ውይይት፤የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ 8 የስልጣን አመታት ሲቃኙ
እሑድ፣ ሚያዝያ 4 2018
ከስምንት ዓመታት በፊት፣ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዶክተር ዓብይ አህመድ በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ወደ መንበረ ስልጣን መጥተዋል። የእሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት በወቅቱ የኢህአዴግን አመራር ይወቅሱ በነበሩ በብዙዎች ዘንድ የእድገት እና የለውጥ ተስፋ አሳድሯል።የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ፣ውጭ የሚገኙ የመንግስት ተቃዋሚዎችን ነፍጥ ያነሱትን ጨምሮ ወደ ሀገር እንዲገቡ በማድረግ፣በፕሬስ ነፃነት፣ የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋት እና ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ሰላም በመፍጠር ያደረጓቸው የመጀመሪያዎቹ ማሻሻያዎች፤ በኢህአዴግ የ27 ዓመታት የአስተዳደር ዘመን ያልተከወነ አዲስ ምዕራፍ ሆኖ ታይቷል። እነዚህ ጥረቶች በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም የኖቤል የሰላም ሽልማትን ጨምሮ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ዓለም አቀፍ እውቅና አስገኝተውላቸዋል።ያም ሆኖ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግስት እንዳጀማመሩ አለመቀጠሉ፤ የታዩት ለውጦች እና ተስፋዎች እየመተመናመኑ እናውስብስብ ፈተናዎች እየታዩ መምጣታቸውን ብዙዎች ይናገራሉ።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በአንድ በኩል የታላቁ ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ፣የአረንጓዴ አሻራ እና ምንም እንኳ ትችት ቢቀርብበትም አንዳንድ የከተማ ልማቶች የበስኬት ሲጠቀሱ፤በሌላ በኩል የሀገሪቱን መረጋጋት እና የወደፊት አቅጣጫ የፈተኑ የትግራይን ጦርነት ጨምሮ የውስጥ ግጭቶች፣የፖለቲካ ውጥረት እና የኢኮኖሚ ጫናዎች ሀገሪቱ አጋጥሟታል። መጀመሪያ አካባቢ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የፖለቲካ ምህዳር እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃም ወደ ኋላ ተመልሷል በሚል መንግስታቸው በመብት ተሟጋቾች ዘንድ ይተቻል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያበጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ምን አሳካች? ምንስ ተግዳሮቶች ገጠሟት? ወደፊትስ ምን መደረግ አለበት ? የዛሬው የእንወያይ ዝግጅት ትኩረቶች ናቸው።
በዚህ ውይይይት አራት እንግዶችን ጋብዘናል።
1, በፈቃዱ ሀይሉ ፀሀፊ ፣እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነው።
2, ዶክተር ንጉሴ በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ የአስተዳደር እና ዴሞክራሲ ትምህርት ክፍል ፤የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የፖለቲካ ሳይንስ መመህር ናቸው።
3, ዶክተር አብዱል መናን መሀመድ የፋይናንስ ባለሙያ ከለንደን
4, አቶ ነጌሶ ኦዳ ጠበቃ እና የህግ ባለሙያ ናቸው።
የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ሙሉ ዝግጅቱን እንዲad,ምጡ እናጋብዛለን።
ፀሐይ ጫኔ