ከምርጫ ማግሥት ማን ምን አለ? የተሰጡ አስተያየቶች
ረቡዕ፣ ግንቦት 26 2018
የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ በኢትዮጵያ እና አባል አገራቱ ሰኞ ዕለት "ምርጫ ማካሄድ ያልቻሉ ሁሉም የምርጫ ክልሎች በቀጣይ ምርጫ የማካሄድ እድል እንዲያገኙ ተስፋ እናደርጋለን" አሉ። የምርጫውን ሒደት በይፋ ያልታዘበው ኅብረቱ፦ «አጠቃላይ ምርጫ መካሄዱን እንቀበላለን» ሲል ዛሬ ረቡዕ ባወጣው አጭር መግለጫ ጠቅሷል። ምርጫ ቦርድ፦ «በተሳካ ኹኔታ ተከናውኗል» ያለውን ጠቅላላ ምርጫ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት «የጨረባ» ብሎታል ። ምርጫው «ዴሞክራሲን አያዋልድም፣ መፍትሔም አይፈይድ" ሲልም ዛሬ ባወጣው መግለጫ አጥጥሎታል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) «በተወሰኑ ቦታዎች ያልተፈቀደላቸው ግለሰቦች በምርጫ ጣቢያው ውስጥ መገኘት» ከታዘባቸው ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሶ፣ «በአንጻራዊነት ስኬታማና ሰላማዊ የሆነ ምርጫ» መከናወኑንና ለዚህም ምርጫ ቦርድ ሊመሰገን እንደሚገባ ገልጸል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመ) በፊናው ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አካታች ነበር ብሏል። የአዲስ አበባ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ የሁሉንም አስተያየት አሰባስቦ ቀጣዩን ዘገባ አጠናቅሯል ።
የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ በኢትዮጵያ ስለ ምርጫው ምን አለ?
ኢትዮጵያ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ያከናወነችውን ጠቅላላ ምርጫ መካሄዱን እንቀበላለን ሲሉ ዛሬ ማለዳ ባወጡት መግለጫ የጠቀሱት የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ በኢትዮጵያ እና 25 የሕብረቱ አባል ሀገራት ኤምባሲዎች፣ በዕለቱ ምርጫ ያልተከናወነባቸው ያላቸው ግን በስም ያልጠቀሳቸው የምርጫ ክልሎች ምርጫ የማድረግ እድል ይሰጣቸዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ይህ የሕብረቱ መግለጫ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና መንግሥት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ዐውታሮች በስፋት የተጋራ እና በበጎ የታየ ሲሆን፣ የምርጫው ሂደት ላይ ልዩነት ያላቸው አካላት ደግሞ ሲቃወሙት እና ግርታ እንደተሰማቸው ተስተውሏል።
ልዑኩ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻዎችን አበረከቱት ላለው አስተዋጽዖ አድናቆት እንዳለውም ጠቅሷል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምርጫውን "የጨረባ" ሲል አጣጣለ
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተባለው የፓርቲዎች ቅንጅት ግን ምርጫውን "የጨረባ" ያለው ሲሆን "ዴሞክራሲን አያዋልድም፣ መፍትሔም አይፈይድም" በሚል አጣጥሎታል። ትብብር አክሎም "ውጤቱ ምንም ቢኾን የትኛውም ዕጩ በትብብሩ ስም ምክር ቤት እንዳይገባ፣ ቢገባም ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው።" የሚል አቋም አራምዷል። እንዲያም ሆኖ "የቦርዱ ኃላፊዎችና ውስን ድርጅቶች ላደረጉትና እያደረጉ ላለው ጥረት እውቅና አለን" በማለት መንግሥት "የሕዝብን ድምጽ እስከሚያከብር" ድረስ ትግሌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብሏል።
ኢሰመጉ በአወንታም፣ በአሉታም የተመለከታቸው ጉዳዮች
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) 433 ቋሚና ተዘዋዋሪ ታዛቢዎችን በማሰማራት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርጫውን መታዘቡን ዐሳውቀል። ታዛቢዎቹ ከ 800 በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መታዘቸውን የጠቀሰው ሀገር በቀሉ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ "በአንጻራዊነት ስኬታማና ሰላማዊ የሆነ ምርጫ" መከናወኑን ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። "መራጮች በምርጫው ቀን ድምጻቸውን ለመስጠት የነበራቸውን ተነሳሽነት፣ በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች የነበረው የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦት በቂ በሚባል ደረጃ መኖሩ፣ ምርጫ በተከናወነባቸው በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የጎላ የጸጥታ መደፍረስ ሳያጋጥም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ መጠናቀቁን" በበጎ ጠቅሷል።
እንዲያም ሆኖ ሚስጥራዊ የድምጽ መስጫ ሳጥን ውስጥ መራጭ እያለ ወደ ውስጥ በመግባት የሥነ ልቦና ጫና ማድረግ፣
ከፍተኛ የመራጮች ሰልፍ መኖር፣ በተወሰኑ ቦታዎች ያልተፈቀደላቸው ግለሰቦች በምርጫ ጣቢያው ውስጥ መገኘት፣ የጸጥታ አካላት ከምርጫ ጣቢያው በተፈቀደላቸው ርቀት ጠብቆ አለመቀመጥ ከታዘባቸው ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ።
ይህንን መሰል ችግር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም መመልከቱን እና እርምት ማድረጉን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል ።
ብሔራዊው የመብቶች ድርጅት - ኢሰመኮስ ምን አለ?
ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ብሔራዊው የመብቶች ድርጅት- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የግል እና የውጭ መገናኛ ብዘኃንን ባልጋበዘበት የትናንቱ መግለጫው፣ ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አካታች ነበር ብሏል። ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ተቋማቸው ምርጫው በሰብአዊ መብቶች መርኾዎች መሠረት መከናወኑን የመከታተል ሥልጣን እንዳለው፣ ሂደቱም ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ስለማሟላቱ የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መሠረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያልተፈጸመበት ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ የምርጫ መሥፈርቶችን ያሟላ እንደነበር ገልፀዋል።
በትናንቱ መግለጫቸው ተቋማቸው ምርጫውን "በተሳካ ኹኔታ አከናውኗል" ያሉትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉን ዶቼ ቬለ ይህንን ለማለት መለኪያዎቹን እንዲያብራሩ ጠይቋቸው ምላሽ ሰጥተዋል። የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ሥራን እና ከምንም በላይ በታቀደው መሠረት ግንቦት 24 ምርጫው መከናወኑን አስረጂ ጠቅሰዋል።
ኃላፊዋ እስከ ትናንት ማክሰኞ ምሽት 2 ሰዓት ገደማ ድረስ ቆጠራ እየተደረገ መሆኑን፣ በተለይ አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የቆጠራ ሥራ እንዳልተጠናቀቀ ገልፀው ነበር። የቦርዱ የክትትል ቡድን የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ማጣራት ያልተገባ ሥራ ሲያከናዉኑ የተገኙ የተባሉ ሁለት ምርጫ አስፈፃሚዎች ከሥራ መታገዳቸውንም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምርጫው "ሰላማዊ ሆኖ" ተጠናቋል ብሏል
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምርጫው "ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን" ዛሬ ከእኩለ ቀን በኋላ አስታውቋል። ምክር ቤቱ "ልዩነቶቻችንንና ችግሮቻችንን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመፈታት በምርጫው የታየውን ሰላም በማስቀጠል የበኩላችንን ሚና በመወጣት፣ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም በጋራ እንድንቆም" የሚል ጥሪም አቅርቧል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026