1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት አምራቾች የገበያውን ፍላጎት መሙላት ለምን ተሳናቸው?

ረቡዕ፣ መጋቢት 21 2014

በኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት ዋጋ እስከ አንድ ሺሕ ብር ሲያሻቅብ መንግሥት ከዓለም ገበያ በመሸመቱ ፍላጎቱን ለመሙላት እየታተረ ነው። ከዓመታት በፊት ከቅባት እህሎች ዘይት ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ተደራራቢ ፈተናዎች ውስጥ እንደሚገኙ የዘርፉ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። የዕርዳታ ዘይት፣ ቫትና የቅባት እህሎች እጥረት ዘርፉን ላለፉት ዓመታት ፈትነዋል

https://p.dw.com/p/49FCa
Öl Speiseöl Flaschen
ምስል፦ Colourbox

የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት አምራቾች የገበያውን ፍላጎት መሙላት ለምን ተሳናቸው?

የፋብሪካ ባለቤት የነበሩት ወይዘሮ መሰረት ታከለ በኢትዮጵያ ገበያ አንድ ሊትር የምግብ ማብሰያ ዘይት እስከ አንድ ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን ሲታዘቡ የሚያመርቱበት "ማሽን ቢኖር ኖሮ" ወደ ዘርፉ መመለስ ይዳዳቸዋል። ወይዘሮ መሰረት የማብሰያ ዘይት የማምረት ሥራን የጀመሩት በ1983 ነበር።  "መካከለኛው ማሽን ነው የነበረን። በቀን እስከ አምስት በርሜል (እስከ አንድ ሺሕ ሊትር) ይሰራል" የሚሉት ወይዘሮ መሰረት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ይገኝ የነበረው ፋብሪካቸው ሥራ ሲጀምር የዛሬን አያድርገው እና አንድ ሊትር ዘይት በስምንት ብር ይሸጥ እንደነበር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የወይዘሮ መሰረት ፋብሪካ ለሚያመርተው የማብሰያ ዘይት የሚያስፈልገውን ሱፍ እና ኑግ ከገበሬዎች እና ከነጋዴዎች ይረከብ ነበር። ወቅቱ የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት ፋብሪካዎች በዋናነት በአገር ውስጥ የሚመረቱ የቅባት እህሎችን ለግብዓትነት ይጠቀሙ የነበረበት ነው። 

በምግብ ዘይት ማምረቻው ዘርፍ በአማካሪነት የሚሰሩት አቶ አብርሀም ዳኜ "ተልባ በከፍተኛ ደረጃ አገር ውስጥ ይመረት ነበር። የጥጥ ፍሬ በከፍተኛ ደረጃ አገር ውስጥ ይመረታል። ኑግ በዚያው መጠን አለ። ጎመን ዘር እና ሌሎችም የቅባት እህሎች በበቂ ሁኔታ አቅርቦት ነበራቸው" ሲሉ ከ30 ገደማ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት አምራቾች የግብዓት ችግር እንዳልነበረባቸው ይናገራሉ። ዘርፉን ላለፉት 30 ዓመታት በቅርበት የሚያውቁት አቶ አብርሀም እንደሚሉት ኢትዮጵያ "በትናንሾችም፣ በመካከለኛ እና ከፍተኛ በሚባሉት ሁሉ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ተጠቅማ" ዘይት ታመርት ነበር።

ከገበሬዎች እና ከነጋዴዎች በሚሰበስበው ሱፍ እና ኑግ የምግብ ማብሰያ ዘይት ያመርት የነበረው የወይዘሮ መሠረት ፋብሪካ ግን ከውጪ ከሚገባው ምርት ትከሻ እየተገፋ በገበያው መቀጠል አልሆነለትም። ወይዘሮ መሰረት ታከለ "የኑግ ዋጋ ጨመረ። የኑግ ዋጋ ሲጨምር ከውጪ የሚገባው ዘይት ደግሞ ቀንሶ ነው የሚገባው። ስለዚህ [ሸማቹ] የእኛን ዘይት ይግዛ ወይስ ያኛውን ይግዛ?" ሲሉ ፋብሪካቸው የገጠመውን ፈተና ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ። "ከውጭ የሚገባው የሱፍ ዘይት ቅናሽ ስለሆነ የእኛ ደግሞ ከጥሬ ዕቃ ጋር ስለማያዋጣ ሁሉም ዘጋው" የሚሉት ወይዘሮ መሰረት በስተመጨረሻ "ሁላችንም ወደ ሌላ የንግድ ዘርፍ ነው የገባንው" በማለት የማብሰያ ዘይት የማምረት ሥራቸውን ያቆሙበትን ኹናቴ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

Spanien Madrid - Verunreinigtes Sonnenblumenöl aus der Ukraine in Spanien entdeckt
በምግብ ዘይት ማምረቻው ዘርፍ በአማካሪነት የሚሰሩት አቶ አብርሀም ዳኜ "ተልባ በከፍተኛ ደረጃ አገር ውስጥ ይመረት ነበር። የጥጥ ፍሬ በከፍተኛ ደረጃ አገር ውስጥ ይመረታል። ኑግ በዚያው መጠን አለ። ጎመን ዘር እና ሌሎችም የቅባት እህሎች በበቂ ሁኔታ አቅርቦት ነበራቸው" ሲሉ ከ30 ገደማ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት አምራቾች የግብዓት ችግር እንዳልነበረባቸው ይናገራሉ።ምስል፦ Gustavo Cuevas/dpa/picture-alliance

የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት አምራቾች መንገዳገድ የጀመሩት ግን ከዚያም ቀደም ብሎ ነው። በ2010 ዓ.ም የተቋቋመው እና ከ60 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት አምራቾች ማህበር አማካሪ የሆኑት አቶ ኻሊድ በሽር እንደሚሉት በአገሪቱ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት የተሰጠ ዕርዳታ ዘርፉን በቀዳሚነት የተገዳደረ ፈተና ነው።

የአዲስ ሞጆ የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ለስምንት አመታት የሰሩት አቶ ኻሊድ "ከፍተኛ ድርቅ የነበረ ጊዜ ከውጪ አገሮች በተለይም ከአሜሪካ ዘይት ይመጣ ነበረ። ያኔ ሲመጣ ተረጂው ክፍል ደግሞ ዘይቱን ብቻውን አይጠቀምም። ለምሳሌ በዕርዳታ ከተሰጠው በርከት ያለ ዘይት ትንሽ የሚጠቀም ከሆነ ሌላውን ወደ ገበያ አወጣው። የርዳታ ዘይት ስለሆነ እና ወጪ ስላላወጡበት ያንን ዘይት ይሸጡና ሌላ ለራሳቸው ፍጆታ የሚፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ይገዛሉ። ያ ዘይት በከፍተኛ ደረጃ ስለሆነ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ዘይት አምራቾቹ ምርታቸውን መሸጥ አልቻሉም" ሲሉ በአገር ውስጥ አምራቾች ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ባለፈው ሐምሌ ደብሊው ኤ የተባለ የምግብ ዘይት ማምረቻ ሲመረቅ የኢንዱስትሪ ምኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት በ2013 የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት ፍላጎት 955 ሺሕ 650 ቶን ወይም በአንድ ወር 79 ሺሕ 637 ቶን ደርሷል። አቶ ኻሊድ ግን የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት ፍላጎት የሚሰላበት መንገድ ላይ ጥያቄ አላቸው።

"የአንድ ሰው የዘይት ፍጆታ ምን ያህል ነው? ተብሎ ጥናት ሲደረግ ጥናቱ መሠረት የሚያደርገው ፋብሪካዎቹ ያመረቱትን እና ከውጪ የመጣውን ዘይት በመደመር ብቻ ነው። ነገር ግን ከውጪ ከፍተኛ የሆነ የኮንትሮባንድ ዘይት ይገባል። ያ ሲደመር ፍጆታው ከፍተኛ ይሆናል" የሚሉት አቶ ኻሊድ ስሌቱ ትክክለኛውን የአገሪቱን ፍጆታ እንደማያሳይ ይሞግታሉ። "አሁን ያለን መረጃ መሠረት የሚያደርገው ከውጪ የመጣው ዘይት ሲደመር በአገር ውስጥ የተመረተው ዘይት በሕዝብ ብዛት ይካፈል እና ይኸን ያህል ፍጆታ ነው ይባላል። ግን ያ ትክክል አይመስለኝም። በቁጥሩ ውስጥ ያልገባ ከውጭ የሚመጣ ከፍተኛ የሆነ የዘይት ምርት በዚህ ስሌት ውስጥ አይገባም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Enjera Äthiopien
በኢትዮጵያ ገበያ ከአንድ አመት በፊት ከ350 እስከ 400 ብር ይሸጥ የነበረው አምስት ሊትር ዘይት ዋጋው ባለፉት ሣምንታት ከ800 እስከ 1000 ብር አሻቅቧል። ይኸ የበርካታ ዜጎችን አቅም የተፈታተነ ነው። ምስል፦ DW/E. Bekele Tekele

የኢንዱስትሪ ምኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ባለፈው ሐምሌ እንደተናገሩት ከቅባት እህሎች ዘይት ጨምቀው የሚያጣሩ 25 መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፍጆታ ያላቸው ድርሻ 6.2 በመቶ ብቻ ነው። የፓልም ድፍድፍ የምግብ ዘይት ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው በማጣራት ለገበያ የሚያቀርቡ አምስት ፋብሪካዎች በአንጻሩ በወር ከ26 ሺሕ ቶን በላይ በማምረት ከአገሪቱ ፍላጎት 40 በመቶ ገደማውን እንደሸፈኑ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር።

የአገር ውስጥ አምራቾችን የተጫነው ቫት ነገር

የግብዓት እጥረት እና የአቅም ጉዳይን በመሳሰሉ የተለያዩ ተግዳሮቶች እየተዘጉ የሚከፈቱትን አነስተኛ ተቋማት ጨምሮ በኢትዮጵያ ገበያ በአሁኑ ወቅት ከ850 እስከ 1000 የሚሆኑ የዘይት አምራቾች እንደሚገኙ አቶ ኻሊድ ይናገራሉ። የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲከፍሉ የሚገደዱት ቫት ከውጪ የሚገባውን ዘይት የማይመለከት ሆኖ መቆየቱ በግብይቱ ተጽዕኖ ካሳደሩ ጉዳዮች ቀዳሚው እንደሆነ አቶ ኻሊድ ይጠቅሳሉ።

"ከቫት ነጻ ሆኖ የሚመጣው ዘይት እያለ የአገር ውስጥ ዘይቶች ደግሞ ቫት ተጨምሮባቸው እየነገዱ ወይም እያመረቱ ነበር። ያ ደግሞ እያንገዳገዳቸው፤ እየጣላቸው [ሔዷል።] ምክንያቱም አስራ አምስት በመቶ ቫት ቀላል አይደለም" የሚሉት የቀድሞው አዲስ ሞጆ የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ "ለረዥም አመታት ´ዘይት አምራቾች ይኸ ቫት ይነሳልን` የሚል ጥያቄ እንደነበራቸው አስታውሰዋል። "ከውጪ የሚመጣውን ከቫት ነጻ አድርጎ ሀገር ውስጥ የሚመረተው ከነቫቱ ሲሸጥ ይኸ አድልዖ ነው፤ እንዲያውም መሆን የነበረበት የተገላቢጦሽ ነበር። ሀገር ውስጥ የሚመረተው ዘይት ነው ድጎማ ሊደረግለት የሚገባው የሚል ጥያቄ ነበራቸው። ይኸን ሁሉ አመት መንግሥት ይኸንን አልሰማም" የሚሉት አቶ ኻሊድ "አሁን በዚች ጥቂት ወራት ውስጥ ቫት አንስቺያለሁ አለ። እሱም ጊዜያዊ ነው" በማለት ተናግረዋል።

የቅባት እህሎች እና የወጪ ንግድ ተጽዕኖ

የማብሰያ ዘይት አምራቾች ለግብዓትነት የሚጠቀሙባቸውን የቅባት እህሎች በፈለጉት መጠን ማግኘት አለመቻላቸው ሌላው ዘርፉን እጅ ተወርች የቀፈደደ ፈተና ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው የአገሪቱ ያለፈው ዓመት የቅባት እህሎች የምርት መጠን ከቀደመው ቅናሽ አሳይቷል። ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2018/2019 የበጀት አመት በ747 ሔክታር መሬት ላይ 7 ሺሕ 850 ኩንታል የቅባት እህሎች አምርታለች። በ2019/2020 በአንጻሩ ለቅባት እህሎች የታረሰው መሬት ወደ 820 ሔክታር ከፍ ሲል የምርት መጠኑ ወደ 8 ሺሕ 421 ኩንታል አድጎ ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በ766 ሔክታር መሬት ላይ ያመረተቻቸው የቅባት እህሎች 7 ሺህ 774 ኩንታል ብቻ ነው። ከቡና ቀጥሎ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ከምታቀርባቸው ሸቀጦች ከፍተኛውን መጠን የሚይዘውም ይኸው የቅባት እህሎች ምርት ነው። ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ 9.3 በመቶውን ድርሻ ሲወስድ ኢትዮጵያም 335 ሚሊዮን ዶላር ገደማ አግኝታለች።

የቅባት እህሎች አንዳች እሴት ሳይጨመርባቸው ወደ ውጪ መላካቸው ግን ለኢትዮጵያ ዘይት አምራቾች በጎ ዜና አይደለም። ባቋቋሙት ሜሞስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በኩል ለኢትዮጵያ የዘይት አምራቾች የማማከር አገልግሎት የሚሰጡት አቶ አብርሀም ዳኜ አገሪቱ የቅባት እህሎችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ትኩረት መስጠቷ ብቻ ሳይሆን የምርታማነት ጉዳይም ፈተና እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Geröstete Sesamsamen
ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው የቅባት እህሎች መካከል ሰሊጥ፣ ኑግ እና አኩሪ አተር ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ።ምስል፦ JIRI HERA/Zoonar/picture alliance

"ኑግ እና ሰሊጥ ሙሉ በሙሉ ኤክስፖርት ነው የሚደረገው። የጥጥ ፍሬ እንዲያውም ሙሉ በሙሉ ከምርቱ ውስጥ እንዲወጣ ነው የተደረገው። ከፍተኛውን መጠን ይሸፍን የነበረው እሱ ነው። እነዚህ የቅባት እህሎች በመውጣታቸው ምክንያት ከፍተኛ የሆነ እጥረት አገሪቷ ውስጥ አጋጥሟል" ሲሉ አቶ አብርሀም ተናግረዋል። በገበሬው ማሳ የቅባት እህሎች የምርት መጠን አነስተኛ መሆን ሌላው በዚሁ ላይ የሚታከል ፈተና ነው። አቶ አብርሀም ለዚህ የጥጥ ፍሬን ጉዳይ በማሳያነት ያነሳሉ። "የምርት መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ የጥጥ ፍሬ ዝርያዎች በአገር ውስጥ የሉም። አሁን እየተመረቱ ያሉት አሮጌ እና ድሮ የገቡ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል። የማብሰያ ዘይት "ፋብሪካዎቹ ውጤታቸው አነስተኛ የሆኑ ምርቶች ገዝተው ዘይት በሚጨምቁበት ጊዜ የትርፍ ኅዳጋቸው በጣም ጠባብ ነው። ከ5 እስከ 10 በመቶ የማይበልጥ የትርፍ ኅዳግ ነው ያለው" ያሉት የዘርፉ አማካሪ አምራቾች የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ከውጪ ወደሚገባው ድፍድፍ የማብሰያ ዘይት እንዳዘነበሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው የቅባት እህሎች መካከል ሰሊጥ፣ ኑግ እና አኩሪ አተር ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ። አቶ ኻሊድ "ኑግ እና አኩሪ አተር ወደ ውጪ ከመላክ ይልቅ እዚሁ ለፋብሪካዎቻችን ብንጠቀም በጣም የተሻለ ነበር" የሚል ዕምነት አላቸው። አቶ ኻሊድ እንደሚሉት በቀጥታ ከሚገኘው የማብሰያ ዘይት ባሻገር ለዶሮ እና የእንስሳት አርቢዎች የሚሆን መኖ ማቅረብ ይቻል ነበር። "ኑግ ወደ 40 በመቶ የሚሆነው ነው ዘይት የሚወጣው። አኩሪ አተር ዘይት የሚወጣው 15 በመቶ አካባቢ ነው። ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል። 80 በመቶ መኖ ነው። ውጪ እየሔደ ያለው ይኸ መኖ ጭምር ነው። እንቁላል ዛሬ እስከ ሰባት እና ስምንት ብር የተወደደበት አንዱ ምክንያት የመኖ ችግር ነው።" የሚሉት አቶ ኻሊድ "ወደ ውጪ የሚሔደው [የቅባት እህል] ዘይቱን ብቻ አይደለም እየጎዳ ያለው። በከፍተኛ ደረጃ የእንስሳት መኖ [አቅርቦትን] እየጎዳ ነው" ሲሉ ተደራራቢውን ችግር ያስረዳሉ።

የማብሰያ ዘይት ዋጋ በኢትዮጵያ ገበያ እስከ አንድ ሺር ብር ሲያሻቅብ የአገር ውስጥ አምራቾች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ አፋጣኝ ድጋፍ ለመስጠት መንግሥት ቃል ገብቷል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው መጋቢት 7 ቀን 2014 በሰጡት መግለጫ ድፍድፍ የማብሰያ ዘይት ከዓለም ገበያ ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው የምግብ ዘይት የሚያመርቱ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ እና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። አቶ አሕመድ እንዳሉት ሁለተኛው ውሳኔ የኢትዮጵያን የማብሰያ ዘይት "ፍላጎት በማሳካት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ" ተብለው ተስፋ የተጣለባቸውን ሶስት ድፍድፍ የማብሰያ ዘይት የሚያስገቡ ፋብሪካዎች የተመለከተ ነው።

Äthiopien Bahir Dar | Speiseöl
ባለፈው ሐምሌ ደብሊው ኤ የተባለ የምግብ ዘይት ማምረቻ ሲመረቅ የኢንዱስትሪ ምኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት በ2013 የኢትዮጵያ የማብሰያ ዘይት ፍላጎት 955 ሺሕ 650 ቶን ወይም በአንድ ወር 79 ሺሕ 637 ቶን ደርሷል።ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ምን ሊደረግ ይገባል?

የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት አምራቾች ማኅበር አማካሪ እንዲህ አይነት የመንግሥት ውሳኔዎች ጥንቃቄ እንደሚያሻቸው ይናገራሉ። "ቀደም ሲል የፓልም ዘይት ትልልቅ አስመጪዎች ነበሩ የሚያስመጡት። ከእነሱ ተወሰደ እና መንግሥት በራሱ አውታር በጅንአድ በኩል የፓልም ዘይት ያስመጣ ነበር። ችግር ሲፈጠርበት አሁንም እንደገና ጥሩ ስም ላላቸው እና አምራች ለሆኑ ዘይት ፋብሪካዎች ከውጪ አስመጥተው የማከፋፈሉን ሥራ ተሰጠ ተባለ። ነገር ግን ሲሰጥ እንዴት ነው የተሰጠበት መንገድ የቁጥጥር ሥርዓቱ እንዴት ነው የሚለው አጠያያቂ ነው። በትክክል ሁሉም የተሳተፉበት ነወይ የሚል ነገር አለ" ሲሉ ተናግረዋል። አሁን ባለው ሥርዓት ውስጥ በአብዛኛው የቁጥጥር ሥርዓቱ ክፍተት ያለው ነው። ሥርዓቱ ለሙስና የተጋለጠ ነው። ሙስናው ማን ሰራው ማን አደረገው የሚል አይደለም። ያ በራሱ የምርመራ ጥናት ይፈልጋል። ነገር ግን በዘይት ላይ ለረዥም ጊዜ ያሉት የአሰራር ሥርዓቶች ክፍተት እንዲኖራቸው እየተደረጉ ነው ያሉት። እነዚያ ክፍተቶች የማይሆን ሥራ እንዲሰራ መንገድ የሚከፍቱ ናቸው" ብለዋል።  

የቅባት እህሎች የሚያመርተውን የእርሻ ሥራ ማዘመን፣ ቴክኖሎጂ እና የጥሬ ዕቃ ግብዓቱን ማሳደግ ካልተቻለ እንደ ሕዝብ ቁጥሩ የሚያሻቅበን የኢትዮጵያ የምግብ ማብሰያ ዘይት ፍላጎት ማሟላት እንደማይቻል አቶ አብርሀም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የዘይት ምርት ሒደት እና የእሴት ሰንሰለቱን በቅርበት የሚያዉቁት አቶ አብርሀም ፋብሪካዎቹ ፊታቸውን ወደ እርሻ ማሳ ማዞር እንደሚገባቸው ይመክራሉ። አቶ አብርሀም "ፋብሪካዎቹ ትርፍን በማየት ከጥሬ ዕቃ ጀምሮ ያለውን ምርት ማምረት ሳይሆን መሀል ላይ ድፍድፍ ዘይት አምጥቶ ማሰራቱ ላይ ነው ትኩረት እየተሰጠ ያለው። ስለዚህ ፖሊሲው መስተካከል ያለበት እነዚህን ፋብሪካዎች አግሮ ኢንዱስትሪ ማድረግ ነው" ብለዋል።

"እሳት የማጥፋቱ ሥራ ለዛሬ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። ነገ መፍትሔ ሊሆን አይችልም" የሚሉት አቶ ኻሊድ በበኩላቸው "ምንድነው መደረግ ያለበት ተብሎ አሳታፊ በሆነ መንገድ በተለይ የዘይት አምራች ማኅበራትን የሚያሳትፍ ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ