1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ወንጀልኢትዮጵያ

“ልጄን ገደል ጥለዋት ‘ሞተች’ ብለው ቅጠል አስቀምጠውባት ጠፉ” በጠለፋ የተጎዳች አዳጊ አባት

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 15 2018

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪ አባት በጠለፋ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት የ17 ዓመት ልጃቸውን በሆስፒታል እያስታመሙ ነው። የ7ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ወጣት የጀርባ አጥንቷ እንደተሰበረና የራስ ቅሏ ሦስት ቦታ እንደተፈነከተ አባቷ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎች ላይ ለፖሊስ ክስ ቢመሠርቱም በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/5B2Pe
አለርት ሆስፒታል
በጠለፋ ወቅት በደረሰባት አደጋ የጀርባ አጥንቷ የተሰበረው እና የራስ ቅሏ ሦስት ቦታ የተፈነከተው ታዳጊ በአዲስ አበባ በሚገኘው አለርት ሆስፒታል በሕክምና ላይ እንደምትገኝ አባቷ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ Eshete Bekele/DW

“ልጄን ገደል ውስጥ ጥለዋት ሞተች ብለው ቅጠል አስቀምጠውባት ጠፉ” የተጠለፈች አዳጊ አባት

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ የውዬ ጉሴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌቱ ካሳዬ እንደ አይን ብሌናቸው የሚያዩዋት የ17 ዓመት እድሜ ታዳጊ ልጃቸው ሴና ወደ ትምህርት ቤት እንደሄደች ሳትመለስ ስትቀር ልጃቸውን ብቻ ሳይሆን ተስፋቸውም ጭምር ነው እንደ ጉም የተነነባቸው፡፡

የ7ኛ ክፍል ተማሪዋ ሴና ጌቱ ትምህርት ከጀመረችበት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስካሁን ከሁሉም ጓደኞቿ የላቀ ውጤት በማምጣት ሁሌም አንደኛ ነበር የምትወጣ ይላሉ አባት በቁጭት በሰጡን ቃለምልልስ፡፡

አደጋው ሲከሰት…

ነገር ግን ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም. የዚህን ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስቴር ፈተናዋን ለመፈተን አከባቢያቸው ወደሚገኘው ትምህርት ቤቷ ወደ ጎሴ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያቀናችው ተስፈኛ ወጣት አካሏም ተስፋዋም ተሰብሮ ወደ ቤት ሳትመለስ ትቀራለች፡፡ “ልጄን ገደል ውስጥ ጥለዋት ሞተች ብለው ቅጠል አስቀምጠውባት ጠፉ” አባት በምሬት የተናገሩት ነው፡፡

“ለአራት ሰዓታት ያህል በዚያ እንደቆየች ነው በነፍስ አግኝተናት ወዲያው ወደ ህክምና የወሰድናት፡፡ በኩዩ ወረዳ ያለው ህክምና የጀርባ አጥንት መሰበር እና ሶስት ቦታ የራስ ቅል መፈንከት የደረሰባት ልጄን ለማከም ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ወደ ፊቼ ሆስፒታል፣ ከዚያን ፊቼ ደግሞ አዲስ አበባ ወደሚገኘው አቤት ሆስፒታል ጻፉልን፡፡ እዚህም አዲስ አበባ መጥተን ወደ አለርት ሆስፒታል አሳልፈውን በጀርባዋ ስድስት ሽቦ አስገብተውባት እስካሁን እየታገልን ነው ነፍሷ አልወጣችም” ብለዋል፡፡

አባት በልጃቸው ተስፋቸውን በአጭሩ የቀጨውን ግለሰብ ያውቃሉ፡፡ ግለሰቡ ከዚህ በፊት በአከባቢ ባህል ልጃቸውን ለትዳር ጠየቃቸው፡፡ አቶ ጌቱ ግን ገና ታዳጊና ተስፈኛ የሆነች ልጃቸው በእጭሩ እንድትቀጭ አልፈቀዱም፡፡ ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ስደርሳቸውም ልጄ መማር አለባት ብለው በአቋማቸው ጸኑ፡፡  “ጠላፊው ታምሩ በቀሌ ይባላል፡፡ አብሮት በጠለፋው የተሳተፉ ወደ ሰባት ይሆናሉ፡፡ እሰራልሃለሁ ብሎ አስፈራርቶች፤ ከፈተናዋ እንዲህ አድርጎአት እየተሰቃየሁ ነው” ይላሉ አባት በምሬት፡፡

ሴና የተጠለፈችው ከትምህርት ቤቷ ቅጥር ግቢ ከጓደኞቿ መሃል ታፍና ተወስዳ ነው፡፡ “ጠላፊዎች በስለት መሳሪያ አስፈራርተውአቸው ተማሪዎች እና መምህራኖቿ እየተመለከቷት ነው በጠራራ ጸሃይ ተጠልፋ በኋላም ለከፋ የአካል ጉዳት የተዳረገችው” አባት በቁጭት የተናገሩት ነው፡፡

ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኝ ጫካ
የ17 ዓመቷ ታዳጊ ከዚህ ቀደም የጋብቻ ጥያቄ አቅርቦ በነበረ ግለሰብ ተጠልፋ ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባት አባቷ ተናግረዋል። ምስል፦ Seyoum Getu/DW

እስካሁን ድረስ እንዲህ ያለን የከፋ ሰብኣዊ ጥሰት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎች አንዳቸውም በህግ ቁጥጥር ስር እንዳልዋሉ አባት ይናገራሉ፡፡ ይህም የሆነው አከባቢያቸው ባለው የከፋ የጸጥታ ችግር እንደሆነ በመግለጽ፡፡ “ያለንበት አከባቢ አስቸጋሪ በመሆኑ የሰው ደም አፍስሰው ወደ ገጠር ሄደው እንደተቀመጡ ነው፡፡ አሁን ወደ ፈጣሪ እያለቀስን ነው፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደንም ክስ ከፍተን ብናስመሰክርም የሚያቀርባቸው ጠፋ” በማለት ፍትህን እንደሚሹም ገልጸዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ ስለዚህ ጉዳይ እና ተያያዥ በግጭት ወቅት የሚሰፋው አስከፊ የሴቶች መብት ጥሰቶች ላይ አስተያየታቸውን በዚህ ዘገባ ለማካተት ለኦሮሚያ ክልል ሴቶችና እና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መብራት ባጫ እና ለአከባቢው ባለስልጣናት በመደወል ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡

ግጭት ሴቶችን ለጉዳት እየዳረገ ነው

ኢትዮጵያ በግጭት ወቅት በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት አሳሳቢ ነው የሚሉት የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ኃላፊ ፌቨን አርዓያ፤ “በግጭት ወቅት ግጭቱ ውስጥ ያለው ወገን ተጋላጭ ሆኑ ወገኖችን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ዓለማቀፍና የአከባቢ ህግጋት ይደነግጋሉ” በማለት ተፈጸሚነቱን ግን በተለይም ግጭቱ እስካለ ድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸውታል፡፡

የሰብዓዊ ጥሰቱን የመከላከል አበይት ተግባራት እና ኃላፊነቶች ላይ አስተያየታውን ያከሉት ባለሙያዋ፤ “የህግ ማዕቀፎችን መከተል ለሁሉም ሰው ግዴታ ቢሆንም የጸጥታ አካላት ችግሩ ሳይደርስ አስቀድመው እንዲከላከሉና ከተከሰተ ደግሞ ፍትህን የማሰጠትና ተጎጂ በቂ ህክምና እና የስነአዕምሮ ምክር እንዲያገኙ መስራት ተጠባቂው ስራ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ 

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ