የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) የአዲስ ስታንዳርድ ፈቃድ እንዲመለስ ጠየቀ
ረቡዕ፣ የካቲት 18 2018
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) የተሰረዘው የአዲስ ስታንዳርድ የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን የምዝገባ ምስክር ወረቀት እንዲመለስ ጠየቀ። ሲፒጄ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያሳለፈውን ውሳኔ የቁጥጥር ተግባር ሳይሆን «የበቀል ርምጃ» ብሎታል ። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አዲስ ስታንዳርድ «የሚዲያ ሥነ ምግባርን፣ የኢትዮጵያ ሕጎች እና የሀገርንና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል» ሲል ከትናንት (የካቲት 17 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) ጀምሮ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ መሰረዙን ዐሳውቋል ። ሲፒጄ ይህንን ርምጃ «በኢትዮጵያ ወሳኝ ዘገባዎችን ለማዳከም የታቀደ የተቀናጀ ዘመቻ አካል» ብሎታል ። አዲስ ስታንዳርድ ዛሬ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ደብዳቤ እንደሚያስገባ ለዶይቼ ቬለ ገልጿል ።
የሲፒጄ መግለጫ ምን ይላል?
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዲስ ስታንዳርድ የበይነ - መረብ መገናኛ ዐውታር ላይ ትናንት የወሰደው ርምጃ "ነፃ ጋዜጠኝነትን [ሥራን] ዝም እያሰኘ ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "አዲስ ስታንዳርድ የሚዲያ ሥነ ምግባርን፣ የኢትዮጵያ ሕጎች እና የሀገርንና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል።" ብሏል። ባለሥልጣኑ የመገናኛ ዐውታሩ እንዲታረም እና "አጥፊ" ካለው አካሄዱ እንዲቆጠብ "በተደጋጋሚ ምክር ሲሰጥ ቢቆይም ለመታረም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል" ሲል ርምጃውን የወሰደበትን ምክንያት አብራርቷል።
ባለሥልጣን እንዳለው አዲስ ስታንዳርድ "የሙያ ሥነ ምግባር እና የሀገርና የሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም አክብሮ እንዲሰራ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ለመታረም ፈቃደኛ አልሆነም።"
የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር ዛሬ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ ተቋሙ በባለሥልጣኑ ማቋቀሚያ እና መተዳደሪያ አዋጅ መሠረት በተቀመጡ ከፈቃድ ስረዛ በመለስ ያሉ ሂደቶችን ማለትም ከቃል እስከ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እና የእርምት ማሳሰቢያዎች አልደረሱት ተናግረዋል።
"ለአዲስ ስታንዳርድ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት እንደነበር [ባለሥልጣኑ] ገልጿል። ያ ሙሉ በሙሉ እውነት አይደለም። ውሸት ነው።"
ዛሬ ለባለሥልጣኑ የበላይ አካል - ለቦርዱ ደብዳቤ እናስገባለን
ዶቼ ቬለ ዋና አዘጋጁ የሰጡትን ይህንን ምላሽ ከባለሥልጣኑ ማረጋገጥ አልቻለም። አዲስ ስታንዳርድ "በተደጋጋሚ" የመንግሥት እርምጃዎች ሰለባ እንደነበር ገልጾ፣ ሚያዝያ 2017 ዓ.ም ፖሊስ የተቋሙን የአንድ ባልደረባ መኖሪያ ቤት በመበርበር፣ "ሦስት ሥራ አስኪያጆችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ንብረቶቹን ወስዶ" እንደነበር፣ ከዚያ አስቀድሞ ሰኔ 2013 ዓ.ም ደግሞ የአሳታሚው የሥራ ፈቃድ በመነጠቁ ተቋሙ ታግዶ እንደነበር ገልጧል። ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር እንደሚሉት ዛሬ ለባለሥልጣኑ የበላይ አካል ደብዳቤ ለማስገባት ሂደት ላይ ናቸው።
"ዝርዝር ነገሮችን ጠቅሰን - የአካሄድ ጥሰቶችን ጠቅሰን ለቦርዱ ደብዳቤ እናስገባለን።"
ሲፒጄ በእሥር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ሕጋዊ ሥርዓቱን የጠበቀ የፍርድ ሂደት እንዲያገኙ ጠይቋል
በሌላ በኩል ሲፒጄ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በእሥር ላይ ከሆኑ ሁለት ዓመታት ያለፋቸው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው እና መስከረም አበራ ፍትሐዊ፣ ግልጽ እና ሕጋዊ ሥርዓቱን የጠበቀ የፍርድ ሂደት እንዲያገኙ ጠይቋል።
ሲፒጄ አዲስ ስታንዳርድ ላይ የተወሰደው ርምጃ "በኢትዮጵያ ወሳኝ ዘገባዎችን ለማዳከም የታቀደ የተቀናጀ ዘመቻ አካል” አድርጎ እንደሚመለከተው ገልጿል። የመገናኛ ዐውታሩ ዋና አዘጋጅ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የርምጃው ባህሪ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ጠቅሰዋል
"ይህ ነገር በአጠቃላይ በሚዲያ ዐውዱ ላይ የመጣ ነገር ነው። የፖለቲካ ውሳኔ ያለ በሚመስል ኹኔታ የነፃ ሚዲያው ላይ እየተወሰደ ያለ ርምጃ ነው።"
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በሀገሪቱ በሚስተዋሉ የዘፈቀደ እሥሮች ጋዜጠኞችም ሰለባ መሆናቸውን ገልፀው፣ እንዲህ ያለው ኹኔታ "የመገናኛ ብዙኃን ዐውዱን እንደሚጎዳ" በመግለጽ አደረግነው ባሉት "ውትወታ" በተለይ በሶማሌ ክልል ታስረው የነበሩ አምስት ሀሳብ የሚያንሸራሽሩ እና ሁለት ፍርደኛ የነበረ ጋዜጠኞች በይቅርታ እንዱፈቱ አድርገናል ሲሉ ትናንት ተናግረዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ