የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ፓርቲዎች ተቃወሙ
ሰኞ፣ የካቲት 16 2018
የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስት የምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ፣ ሳልሳይ ወያነ እና ባይቶና ፓርቲዎች ተቃወሙ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁመራ፣ አዲረመፅ፣ ኮረም፣ ጠለምት እና ራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች “ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ” የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን አሳውቋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን ያሳወቀው ጥር 25 ቀን 2018 እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ያሠራጨው ደብዳቤ ይጠቁማል። በደብዳቤው መሠረት ውሳኔው የሚመለከተው “በትግራይ እና በአማራ ክልላዊ መንግሥታት መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩ” የተባሉ አምስት የምርጫ ክልሎችን ይሆናል።
በዚህ መሠረት አቶ አገኘሁ ተሻገር በአፈ-ጉባኤነት የሚመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የይገባኛል ጥያቄው እስከ ሚፈታ የሁመራ፣ የአዲረመፅ፣ የኮረም ኦፍላ፣ የጠለምትና የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ” ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ “በአካባቢዎቹ ላይ የተነሣው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ-መንግሥት ውሳኔ ሲፈታ አመቺ ጊዜ ተመርጦ” የክልል ምክር ቤት ምርጫ “ወደፊት እንዲካሔድ መወሰኑን” እንዳሳወቀ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሣኔ መሠረት የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተጠቀሰው አግባብ ለመፈጸም የሚያስችለውን ሕግ እና ሥርዓት በመጠበቅ ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን” አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ውሳኔው የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት እና በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ሥምምነት “በግልጽ የሚቃረን” እንደሆነ ተችቷል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ “የትግራይ ሕዝብ ውክልና እና ድምጽ በሌለበት” የጸደቀውን ውሳኔ አጥብቆ እንደሚያወግዝ በክልሉ ኮምዩንኬሽን ቢሮ በኩል ባሠራጨው መግለጫ አስታውቋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ “ከባድ እና ብዙ መዘዝ የሚያስከትል” በመሆኑ “በአፋጣኝ እንደገና እንዲጤን እና አደገኛው አካሔድ እንዲታረም” ጥሪ አቅርቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካሪ በሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ፣ ሳልሳይ ወያነ እና ባይቶና ፓርቲዎችም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ተቃውመዋል።
የስምረት ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በጻፉት ደብዳቤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የምርጫ ክልሎችን የማዋቀርም ሆነ ክልሎችን ከነባር አስተዳደራዊ መዋቅራቸው ውጭ በፌድራል መንግሥት ሥር እንዲሆኑ የመወሰን ምንም ዐይነት ሕገ-መንግሥታዊ ውክልና” እንደሌለው ገልጸዋል።
ስምረት ፓርቲ በደብዳቤው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጀምሮታል ያለውን “ሕገ-ወጥ ዳንኪራ በአስቸኳይ እንዲያቆም እና ለሕገ-መንግሥቱ የበላይነት እንዲገዛ” አሳስቧል። ፓርቲው “ማስተካከያ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ በምርጫም ሆነ በመሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንደማይሳተፍ” በደብዳቤው ገልጿል።
አርታዒ ልደት አበበ