በታይላንድ ሱፐር ማርኬት ውስጥ 1000 ዶላር ይከፈላችኋል ተብለው የታለሉ ኢትዮጵያውያን ሰቆቃ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 2 2018
ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ ከካምቦዲያ ፅፎልን ነበር። መልዕቱም እሱን ጨምሮ አምስት ኢትዮጵያውያን በአንድ በካምቦዲያ ህገ-ወጥ ኩባንያ ውስጥ በግዳጅ ይሰሩ እንደነበር እና ከአራት ወራት በኋላ ከአሰሪዎቻቸው ማምለጥ እንደቻሉ፤ ነገር ግን እጅ የሰጡበት ጣቢያ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ 2000 የአሜሪካን ዶላር እንደጠየቃቸው፣ በአካባቢው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ሆነ ቆንሳላ አለመኖሩ ደግሞ ፈተናቸውን እንዳበዛው በመግለፅ የሚመለከተው አካል ጋር መልዕክትታቸውን እንዲደርስ ጠይቆናል። መልዕክቱን በአድማጮች ማህደር ዝግጅታችን ከማቅረብ ባሻገር፤ እኛም ደጋግመን መልዕክቱ በደረሰን ስልክ ቁጥር ደውለናል ግን በወቅቱ ማንንም ማግኘት አልቻልም ነበር። ሰሞኑን መልዕክቱን የፃፈልን ወጣት መልስ ሰጥቶናል። ኢትዮጵያ ገብተናልም ብሎናል።
የውጭ ሀገር "የስራ እድል"
ትክክለኛ ስሙን እንዳንጠቅስ ጠይቆናል። ይህም በደረሰበት የሞራል መሰበር ነው። በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ወጣት ወደ ታይላንድ ከመሄዱ በፊት ምዕራብ አርሲ ውስጥ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ በመንዳት ይተዳደር ነበር። ለዚህ ዘገባ ተስፋዬ ብለነዋል። “ወደ ውጪ ለመሞከር ከልጆች ጋር በምማከርበት ሰዓት አንድ የማውቀው ጓደኛዬ ከዚህ በፊት የሄዱ ሰዎች ታይላንድ አሉ በእነሱ በኩል ሞክር አለኝ እና አገናኘኝ። በቴሌግራም ነው የተዋወቅነው። ከዛ ታይላንድ እንደምንሄድ እና ሱፐር ማርኬት ውስጥ እንደምንሰራ አስረዱኝ። ”ይላል።
ከመጀመሪያው ሰዓት አንስቶ ከተስፋዬ ጋር የነበረው ወጣትም ትክክለኛ ስሙን እንዳንገልፅ ጠይቆናል። ለዚህ ዘገባ ባቢ ብለንዋል። እሱም እንደ ተስፋዬ የተገኘውንና «የስራ እድል» የተባለዉን አጋጣሚ ለመጠቀም አላቅማማም። ኢትዮጵያ ውስጥ ታክሲ በመንዳት ነበር የሚተዳደረው፣ „ እዛ አንድ ሺ ዶላር ይከፈላችኋል አለን። እዚህ የምናኘው ትንሽ ስለሆነ ራሳችንን እንቀይራለን ብለን ተስማማን። ቲኬት የምንቆርጥበትን ቀን ነገረን። የቱሪስት ቪዛ ይመታላችኋል። እዛ ከደረሳችሁ በኋላ ወደ ስራ ቪዛ ይቀየርላችኋል ብሎን ነበር የሄድነው”። ይላል ባቢ።
በእንደዚህ አይነት መንገድ ተታለው ለህገ ወጥ የማጭበርበር ስራ ወደ ታይላንድ ፤ ማይናማር እና ካምቦዲያ የሚሄዱ ብዙ ናቸው። በካምቦዲያ የሚገኝ ህገ ወጥ ማዕከል ምን እንደሚመስል በዚህ ሳምንት አሶሺየትድ ፕረስ ይፋ ያደረገው የቪዲዮ ዘገባ ላይ መመልከት ይቻላል። ማዕከሉ ከታይላንድ ድንበር 500 ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በታይላንድና ካምቦዲያ ድንበር ላይ በነበረ ግጭት ነው የታይላንድ ጦር ባለፈው ታህሳስ ወር ማዕከሉን በቁጥጥር ስር ያዋለው። ሥፍራዉ 80 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ወይም 150 የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክል ነው። 157 ህንፃዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም 29ኙ ቢሮዎች ናቸው። ክፍሎቹ ጎን ከጎን በተቀመጡ ኮምፒውተሮች የተጨናነቁ ናቸዉ። በዚህ ግዙፍ ማዕከል 10 000 የሚሆኑ ሰዎች ይሰሩ እና ይኖሩ እንደነበር የታይላንድ ጦር ይገምታል።
የኦሶሲየቲድ ፕረስ ዘገባን ያሳየነው ተስፋዬ የነበርንበት ቦታ በርግጥ ለታይላንድ ቅርብ ነበር ግን በ10 ሺ ሳይሆን በመቶ ሺ የሚቆጠር ሰው የነበረበት ቦታ ነው የነበርነው ይላል። ሁለቱም ኢትዮጵያውያን የተወሰዱበት ማዕከል እስኪደርሱ ድረስ መታለላቸውንም ይሁን ከታይላንድ ውጪ እንደነበሩ አላወቁም። በጉዞ ላይ የተነገራቸው የሚሰሩበት ቦታ ከባንኮክ ውጪ እንደሆነ ነው። ተስፋዬ ታይላንድ ከደረሱ በኋላ ያለውን እንዲህ ሲል ገልፆልናል። “ታይላንድ ስንደርስ ኤጀንቱ ከካምቦዲያ መኪና አምጥቶ ኤርፖርት ተቀበለን። ስራው ከተማ ውስጥ እንደሚሆን እንገምት ነበር ። ይዘውን ሄዱ የት እንደሚያደርሱን አናውቅም ነበር። ካምቦዲያ አደረሱን። ካምፓኒው ውስጥ አስገቡን። እንደገዙን እቃ ነው የሚቆጥሩን። በቀን እስከ 18 ሰዓት ነው የምንሰራው። የስራ ቋንቋው እንግሊዘኛ ነው”
ባቢም ቢሆን „ስራችን ሰው ማሳመን ነበር” ይላል። የቋንቋ ችሎታቸውን አጭበርባሪዎቹ ሱፐር ማርኬት ስትሸጡ ከሰው ጋር እንዴት መግባባት ትችላላችሁ በሚል አስቀድመው እንዴት እንዳረጋገጡ ገልፆልናል።
“ስትሸጡ ከሰዎች ጋር በእንግሊዘኛ ነው የምትግባቡት እንግሊዘኛችሁ እንዴት ነው ተብለን ነበር። ፐርፌክት ባትሆኑም ከሰዎች ጋር መግባባት መቻል አለባቹ የሚለውን በኦንላይ ኢንተርቪው አድርገውን ነበር።”
በደቡብ ምስራቅ እስያ በሳይበር የሚፈፀሙ ማጭበርበር ድርጊቶች በቅርብ ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ነው። እንደ የተባበሩት መንግስታት ባለሙያዎች ገለጻ፣ በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የወንጀል ኢኮኖሚዎች አንዱ ናቸው። ከ66 አገሮች የተውጣጡ ቢያንስ 300,000 ሰዎች በእንደዚህ አይነት ድርጅቶች ያለ ፍላጎታቸው እንደተወሰዱ ይታመናል። አንዳንድ ማዕከላት በሺ ወይም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን እንዳሰማሩ ይታመናል።
የእነ ባቢ የማጭበርበር ስራ ምን ይመስላል?
„አሜሪካ እና አውሮፓ ላይ ነው በፌክ ኮይኖች ገንዘብ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚደረገው። ከዛ ለመውጣት እስከ 10 ሺ ዶላር ነው የሚጠየቀው። እሱን ማድረግ አልቻልንም። ለአራት ወር በጫና ውስጥ ሆነን እየሰራን ነበር። በቀን ከ4 እስከ 5 ሰው ማሳመን አለብን። እሱን ማድረግ ካልቻልን ሰአት ተጨምሮ እንሰራለን። እንደበደባለን። በኤሬክትሪክ እንገረፋለን። ምግብ ላይሰጥ ይችላል። በጣም ከባድ ነበር " ይላል ባቢ። ተሞክሮውን ሲያካፍለን። እነዚህ የግዳጅ ሰራተኞች የተለያዩ ገፀ ባህሪያት ይሰጣቸዋል። በፋይናንስ እና አክሲዮን ገበያ በቂ እውቀት ያላቸው ፤ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ሆነው ይቀርባሉ። በተለያዩ ለእነሱ በተነደፉ የማጭበርበሪያ ዘደዎች እና ታሪኮች የሚጠበቅባቸውን ስራ ማሟላት ኢትዮጵያውያኑም ይሁኑ ሌሎች የግዳጅ ሰራተኞች ማከናወን አለባቸው።
የአሜሪካ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (FBI) ባለፈዉ ማክሰኞ ዕለት ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው አሜሪካውያን በ2025 ብቻ ተጭበርብረው 21 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኪሳራ ደርሶባቸዋል።
“ስራው ምንም ሊዋጥልን አልቻለም። መጀመሪያም ቢሆን ፍላጎቱ አልነበረንም። በሰዓቱ ከሰዎቹ ጋር ልንግባባ አልቻልንም። አራት ወር ሙሉ የተከፈለን ነገር የለም። በተለያየ ሰዓት ድብደባ ይደርስብናል። ከአራት ወር በኋላ ካምፓኒው ቦታ ሲቀይር በዛ ሰዓት ሸሽተን ጠፋን። ፓስፖርታችን እነሱ ጋር ነበር። ለፖሊስ አመለከትን። የት እንደነበርን። እነሱ ግንኙነት አላቸው። ሄደው ፓስፖርታችንን አመጡልን። ወደሀገራችን መልሱን ብለን አመለከትን።
እንድንመለስ እስከ 3000 ዶላር ጠየቁን
ኢሚግሬሽን አለ ካምቦዲያ ውስጥ እዛ ወሰዱን ” ይሁንና ኢሚግሬሽኑ ወደ ሀገራችን እንድንመለስ እስከ 3000 ዶላር ድረስ ጠይቆን ነበር የሚለው ተስፋዬ በመጨረሻም 2000 ዶላር ሊከፍሉ ተስማሙ። ፖሊሶቹ በተቀናጀ መልኩ እንደሚዘርፉ እና በእስር ቤቱ ውስጥ የቱርክ፤ የ ጀርመን እና የሩሲያ ዜጎች ታስረው አይተናልም ይላል ተስፋዬ“እኛን አሁን ሞራል በሚነካ መልኩ ሶስት ጊዜ በኤሌክትሪክ ሾክ አድርገውናል። በማዕከሉ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው።በወቅቱ ተመካክረን ጠፍተን ኢሚግሬሽን መግባት የቻልነው አምስት ብቻ ነበርን። አራታችን ቤተሰባችን አስቸግረን ያላቸውን ንብረት እየሸጡ 310 000 ብር ለእያንዳንዳችን ላኩልን።አንደኛው ቤተሰቦቹ ገንዘቡን ሊልኩለት አልቻሉም እዛ ነው ያለው። የተቀረነው አሁን ኢትዮጵያ ገብተናል። ሁለቱ ወደ ክፍለ ሀገር ቤተሰቦቻቸው ጋር ሄደዋል። እኛ ሁለታችን አዲስ አበባ ነው ያለነው። ስራ የለንም። በገንዘብም በሞራልም ተጎድተናል። የሚደግፈን አካል ብናገኝ ራሳችንን ለማደራጀት እና ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ ነን ። “
ተስፋዬ እና ባቢ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወጣቶች 100 በመቶ ርግጠኛ ባልሆኑበት ነገር በተለይም ወደ እስያ የሚደረግ ስምሪት ላይ እንዲጠነቀቁ ይመክራሉ። ሁለቱም የቤተሰባቸውን ዓይን ማየት ከብዷቸዋል። ካምቦዲያም በነበሩበት ወቅት ክፍያ ስላክተከፈላቸው ለቲኬት ከቤተሰብ ጓደኛ እና ዘመድ አድማድ የተበደሩትን ገንዘብ እንኳን መመለስ ባለመቻላቸው ከፍተኛ ሀዘን ላይ ይገኛሉ። „ከሰዎች ጋር መገናኘት ይከብዳል። ውጪ ሀገር ሄዶ ተቀይሮ ይመጣል የሚል ዘመድ እያለ፤ ቤተሰብ ከአንቺ ርዳታ እየጠበቀ ጭራሽ የቤተሰብን ንብረት አሽጠሽ ከአንቺ በታች ያሉትን እድል ዘግተሽ ከሰዎች ጋር ለመገኛነት በጣም ከባድ ነው። እኔ ራሱ ስለ ማይናማር የሰማሁት ካምቦዲያ ከገባሁ በኋላ ነው። ተመሳሳይ ካምፓኒ አለ ሲባል የሰማሁት። ወደ ዱባይ የሄዱ ጓደኞች ነበሩን፤ መስተንግዶ ተቀጥረው ያሉ፤ ሱፐር ማርኬት ውስጥ እና በሹፍርና የሚሰሩ። እንደዛ አይነት ስራ ነው እኛ የመሰለን። “ ይላል። ባቢ።
ተስፋዬም ቢሆን በሰዓቱ ምንም የሚያውቀው ነገር እንዳልነበር ገልፆልናል። ሁለቱም መልሰው የቤተሰቦቻቸውን ዓይን ማየት እንዲችሉ እና ወደ ቀድሞው ስራቸው እንኳን እንዲመለሱ በአሁኑ ሰዓት የማህበረሰቡን ድጋፍ ይሻሉ።