1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኅብረቱ አዛውንቶች የተዘነጉ ወጣቶች ምሬት

ዓርብ፣ የካቲት 13 2018

1.4 ቢሊዮን ግድም ነዋሪዎች ባሏት አፍሪቃ ሲሦው ወጣት ነው ። የአፍሪቃ ወጣቶች የአፍሪቃ ኅብረት የአብዛኞቻችንን ፍላጎት አላሟላም ሲሉ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ኅብረቱ ወጣቶቹ ላይ የተከሰተውን ቀውስ መፍታት ተስኖታል ሲሉ ይተቹታል ባለሞያዎች ። ሙሉ ዘገባውን በማገናኛው መከታተል ይችላል ።

https://p.dw.com/p/5965f
የ39ኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተሳታፊዎች በከፊል
የ39ኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተሳታፊዎች በከፊልምስል፦ Eskinder Firew/DW

የአፍሪቃ ወጣቶች በአፍሪቃ ኅብረት ተዘንግተናል ይላሉ

1.4 ቢሊዮን ግድም ነዋሪዎች ባሏት አፍሪቃ ሲሦው ወጣት ነው ። 400 ሚሊዮን ግድም የአፍሪቃ ነዋሪዎች እድሜያቸው ከ15 እስከ 35 የሆኑ ወጣቶች መሆናቸው ይነገራል ። የአፍሪቃ ኅብረት  የተቋቋመው «የአፍሪቃ አንድነትን እና ተደጋጋፊነትን ለማጠናከር» መሆኑን ይገልጣል፥ ወጣቶቹ ላይ የተከሰተውን ቀውስ መፍታት ግን ተስኖታል ሲሉ ይተቹታል ባለሞያዎች ። 

የአፍሪቃ ወጣቶች የአፍሪቃ ኅብረት የአብዛኞቻችንን ፍላጎት አላሟላም ሲሉ በተደጋጋሚ ይተቻሉ ። ተንታኞች እንደሚሉት የአፍሪካ ኅብረት ወጣቶች የሚጠብቁትን ነገር ባለማሟላቱ ምክንያት የቅቡልነት ቀውስ ውስጥ ገብቷል ። የኅብረቱ አገራት ተግዳሮት ይህም ብቻ አይደለም ። በርካታ የአፍሪቃ አገራት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የጸናባቸው፣ አወዛጋቢ ምርጫዎችን ያስተናገዱ ናቸው ። ወይንም ደግሞ በውጭ ርዳታ ቅነሳ ምክንያት በተከሰቱ የኢኮኖሚ ችግሮች የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ይጋፈጣሉ ። ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ አገራት በአገር ውስጥ ግጭት እና ጦርነት የተጠመዱ ናቸው ። የንጋት ግሎባል ኢኒሺዬቲቭ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል መለሰ፦ ወጣቶች በበዙባት አፍሪቃ የወጣቱ ጥያቄ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ይናገራሉ ።

«በርካታው የአፍሪቃ ኅብረተሰብ ወጣት እንደመሆኑ መጠን በርካታ ከወጣቱ ጋር ተስማሚ የሆኑ ነገሮችን ይጠይቃል ። እንደ ምሳሌ ብናነሳ፦ እውነተና የሆነ ሥራ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ፣ ወጣቱን ማእከል ያደረገ ይህን የሚይዝ የሥራ አይነት ፖሊሲን፤ እንደገና ደግሞ እውነተኛ የሆነ መሪነት ፣ ተጠያቂነት ያለበት፤ አኅጉሩ ላለው ሐብት ተጠያቂነትን ያጸና ነገር፤ ጥራት ያለው ትምህርት በአጠቃላይ ዘመኑን የዋጀ ነገር ወጣቱ ይፈልጋል ።»

እናም በርካታ አፍሪቃውያን ወጣቶች ፍላጎታቸው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሳይሟላ ሲቀር  ሕገወጥ ስደትን ጨምሮ ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ ። ዘንድሮ ከየካቲት 7 ቀን፣ 2018 ዓ.ም እስከ ቅዳሜ የካቲት 8 ለሁለት ቀናት ተካሂዶ በተጠናቀቀው  39ኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የወጣቶቹ ጥያቄ ዳግም ተነስቷል ።  ኅብረቱ ስለ ነፃ ንግድ ቀጠና ወሳኝነት እና መሰረተ ልማት ትስስር አስፈላጊነት አጽንኦት ሲሰጥ የወጣቶች የፈጠራ ክኅሎት ጉዳይም በኮሚሽኑ ኃላፊዎች ዘንድ ተነስቷል ።

በአፍሪቃ ኅብረት ተገኝተው ንግግር ያሰሙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ
በአፍሪቃ ኅብረት ተገኝተው ንግግር ያሰሙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽምስል፦ Xie Jianfei/Xinhua/picture alliance

ከ25 ዓመታት በኋላ የአፍሪቃ ወጣቶች ብዛት አሁን ካለው 400 ሚሊዮን በእጥፍ እንደሚያድግ ተተንብዮዋል ። ወጣቶችን ጨምሮ አብዛኛው ነዋሪ ግን ዛሬም ድረስ በድኅነት አረንቋ ውስጥ ይገኛል ። ኅብረቱ ዓመታዊ ጉባኤውን አዲስ አበባ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ባካሄደበት ወቅት በርካታ የአፍሪቃ ወጣቶች በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ምሬታቸውን ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል ። እንደ አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ ዘገባ ከሆነ፦ ወጣቶቹ ኅብረቱን «የአዛውንቶች ስብስብ» ሲሉ በብርቱ ተችተዋል ። የወጣቶቹንም ፍላጎት ቅድሚያ የመስጠት ፍላጎቱ የለውም ሲሉም ተደምጠዋል ።

ወጣት ትእመር ብርሃኔ፦ «ሞዴል አፍሪቃ ኅብረት ኢትዮጵያ» በተሰኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ውስጥ የሥነ ጥበብ ፣ መገናኛ ብዙኃን እና ተግባቦት ኃላፊ ናት ። መሰል ጥያቄ በተደጋጋሚ እንደሚነሳ ትገልጣለች፥ መፍትኄው ግን ወጣቱ ዘንድ ነው ትላለች ። «እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ ይነሳሉ፥ እኛም እንሰማለን በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውኃሮች ላይም ወጣቶች ሲነጋገሩበትም የምንመለከተው ነገር ይመስለኛል » ያለችው ወጣት ትእምር፦ ወጣቱ የኅብረቱ መሪዎች የሚያወጧቸው ፖሊሲዎችን በንቃት በመከታተል ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ብላለች

ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፦ የአፍሪቃ ኅብረት አብዛኛ መሪዎች በእድሜ የገፉ እና ለረዥም ዘመንም መንበረ ሥልጣን ላይ የጃጁ በመሆናቸው የወጣቶችን ጥያቄዎች የመመለሱ ጉዳይ አጠያያቂ ነው ።   ወጣቱ ወደ ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጣ ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት እንደሚገባውም ወጣት ትእመር ትመክራለች ። «እንደምናውቀው ይኼ የመሪዎች ስብሰባ ነው ብዙ ጊዜ መሪዎች ሲሰበሰቡ ደግሞ የወጣት ድምጽ አልተካተተም ምናምን ምናምን የሚሉ ጥያቄዎች ትክክል ቢሆኑም፤ አንዳንዴ ደግሞ ወደ ራሳችን ተመልክተን ወጣቶች ምን ያህል አገራቸው ላይ ስላለው ፖሊሲ፣ የፖሊሲ አፈጻጸሞች ምን ያህል ያውቃሉ የሚለውንም ጥያቄ አንድ ላይ ማንሳት ያለብን ይመስለኛል ።»

አቶ ዳንኤል በበኩላቸው፦ ከወጣቱ የሚጠበቁ ነገሮች መኖራቸው ላይም አጽንኦት ይሰጣሉ ። «የወጣቱ የሥራ ባሕል እንዲያድግ ከወጣቱም በኩል የሚጠበቁ ነገሮች እንዳሉ አይተናል መንግሥት፣ ፖሊሲ፣ ምቹ አካባቢ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብ አመለካከቱ ላይም ያን ማእከል ያደረገ ወጣት የራሱንም ድርሻ መወጣት እንዳለበት፥ እዛም ላይ ክፍተት እንዳለ አይተናል ።»

ወጣቱ ፍላጎቶቹ በማይሟሉበት ወቅት ገሚሱ አደገኛ ስደትን ጨምሮ ለበርካታ ችግሮች ይዳረጋል ። በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ብዙ ሥራዎችን የሚሠሩት እና በጉዳዩ ላይም ጥናት ያደረጉት አቶ ዳንኤል ወጣቶች ላይ ስለጋረጡ ተግዳሮቶች ቀጣዩን ብለዋል ።  «ከተመቻቸ ሥራ ካለመኖር ጋር፤ ከወጣቱ የተለያዩ ክኅሎቶች ማጣት ጋር ተያይዞ እንቅስቃሴው ለምሳሌ ከአገር አገር የሚደረገው ጉዞ፤ ተንቀሳቅሶ የመስራት ሕገ መንግሥታዊ የሆነ መብትን ከመጠበቅ አንጻር በጣም የተወሰኑ ውስንነቶች አሉ ።»

የአፍሪቃ ኅብረት የተቋቋመው «የአፍሪቃ አንድነትን እና ተደጋጋፊነትን ለማጠናከር» መሆኑን ይገልጣል
የአፍሪቃ ኅብረት የተቋቋመው «የአፍሪቃ አንድነትን እና ተደጋጋፊነትን ለማጠናከር» መሆኑን ይገልጣልምስል፦ Eskinder Firew/DW

የአፍሪቃ ኅብረት «አጀንዳ 2063»ን የተመለከተችው ወጣት ትእመር ኅብረቱ ካሰፈራቸው ሰባት ግቦች መካከል «በወጣቶጥ የምትመራ አፍሪቃን መመሥረት » አንዱ መሆኑን ጠቅሳለች ። ያም በመሆኑ ወጣቱ አፍሪቃ ውስጥ ያለውን ችግር መመልከት እንደሚገባው በመጥቀስ ያን ክፍተት ለማጥበብ ከባልደረቦቿ ጋር ጥረት እንደምታደርግ ገልጣለች ። «በወጣቶች የምትመራ አፍሪቃን ስንመሰርት ወጣቱ አፍሪቃ ላይ ስላሉት ችግሮች በደንብ ግንዛቤ አለው ወይ፣ ችግሮቹንስ ለመፍታት በምን ያህል ደረጃ ዝግጁ ነው፤ ምን ያህልስ እየሠራ ነው፤ ምን ያህል ስለችግሮቹ ያጤናል የሚለውንም ነገር ሁሌም ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት ብዬ አስባለሁ ።»

ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩት አቶ ዳንኤል ለአፍሪቃ መሪዎችም ለወጣቶቹም መልእክት አላቸው ። «የአፍሪቃ መሪዎች ወደ ራሳቸው መመልከት አለባቸው፤ አቅማቸውን ማየት አለባቸው፤ ፖሊሲዎቻቸውን መፈተሽ አለባቸው የአሠራር ስርዓታቸውን ማዘምን እና ከዘመኑ ጋር ከወጣቱ ፍላጎት ጋር የሚሄድ ማድረግ አለባቸው በዛኛው ወገን ደግሞ ወጣቶቹ ራሳቸውን ለደጋ ከሚጥል ነገር ተቆጥበው አገር ውስጥ ያለውን እድል አሟጠው መጠቀም አለባቸው በሰው አገር ሄዶ አንዳንድ ነገር ውስጥ ከመግባት በፊት ምንድን ነው ያለው ብለው፤ ደፈር ብለው ችግሮችን ለመጋፈጥ የቆረጡ መሆን አለባቸው ።»

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti