቬለው የአማርኛው አገልግሎት ከፍተኛ ዐርታዒ ነጋሽ መሐመድ ለቦርዱ ሰብሳቢ የአውሮፓ ሕብረት ምርጫውን እንዲታዘብ ለምን እንዳልተጋበዘ ጠይቆ ምላሽ ተሰጥቷል።

"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ የሚሰጠው ለሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ነው። ለዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ የሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።"

ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው 54 ሚሊየን ሰው  ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህሉ ነው?

ኢትዮጵያ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየ10 ዓመቱ ማድረግ እንዳለበት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 103 ላይ ሰፍሯል። በድንጋጌው መሠረት የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከ ስምንት ዓመታት በፊት 2010 ማድረግ ነበረበት። ተ

ደጋግሞ የተራዘመው ይህ ሥራ ግንቦት 2014 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ለአምስተኛ ጊዜ ተራዝሟል። በዚህ ምክንያት ምንም እንኳን በመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆነ በአንዳንድ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ቁጥሮች ቢጠቀሱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በቆጠራ አልታወቅም።

ይህም በመሆኑ ሰኞ ግንቦት 24 በሚደረገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው 54 ሚሊዮን ሕዝብ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህሉ እንደሆነ አይታወቅም።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ