1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጊዜያዊነት ታገደ

ሐሙስ፣ የካቲት 19 2018

የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ መስጠቱን የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ። የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው አቶ ጌታቸው የሚመሩት ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ላይ ባቀረበው ክስ መሠረት ነው።

https://p.dw.com/p/59RJ5
የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት
የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ ያገደው አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ባቀረበው ክስ መሠረት ነው።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ መስጠቱን የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ። የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው አቶ ጌታቸው የሚመሩት ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ላይ ባቀረበው ክስ መሠረት ነው።

ጉዳዩን ዛሬ የካቲት 19 ቀን 2018 የተመለከተው ፍርድ ቤት ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ “በቃለ መሀላ የተደገፈ የእግድ አቤቱታ” ማቅረቡን አቶ ጌታቸው በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጻቸው ያጋሩት ደብዳቤ አሳይቷል። 

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሦስት ዳኞች በአቶ ጌታቸው የተወከለው ፓርቲ ያቀረበውን አቤቱታ እና ክስ በመመርመር “የከሳሽ ክስ እና ማስረጃ ግልባጭ” ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደርሶ መልሱን ለየካቲት 25 ቀን 2018 እንዲያቀርብ መታዘዙን ደብዳቤው ያሳያል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አከራካሪ የሆኑት ምርጫ ክልሎችን በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ የሚፈጸም ከሆነ ክርክሩ ውጤት የሚያጣ ስለሆነ ይህ የተከሳሽ ወይም የተጠሪ ውሳኔ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ” ዳኞቹ አዘዋል። 

በዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ “አቤቱታ የቀረበበት” ጉዳይ ታግዶ የሚቆየው በፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚደረገው “ይህ ክርክር ታይቶ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ” ነው። 

የስምረት ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ
የስምረት ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በጻፉት ደብዳቤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የምርጫ ክልሎችን የማዋቀርም ሆነ ክልሎችን ከነባር አስተዳደራዊ መዋቅራቸው ውጭ በፌድራል መንግሥት ሥር እንዲሆኑ የመወሰን ምንም ዐይነት ሕገ-መንግሥታዊ ውክልና” እንደሌለው ገልጸዋል።ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁመራ፣ አዲረመፅ፣ ኮረም፣ ጠለምት እና ራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች “ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ” የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን ያሳወቀው የካቲት 16 ቀን 2018 ነበር። 

“በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሣኔ መሠረት የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተጠቀሰው አግባብ ለመፈጸም የሚያስችለውን ሕግ እና ሥርዓት በመጠበቅ ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዕለቱ አስታውቋል።
ውሳኔውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በትግራይ ክልል  የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ልዩ ልዩ ማኅበራት በጽኑ ተቃውመው ነበር። 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በበኩላቸው ውሳኔውን እንደሚደግፉ ገልጸዋል። 

አርታዒ አዜብ ታደሰ 
 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele