1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፍኖተ ካርታ ወደየት አለ?

እሑድ፣ ጥር 12 2011

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለውጦች እና ማሻሻያዎችን መተግበራቸውን ብዙዎች ይስማማሉ። ሆኖም እርሳቸው የሚመሩት መንግስት ከነጠላ እርምጃዎች በዘለለ የኢትዮጵያን የወደፊት አቅጣጫ የሚጠቁም ዝርዝር ፍኖተ ካርታ አለማዘጋጀቱን አንስተው የሚተቹም አሉ።

https://p.dw.com/p/3Bq5A
Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

ውይይት፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፍኖተ ካርታ ወደየት አለ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከስምንት ወራት ገደማ በፊት ወደ ስልጣን ሲመጡ ስለ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነጻነት እና የሀሳብ ልዩነት አስፈላጊነት ተናግረው ነበር። በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባሰሙት ንግግር ስለ ህገ መንግስት በአግባቡ መተግበር፣ ስለ ሰብዓዊ እና ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንደዚሁም ዜጎች በአገራቸው የአስተዳደር መዋቅር ስላላቸው ተሳትፎ አፅንኦት ሰጥተው አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ ንግግራቸው በስልጣን ዘመናቸው ሊያሳኳቸው የሚያስቧቸውን ሌሎች ዕቅዶችም ዘርዝረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከዚያ በኋላ በተከተሉት ወራት በወሰዷቸው እርምጃዎች ለውጦች መምጣታቸውን ብዙዎች ይስማማሉ። ሆኖም የእርሳቸው መንግስት ከነጠላ እርምጃዎች በዘለለ ሀገሪቱ ወደፊት የምትሄድበትን አቅጣጫ የሚጠቁም ዝርዝር ፍኖተ ካርታ አለማዘጋጀቱን አንስተው የሚተቹ ወገኖች አሉ። የ“እንወያይ” መሰናዷችን ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ፍኖተ ካርታ የግድ ያስፈልጋል ሲሉ ተከራክረዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዱ ጋዜጠኛ እና በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ የሚሰሩ ባለሙያ አቶ መስፍን ነጋሽ ናቸው። አቶ መስፍን የዛሬ ስድስት ወር ግድም፣ በሐምሌ 2010 የፍኖተ ካርታን አስፈላጊነት የሚያወሳ ባለ16 ገጽ ጽሁፍ ለንባብ አብቅተው ነበር። “ኢትዮጵያ፣ የዲሞክራሲያዊ ሽግግር ፍለጋ- ለተሃድሶ እና ለሽግግር ዘመን የፍኖተ ካርታ ጥቆማ” በተሰኘው በዚሁ ጽሁፋቸው ፍኖተ ካርታ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አካላት መዘጋጀት እንደሚችል አመላክተዋል።  

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የህግ ባለሙያ እና የመንግስት ጉዳዮች አማካሪው አቶ ምስጋናው ሙሉጌታም ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ ለመውጣት የአጭር እና የረጅም ጊዜ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል። በሌሎች ዘርፎች ላይ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ቢቻልም ለፖለቲካው ቅድሚያ መሰጠት አለበት ይላሉ። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።   

ተስፋለም ወልደየስ