1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ወንጀልአፍሪቃ

የግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. የዓለም ዜና

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ዓርብ፣ ግንቦት 21 2018

ከአማራ ክልል መንገደኞችን ጭኖ ትናንት ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረ አውቶብስ ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካቶች መገደላቸው ተሰማ። ማዕከላዊ ኬንያ ውስጥ በሚገኘው የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የተነሳውን እሳት በመለኮስ የተጠረጠሩ ስምንት ተማሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ። የኬንያ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ በኤቦላ ተሐዋሲ ለተያዙ የአሜሪካ ዜጎች አግልሎ ማቆያ የማዘጋጀት እቅድን በጊዜያዊነት አገደ። ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለገባችበት ውዝግብ ለታሰበው የሰላም ስምምነት ከቃል ይልቅ ተግባር እንደምትፈልግ አስታወቀች።

https://p.dw.com/p/5EYm0

አዲስ አበባ፤ መንገደኞች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት

ከአማራ ክልል መንገደኞችን ጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረ አውቶብስ ላይ በታጣቂዎች ጥቃት በርካቶች መገደላቸው ተሰማ። ጥቃቱ ትናንት የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ሲሆን በታጣቂዎቹ ታስረው የተወሰዱ መንገደኞችም አሉ። የዓይን እማኝ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ድርጊቱ የተፈጸመው ትናንት ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ገደማ ነው። ጥቃቱ በጎሀጽዮን እና ቱሉ ሚልኪ መካከል በሚገኝ አደገኛ ስፍራ መፈጸሙም ተገልጿል። እማኞች እንደተናገሩት በተጠቀሰው ስፍራ በቅርብ ርቀት ላይ ያደፈጡት ታጣቂዎች አውቶቡሱ ላይ ባደረሱት ጥቃት መንገደኞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ስማቸው እንዳይገለጽ ያሳሰቡት የመረጃ ምንጭ፤ 60 ተሳፋሪዎች ከነበሩበት አውቶብስ በጥቃቱ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ40 በላይ የሚሆኑ ተሳፋሪዎች ደግሞ በታጣቂዎቹ መታገታቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። በተጠቀሰው ስፍራ መንገደኞች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት መድረሱ ነው የተገለጸው። ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

 

ናይሮቢ፤ ሴቶች በሚማሩበት ት/ቤት እሳት በመለኮስ የተጠረጠሩ መያዛቸው 

ማዕከላዊ ኬንያ ውስጥ በሚገኘው የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የተነሳውን እሳት በመለኮስ የተጠረጠሩ ስምንት ተማሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ። 800 ሴት ተማሪዎችን ያስተናግድ እንደነበር በተገለጸው አዳሪ ትምህርት ቤት ትናንት በተነሳው የእሳት አደጋ የ16 ተማሪዎች ሕይወት አልፏል። በአደጋው ሌሎች 79 ተማሪዎች መጎዳታቸውን የኬንያ የትምህርት ሚኒስትር ጁሊየር ኦጋምባ ተናግረዋል። መንስኤውን ለማጣራት ምርመራ ያካሄደው የኬንያ ፖሊስ ዛሬ ይፋ ባደረገው የመጀ,መሪያ ደረጃ መረጃ፤ ስምንት ተማሪዎች እሳቱን ከመለኮስ እቅድና ያንን ከማስፈጸም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አመላክቷል። መርማሪዎቹ እንደገለጹትም በእሳት አደጋው የተጎዳው የተማሪዎች ማደሪያ 135 ተደራራቢ አልጋዎች ያሉበት ነው። የትምህርት ቤቱ ቦርድ ከሥራ የታገደ ሲሆን ሕጋዊ እርምጃዎች እይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል። ኬንያ ውስጥ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲህ ያሉ የእሳት አደጋዎች እንደሚደጋገሙም አመልክቷል።

 

ኮንጎ፤ የኢቦላ ታማሚዎች መሰወር ያስከተለው ስጋት

ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በኤቦላ ተሐዋሲ ተይዘው በማቆያ ስፍራ የነበሩ ታማሚዎች የእሳት አደጋን ተከትሎ ከአካባቢው መሰወራቸው ስጋት አስከትሏል። ታማሚዎች የነበሩበት ማቆያ በተሐዋሲው የሞተ ሕጻንን አስከሬን በመውሰድ ሂደት በተፈጠረ ግርግር ነበር ከቀናት በፊት በእሳት የጋየው። የሟች ቤተሰቦች ባስነሱት ረብሻም የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶችም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በወቅቱ እዚያ የነበሩ በተሐዋሲው መያዛቸው የተረጋገጠ 18 የኢቦላ ታማሚዎች ከእሳት አደጋው ሸሽተው ወደየመንደራቸው በመሄዳቸው ተሐዋሲውን ያዛምታሉ በሚል ተሰግቷል። ታማሚዎቹንም ወደማቆያው ስፍራ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው። ምንም እንኳን ኤቦላ እስካሁን ህክምና የሌለው አደገኛ ተላላፊ በሽታ ቢሆንም ወረርሽኙ በተቀሰቀሰበት አካባቢ ኅብረተሰቡ በአግባቡ እንዳልተረዳው ነው የህክምና ባለሙያዎች ያመለከቱት። ተሐዋሲውን ከታማሚው ሰው ይልቅ ሕዝቡን በተሽከርካሪ ሆነው ከተማ ውስጥ እየተዘዋወሩ የሚመክሩ የህክምና ባለሙያዎች እያዛመቱ ነው ብለው እንደሚያስቡ ነው የተገለጸው። አንዳንዶችም በሽታው አለ ብለው እንደማያምኑ በኤቦላ የሞቱ ወገኖች በጥንቃቄ እንዲቀበሩ የሚያደርገውን ቡድን የሚቆጣጠሩት ጆን ቱምጁምቤ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

«በመጀመሪያ ሰዎች አስከሬን ሰዎችን ገደለ እያሉ በማሾፍ ነበር የሚያወሩት። ከዚያም ብዙ ሰዎች ይሞቱ ጀመሩ። ምንም እንኳን ሰዎች ቢሞቱም፤ እነሱ ግን በሽታው መኖሩን አላመኑም። ያ ነው ቀዳሚው ተግዳሮት።»

የዓለም የጤና ድርጅት ባለሙያዎች ዛሬ በሰጡት መግለጫ በተሐዋሲው ከ900 በላይ ሰዎች ሳይያዙ እንዳልቀሩ ተናግረዋል። የድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ የጤና መርኀግብር የበላይ አናይስ ሌጀንድ፤

«አጠቃላይ 906 በተሐዋሲው መያዛቸው የተጠረጠረ ሰዎች አሉ፤ 223 ሰዎችም ሞተዋል። መንስኤው በመጣራት ላይ ነው። ምርመራዎች እየተደረጉ ነው፤ እናም የመመርመር አቅም ሲጠናከር ደግሞ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል።»

 

ናይሮቢ፤ የኬንያ ፍርድ ቤት የኤቦላ ታማሚዎች ማቆያ እቅድን አገደ 

የኬንያ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ በኤቦላ ተሐዋሲ ለተያዙ የአሜሪካ ዜጎች አግልሎ ማቆያ የማዘጋጀት እቅድን በጊዜያዊነት አገደ። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተሰማው መገናኛ ብዙኃን አሜሪካ ለኤቦላ ተሐዋሲ የተጋለጡ ዜጎቿ ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ በመከልከል፤ እስኪያገግሙ ኬንያ በሚዘጋጅ ማቆያ እንዲገቡ የማድረቅ እቅድ አላት ማለታቸውን ተከትሎ ነው። ምንም እንኳን የኬንያ መንግሥት የተባለውን በይፋ ባያረጋግጥም፤ የተሰራጨው መረጃ ግን ኬንያ ውስጥ ስጋት መፍጠሩን የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ ዘግቧል። ፊርማ አሰባስቦ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ያቀረበው ካቲባ ኢንስቲትዩት ሲሆን፤ ፍርድ ቤት በውሳኔው፤ ባለሥልጣናት በአሜሪካም ሆነ በሌላ የውጭ ሀገር ስር የሚተዳደር የኢቦላ ታማሚዎች ማቆያ ስፍራ እንዳይገነቡ ወይም ፈቃድ እንዳይሰጡ አግዷል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔው ጊዜያዊ መሆኑን አመልክቶ ለቀረበው አቤቱታ የኬንያ መንግሥት የፊታችን ማክሰኞ ግንቦት 25 ምላሽ እንዲሰጥ አሳስቧል።

 

ኻርቱም፤ የሱዳን የህክምና ቡድን ፈጥኖ ደራሹን ኃይል መክሰሱ 

በሱዳን ፈጥኖ ደራሹ ኃይል የተቃራኒው ወታደራዊ ኃይል በሌለበት በፈጸመው ጥቃት 27 ሰዎች መገደላቸውን አንድ ግብረ-ሠናይ ድርጅት አመለከተ። ከሟቾቹ መካከል አዛውንቶች ይገኛሉ ተብሏል። መረጃውን ይፋ ያደረገው የሱዳን የህክምና ቡድን የተሰኘው ግብረ-ሠናይ ድርጅት ታጣቂው ኃይል፤ ትናንት ሲቪሎች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት ግድያውን ፈጽሟል ሲልም ከስሷል። ጥቃቱም በጦርነት ውስጥ ለመኖር የሚታገሉ የሱዳን ዜጎች የሚገኙበትን ሰብአዊ ቀውስ እንዳባባሰውም አስታውቋል። የሐሙስ ዕለቱ ጥቃት የተፈጸመው በኢድ አል አድሀ ሁለተኛ ቀን ሲሆን ማኅበረሰው በዓሉን እያከበረ እንደነበረ ተገልጿል። የሱዳን የህክምና ቡድን በመግለጫው፤ የሲቪሎችን መንደር እና መኖሪያ ኢላማ ያደረገውን አሰቃቂ ያለውን ጥቃት የዓለም አቀፍ ግብረ-ሠናይ ሕጎችን የጣሰ ነው ሲልም ኮንኗል።

 

ቴህራን፤ ኢራን ለሰላም ስምምነቱ ከቃላት ይልቅ ተግባር ያስፈልጋል ማለቷ

ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለገባችበት ውዝግብ ለታሰበው የሰላም ስምምነት ከቃል ይልቅ ተግባር እንደምትፈልግ አስታወቀች። ቴህራን ጦርነቱን ለማቆምና የሆርሙዝ ሰርጥን ለማስከፈት ከዋሽንግተን ጋር የጀመረችው ንግግር ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ መሆኑን የጠቆሙት የአሜሪካ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አራት የመረጃ ምንጮቹን የጠቀሰው የዜና አውታሩ፤ ካለፈው ሚያዝያ አንስቶ የተጀመረው የተኩስ ማቆም ስምምነት ለ60 ቀናት ኢራን በዘጋችው ስልታዊ ሰርጥ ነዳጅም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንዲተላለፉበት የሚያደርግ ነው። ከኢራን በኩል አወዛጋቢው የኒኩሊየር መርኀግብሯን የሚመለከቱ ጉዳዮች አሉበት። እንዲያም ሆኖ ሮይተርስ እንደዘገበው እስካሁን ውሉ በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አልጸደቀም። የኢራኑ ከፍተኛ ተደራዳሪ መሀመድ ባቃር ታዲያ እኛ ቃላት ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃዎችን ነው የምናምነው፤ ከዚያኛው ወገን ምንም አስተማማኝ ነገር በሌለበት አንዳች አናደርግም ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው ጽፈዋል። ባቃር፤ አክለውም፤ «የአንድ ስምምነት አሸናፊ የሚሆነው አካል፤ ለቀጣዩ ቀን ጦርነት የተዘጋጀ ነው» ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።