የእሥራኤል-ዩናይትድ ስቴትስ ኢራን ጦርነት ዳፋ ለኢትዮጵያ፦ እንወያይ
እሑድ፣ ሚያዝያ 18 2018
የእሥራኤል-ዩናይትድ ስቴትስ ኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከሁለት ወራት ግድም አንስቶ በመላው ዓለም የኤኮሚ እና የደሕንነት ምስቅልቅል አስከትሏል ። የጦርነቱ ዳፋ ከመካከለኛው ምስራቅ አልፎ መላው ዓለምን አዳርሷል ። ኢራን በፍኖተ ሆርሙዝ በኩል ነዳጅ የጫኑ መርከቦች እንዳያልፉ መከልከሏ ኢትዮጵያን ጨምሮ በየአገሩ ብርቱ የነዳጅ እጥረት አስከትሏል ።
ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አንስቶ፣ ለማዳበሪያ እና ለከፍተኛ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችም ነዳጅ እጅግ በአንገብጋቢነት ከሚያስፈልጋቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያም አንዷ ናት ። የነዳጁ እጥረት በኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዲሁም በምርት ግብዓቶች አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉ እየተስተዋለ ነው ።
በአንዳንድ አካባቢዎች የነዳጅ እጥረቱ ተባብሶ ነዳጅ በጥቁር ገበያ በውድ ዋጋ እየተሸጠ ስለመሆኑ መረጃዎች እየወጡ ነው ። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቤንዚን አንዱ ሊትር ከ1500 እስከ 2000 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ በርካቶች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ከሰሞኑ የትንሣኤ በዓል ወቅትም የተለያዩ ግብአቶች ከሌላ ጊዜው በተለየ ዋጋቸው እጅግ ከፍ ብሎ ታይቷል ።
የእሥራኤል-ዩናይትድ ስቴትስ ኢራን ጦርነት የተኩስ አቁሙ ቢራዘምምም በሆርሙዝ ሰርጥ ኢራን ቁጥጥሯን በማጥበቋ እና ዩናይትድ ስቴትስም በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው ገደብ ባለመነሳቱ ውጥረቱ አይሎ ቀጥሏል ። ለመሆኑ ይህ የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት መቀጠሉ ኢትዮጵያ ላይ ያሳደረው ጫና እንዴት ይቃኛል? የውይይታችን ዐቢይ ትኩረት ነው ።
በውይይቱ ሦስት እንግዶች ተሳታፊ ናቸው ።
-
ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ፦ የኤኮኖሚ ተንታኝ
-
አቶ መስፍን አማን፥ የፖለቲካ ተንታኝ
-
ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ የዶይቸ ቬለ የዋሽንግተን ዘጋቢ ናቸው ።
እንግዶቻችን በውይይቱ ተሳታፊ ለመኾን ፈቃደኛ በመኾናችሁ፦
ሙሉውን ውይይት በድምፅ ማእቀፉ በማገናኛ በኩል ማድመጥ ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ