ለጸጥታ ቅድሚያ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ
ዓርብ፣ የካቲት 6 2018
በአህጉሪቱ መፍትሔ ሳያገኙ የቀጠሉት የጸጥታ ችግሮች የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ቀዳሚ አጀንዳዎች እንደሚኾኑ ዲፕሎማቶችና ተንታኞች ተናግረዋል።
ጉባኤው ለነዚሁ የጸጥታ ችግሮች እልባት ማስገኘት የተሳናቸውን የህብረቱን የሠላምና ጸጥታ እንደዚሁም የአስተዳደር መዋቅሮች ለማሻሻል በሚቀርበው ምክረ ሐሳብ ላይሞ እንደሚነጋገር ተገልጿል ።
በወቅታዊው የኢትዮጵያና የኤርትራ ውጥረት ላይ ይነጋገር እንደኾነ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የካቲት 7 ቀን 2018 ዓ/ም በአዲሰ አበባ የሚጀመረውና ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ዋነኛ መነጋገሪያ ከቀደሙት አመታት የተለየ እንደማይሆን DW ያነጋገራቸው ዲፕሎማቶች አስረድተዋል ።
የ 55ቱም አባል አገራት አምባሳደሮች አባል የሆኑበትን የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ መልዕክተኛች ኮሚቴ (PRC) ከአሁን ጀምሮ ለአንድ አመት የሚመሩት የቡሩንዲ አምባሳደር ዊሊ ናያምቲዌ የአህጉሪቱ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ከጉባኤው ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳዎች አንደኛው እንደሚኾን አረጋግጠዋል።
"በአህጉሪቱ ያለው የጸጥታና ሠላም ጉዳይ ፣ ግጭቶችን ሁሉ በ2030 ለማስቆም ፍኖተ ካርታ ካጸደቅንበት እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ የአፍሪካ ሕብረት ቅድሚያ የሚሰጠው አንደኛ አጀንዳ ኾኖ ቆይቷል"
ብለዋል።
እ.አ.አ በሚየዚያ 2023 የተጀመረው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።12 ሚሊየን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቀለዋል -150,000 የሚኾኑት ደግሞ ሕይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል።የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ጦር ኃይልና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ለሚካሄደውና ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ላስከተለው ጦርነት እስካሁን ሰላማዊ መፍትሔ ማምጣት አልቻለም።
በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል አይ.ኤስ.ኤስ በመባል በሚታወቀው የጸጥታ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የኾኑት ሙሳ ሶማሆህሮ፣ ለዚህ አንዱ ምክንያት የአፍሪካ ሕብረት የሚከተለው መርህ መኾኑን ገልጸዋል።ይህ መርህ በየአካባቢው ያሉ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች በአቅራቢያቸው ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት ቅደሚያውን እንዲወስዱ የሚያደርግ መኾኑንም አስታውሰዋል።
በዚህ መርህ መሰረት፣ለሱዳን ግጭት መፍትሔ ለመፈለግ ቅድሚያው የነበረው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ያንን ማድረግ አለመቻሉን አስታውቀዋል።
ከአህጉሪቱ ወጭ የኾኑ አካላት መፍትሔ የማፈላለጉን ሂደት የተቀላቀሉትም የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤቶች በፈጠሩት ክፍተት መኾኑን ተናግረዋል።
"አሁን ከአህጉሪቱ ውጭ የኾኑ ተሳታፊዎች በአፍሪካውያን ተቋማት ማለትም በኢጋድና በአፍሪካ ሕብረት የተፈጠረውን ክፍተት እየሞሉ ነው'" በማለት አስረድተዋል።
በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ በአገሪቱ ጦርና ኤም 23 በሚባለወ አማጺ ቡድን መካከል የቀጠለው ጦርነትም ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እያስከተለ ቀጥሏል።ሐሙስ የካቲት 5 ቀን 2018 ዓ/ም
በኹለቱ ወገኖች መካከል የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ግን ተስፋ አሳድሯል።በዚህ ስምምነት ወስጥ መሪውን የማደራደር ሚና የተጫወተው ግን የአፍሪካ ሕብረት ሳይሆን ኳታርና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።
መሠረቱን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው የፍትህና የእርቅ ተቋም የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካሪ የኾኑት ቲም ሙሪቲ፣የሰላም ሂደቶችን ከማካሄድ አንጻር፣ሕብረቱ የመሪነት ሚና እየታጫወተ እንዳልኾነ ጠቅሰዋል።
" ይሄ በሚያሳዝን ሁኔታ እውነት ነው።ከአህጉሪቱ ውጭ የኾኑ በርካታ ተሳታፊዎች በአፍሪካ ውስጥጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው።ይህ እየኾነ ያለው በውስጥ ድክመቶቻችንን ምክንያት ጭምር ነው" ብለዋል።
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚካሄደው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ወደ ሌላ ዙር ጦርነት እንዳያመራ በተሰጋበት ወቅትም ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ/ም በጻፉት ደብዳቤ፣ኤርትራን የግዛት ድንበር በመጣስና በአገሪቱ ካሉ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመስራት ወንጅለዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር በበኩሉ፣ውንጀላውን "ፈጽሞ መሠረት የሌለውና የፈጠራ" ሲል አስተባብሏል።
ጉባኤው፣ በዚህ የኹለቱ አገራት ውጥረት ላይ ይነጋገር እንደኾነ የታወቀ ነገር የለም።ከመሪዎቹ ጉባኤ ቀደም ብሎ በተካሄደው 48 ኛው የሕብረቱ መደበኛ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቴዎስም ሰለ ጉዳዩ አላነሱም።
በሌላም በኩል ጉባኤው፣የአፍሪካ ሕብረትን የሠላምና ጸጥታ እንደዚሁም የአስተዳደር መዋቅሮች ለማሻሻል ያስችላል በተባለው ምክረ ሐሳብ ላይም ይነጋገራል።
ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብ የተቋቋመውና ታዋቂ አፍሪካውያንን ያካተተው ቡድን ሂደቱን በሚመሩት የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አማካይነት የሚያቀርበው ሐሳብ የሕብረቱን የማስፈፀም አቅም የሚያጠናክር መኾን እንዳለበት ቲም ሙርቲ ይናገራሉ።
አይ.ኤስ.ኤስ በመባል የሚታወቀው የጸጥታ ጥናት ተቋም እ.አ.አ.በ2023 ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፣የአፍሪካ ሕብረት የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት እ.አ.አ. ከ2004 ጀመሮ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች 90 በመቶው ተግባራዊ አልተደረጉም።
እስክንድር ፍሬው
ታምራት ዲንሳ
ጸሐይ ጫኔ