1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትአፍሪቃ

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና እየተሰጠ ነው

ሐና ደምሴ
ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2018

የ 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ትናንት ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በመላ ሀገሪቱ በይፋ ተጀምሯል። ተማሪዎች ወደ ፈተና ማዕከላትና የመፈተኛ ክፍሎች ከመግባታቸው በፊት ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር ተደርጎባቸዋል።

https://p.dw.com/p/5GOEY
በአዲስ አበባ ከተማ የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና
በአዲስ አበባ ከተማ የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከሚፈተኑ ተማሪዎች ጥቂቱምስል፦ Hanna Demisse/DW

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና እየተሰጠ ነው

ይህም የፈተናውን ፍጹም ፍትሃዊነትና ታማኝነት ለማረጋገጥ ነው ቢባልም ይህ ጥብቅ ቁጥጥር በተማሪዎች ላይ ጭንቀትን ፈጥሮባቸው እንደ ነበር ተናግረዋል። ፈተናው እና ቁጥጥሩ የተማሪዎችን በራስ የመተማመን ስሜት ለማጎልበት እና በሥራቸው ብቻ ተመስርተው ውጤታማ እንዲሆኑ ለመድረግ ያለመ ነው ተብሏል።  

ኢትዮጵያ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እዳስታወቀው ፈተናው እስከ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም. ድረስ  ይቆያል። በዚህ ፈተና ላይ በአጠቃላይ 563,501 ተፈታኞች ይቀመጣሉ። ከእነዚህም መካከል 306,456ቱ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ 257,045ቱ ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው።  

ፈተናው በ 607 የፈተና ማዕከላት ውስጥ በስድስት ዙሮች የሚሰጥ ሲሆን፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ዙር ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ታውቋል። የዘንድሮውፈተና ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት የውጤት ማሽቆልቆል ማሻሻያዎችን ለማስመዝገብ ትልቅ ዝግጅት የተደረገበት መሆኑን የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች ገልጸዋል።  

የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና
የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተጀምሯልምስል፦ Hanna Demisse/DW

 

በአዲስ አበባ DW በተገኘባቸው በሦስት የፈተና ማዕከላት ውስጥ፣ተማሪዎች ያለ ችግር ወደ ተመደቡባቸው የፈትና ማዕከላት ክፍሎች መግባታቸውን ተመልክተናል። በማዕከላቱ የተደረገው ጥብቅ ፍተሻና ዝግጅት በተለየ መልኩ የሚጠቀስ ነው። ተማሪዎች የተከለከሉ ዕቃዎችን እንደ ስልክ፣ታብሌት እና ስማርት ሰዓት ያሉ ሳይይዙ በመምጣት ለሕጉ ተገዢ መሆናቸውን አሳይተዋል። ወደ ማዕከላት ሲገቡም አስቀድሞ የተዘጋጀላቸውን የፈተና መግቢያ ካርድ፣ የተማሪ መታወቂያ፣የተፈቀደ እስክሪብቶ ወይም እርሳስ እና ባዶ ወረቀት ብቻ መያዛቸውን አረጋግጠናል።

መነፅር የሚያረጉ ተማሪዎች በሀኪም የታዘዘ ለመሆኑ የሀኪም ፍቃድ ወረቀት ሲጠየቁ DW በተመልክቷል። ፈተናውን ተፈትነው የወጡ ተማሪዎች የፈተና ውሎ ያለምንም የደኅንነት ስጋት በሰላም  መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ካለፉት ዓመታት ዝቅተኛ የውጤት ሪከርድ በመነሳት ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተማሪዎቹ ይናገራሉ።በመላው ሀገሪቱ የተጀመረው ይሄው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በቀጣዮቹ ቀናትም በተመሳሳይ የዝግጅትና የጥንቃቄ ደረጃ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ለተፈታኝ ተማሪዎች በሙሉ መልካም ዕድል እንመኛለን።

ሃና ደምሴ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ