በአርሲ ዞን ሮቤ ዲዳዓ ወረዳ በንጹሐን ላይ የተፈጸመው ጥቃት
ዓርብ፣ ሚያዝያ 16 2018
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሮቤ ዲዳዓ ወረዳ ባሳለፍነው ሰኞ ሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ቤተሰቦች እና የቤተክስቲያን አገልጋዮች ገለጹ። ሙልዬ ፍሰኃ የተባሉት ለዓመታት በዚያ የኖሩ አገልጋይ በተጠቀሰው ቀን አመሻሹ ላይ ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር ከቤታቸው ተጠርተው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ግድም ወደ ጫካ ተወስደው እንደተገደሉ ነው የተሰማው።
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የሟች አቶ ሙልዬ ፍሰኃ ቤተሰብ ግድያው የተፈጸመበትን ሂደት ሲያስረዱ «አደጋው የደረሰው በዕለቱ 12 ምሽት አካባቢ ነው» ነው ያሉት። አስተያየት ሰጪው የቤተሰብ አባል አክለውም፤ ታጣቂዎቹ በዚያ ሰዓት እንደገቡ ሟቹንና ሌሎች ሁለት ሰዎችንም ጨምረው ይዘዋቸው በመውጣት ወደ ምሽት ሦስት ሰዓት አከባቢ የመሳሪያ ድምጽ መሰማቱን ገልጸዋል።
ሌላው ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየት የሰጡን በአካባቢው የጄና መብሩቁ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ፤ ሰኞ ዕለት ከቤታቸው ተወስደው የተገደሉት አቶ ሙልዬ ፍሰኃ፤ በታጠቁ አካላት ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ነው ብለዋል። «ጄና መብሩቅ ቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው የሚኖሩት» ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ቤተ ክርስቲያኑን ለብዙ ዓመታት ማገልገላቸውንም ገልጸዋል። ሰኞ ሚያዚያ 12 ቀን ለ13 አጥቢያ ምሽቱን አንድ ሰዓት አካባቢ ወደ ቤታቸው የመጡ «ያልታወቁ» ያሏቸው የታጠቁ አካላት በቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ገና ከብት አጉረው ወደ ቤታቸው እንደገቡ ይዘዋቸው ወጥተዋል ነው ያሉት።
አስተያየት ሰጪው የሃይማኖት አባት እንዳሉት በዕለቱ ምሽቱን የተገደሉት አቶ ሙሉዬ ፍሰኃ ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር ጭምር ወደ ጫካ ተወስደው እንደሆነም ነው የገለጹት። «ሙስሊም ሁለት ወንድሞች አሏቸው፤ እሳቸው ክርስቲያን ናቸው፤ ሦስቱንም ነው ወደ ጫካ ወስደው የገደሏቸው» ብለዋል። አስከሬናቸውም በማግስቱ ጠዋት ተገኝቶ መቀበሩን ገልጸዋል።
በዚህ አካባቢ ብቻ ከ2017 ዓ.ም. ወዲህ እንኳ በተለያዩ ጊዜያት ወደ 46 ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን በታጣቂዎች መገደላቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪው የቤተ ክርስቲን አገልጋይ፤ ምዕመናንም በተለያዩ ቀበሌያት ለመፈናቀል መገደዳቸውን አስረድተዋል። «በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ ፍቅሬ የተባሉ አንድ ግለሰብ መጋቢት 16 ተገድለው ከአሁኑ ጋር ከ2017 ወዲህ በተመሳሳይ መልኩ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥን ወደ 46 አድርሶታል፤» ብለዋል።
ይህ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረው የታጣቂዎች ጥቃት ደግሞ በርካታ ሰዎችን ከሃብት ቄዬያቸው ማፈናቀሉንም እንዲሁ አስተያየት ሰጪው አስረድተው፤ ስጋቱ አሁንም አለማባራቱን ተናግረዋል። «በየዘመዱ በከተማ ከቀዬያቸው ተፈናቅለው የተጠለሉ በርካታ ናቸው» ያሉት አስተያየት ሰጪው የሃይማኖት አባት፤ ስጋቱ እየተገታም እንዳልሆነ በአስተያየታቸው ገልጸዋል።
ዶይቼ ቬለ ነዋሪዎቹ ከጸጥታው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ስላነሱት ጥቃትና ተፈጽሟል ስለተባለው ግድያ ከወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባያን ቃሲም ተጨማሪ አስተያየት ለማግኘት በእጅ ስልካቸው በመደወልና እና የጽሑፍ መልዕክት በመላክም ያደረግነው ጥረት ለዛሬ ምላሽ አላገኘም።
ከዚህ በፊት በአርሲ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም መንግሥት በተጠናከረ መልኩ የጸጥታ አካላትን በማሰማራት ንጹሐን ዜጎችን እንዲጠብቅ መንግሥታዊው የ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መጠየቁ ይታወሳል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ