1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የምርጫው ዘመቻ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 18 2018

ሰኞ ግንቦት 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ የፀጥታ ይዞታ አለባቸው በተባሉ አከባቢዎች በአካል በመድረስ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረጉን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ገለጸ ። በምርጫ ሂደቱም በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎች የምርጫ ቅስቀሳ ስልቶች ያሉትን እድሎች ተጠቅሞ ደጋፊዎቹ ጋር ለመድረስ የተቻለውን ማድረጉንም ዐሳውቋል ።

https://p.dw.com/p/5ELpT
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ዋና ጽ/ቤት
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ዋና ጽ/ቤትምስል፦ Seyoum Getu/DW

ኦነግ ከምርጫው ምን ልምድ ቀስሟል?

ሰኞ ግንቦት 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ የፀጥታ ይዞታ አለባቸው በተባሉ አከባቢዎች በአካል በመድረስ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረጉን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ገለጸ ። ኦነግ ከ1980ዎቹ አጋማሽ የሽግግር መንግስቱ ተሳትፎ በኋላ በምርጫ ሲሳተፍ ይህ የዘንድሮው የመጀመሪያው ይኾናል ተብሏል ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እየተገባደደ ባለው የሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ ውስጥ በሰፊው ተሳትፎ እያደረጉ ከሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ይጠቀሳል፡፡

የምርጫ ተሳትፎውና ቅስቀሳው

ፓርቲው በዚሁ የምርጫ ሂደት የተገኘውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ በእጁ ያለውን አማራጭ ፖሊሲ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ጥሯል ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ፤ ሂደቱ ግን ከተግዳሮት ነጻ ነው ሊባል የሚችል እንዳልነበር ዐሳውቀዋል፡፡ "ያለንን የፖሊሲ አማራጭ በያጋጣሚው ለህዝባችን አድርሰናል” ያሉት አቶ ለሚ፤ ያ ማለት ግን "ችግሮች የሉም ማለት አይደለም” በማለት ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረቶች መደረጋቸውን በዚህም "በተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎች” ለመጠቀም መጣራቸውን አንስተዋል፡፡

ከምርጫው ምን ልምድ ተቀስሟል?

ከ1980ዎቹ አጋማሽ የሽግግር መንግስቱ ተሳትፎ በኋላ በምርጫ  ተሳትፎ ይህ የመጀመሪያው ተሳትፎ እየሆነለት የሚገኘው ኦነግ ከዚህስ ምርጫ ምን አይነት ልምድ አግኝቶ ይሆን ተብለውም፤ "የድርጅቱን ስነምግባር እንዲሁም በወጣቶች የተሞላ ድርጅት እንደሆነ ሁሉ ያሳንበት አጋጣሚን የፈጠረ ነው” ብለዋል አቶ ለሚ፡፡ በምርጫ ሂደቱ "ከአፈሙዝ ወደ ምርጫ ሳጥን የመጣንበት” አጋጣሚም የፈጠረ ሲሉ ሂደቱን ገልጸውታል፡፡

የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ለሚ ምርጫው ከተግዳሮት ነጻ አለመሆኑንም ባስረዱበት አስተያየታቸው፤ "አጠቃላይ የአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ” አንዱ ፈተና መሆኑን እንዲሁም ፓርቲው እንደ አገራዊ ፓርቲ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ከአንድ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ብቻ እየተንቀሳቀሰ በሰፊው ተሳትፎ ለማድረግ መገደዱ ግን ቀላል ፈተና እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡

ኦነግ በአንድ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ብቻ ተ,ወስኖ በሰፊው ተሳትፎ ለማድረግ መገደዱ ብርቱ ተግዳሮት መኾኑን ጠቁሟል
ኦነግ በአንድ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ብቻ ተ,ወስኖ በሰፊው ተሳትፎ ለማድረግ መገደዱ ብርቱ ተግዳሮት መኾኑን ጠቁሟልምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኦነግ የምርጫ ቅስቀሳው ሁኔታ

ኦነግ በምርጫ ሂደቱ በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎች የምርጫ ቅስቀሳ ስልቶች ያሉትን እድሎች ተጠቅሞ ደጋፊዎቹ ጋር ለመድረስ የተቻለውን ስለማድረጉም የገለጹት አቶ ለሚ፤ በአካልም ቢሆን በተለያዩ አስቻይ የጸጥታ ሁኔታ ባለባቸው አከባቢዎች ደርሶ በአካል ቅስቀሳ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡ "በአዲስ አበባ እና በዚያው በሚገኙ የሸገር ከተማ ክፍለ ከተሞች፤ እንደ ባሌ እና አርሲ ባሉ ደቡብ ምስራቃዊ የኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች” በአካል በመድረስ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ቃል አቀባዩ በምዕራብ ኦሮሚያ በጊምቢ እና የቀለም ወለጋ አከባቢዎች እንዲሁም በምስራቅ ኦሮሚያ እንደ ሀራረጌ ባሉ ዞኖች እና በድሬዳዋ ከተማም ጭምር ቅስቀሳ ስለማድረጋቸው ገልጸዋል፡፡

ኦነግ ለሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫው በአራት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች 163 እጩዎችን ማቅረቡን ከዚህ በፊት የፓርቲው ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ ዓለማየሁ ድሮ ለዶይቸ ቬለ ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ለሚ እንዳሉትም የቴክኖሎጂ ሁኔታውና የፀጥታ ተግዳሮቱ ፓርቲው በፈለገበት መጠን ተሳትፎ እንዳያደርግ ውስን ተግዳሮቶች ብፈጥሩም በኦሮሞ ትግል ውስጥ ትርጉም ባላቸው አከባቢዎች ላይ ግን የተሻለውን ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

ሥዩም ጌቱ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ