1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት፤ አብላጫ ድምጽ ወይስ ተመጣጣኝ?

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 4 2018

ምርጫ በኢትዮጵያ በአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት የሚመራ ነው፡፡ ይህ የምርጫ ስርዓት ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት እንዲቀየር የሚጠይቁ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ግን በርካቶች ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/5DetM
ምርጫ 2018 ኢትዮጵያ
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይካሄዳልምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት፤ አብላጫ ድምጽ ወይስ ተመጣጣኝ?

 

ምርጫ በኢትዮጵያ በአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት የሚመራ ነው፡፡ ይህ የምርጫ ስርዓት ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት እንዲቀየር የሚጠይቁ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ግን በርካቶች ናቸው፡፡ ለመሆኑ የምርጫ ስርዓቱን በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚጠይቁት ከአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት እንዳይመጣ እንቅፋት የሆነው ምንድነው?

አብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት

ኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት ከአብላጫ ድምጽ ወደ ተመጣጣን ድምጽ የምርጫ ስርኣት እንዲቀየር ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ በአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ከ50 በመቶ በላይ የምርጫ ድምጽ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥምረት የፌዴራል እና ክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ተቆጣጥረው መንግሥት እንዲመሰርቱ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ሕግ ሆኖ እየሠራ ያለውን የምርጫ ስርዓት «በተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት» እንዲተካ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄ እያቀረቡ ያሉት ለምን ይሆን በሚል የተጠየቁት የሕግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ፤ «ይህ የምርጫ ስርዓት ሌሎች ከ49 በመቶ በታች ድምጽ ያገኙ ያለተወካይ እንዲቀሩ የሚያደርግ ነው» በማለት ተመጣጣኝ የምርጫ ድምጽ ስርዓት የሚባክን ያሉትን ድምጽ እንደሚቀንስ በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡ ይህም ባሉት የክልል እና የፌዴራል ምክር ቤቶች ውስጥ ተወካይነታቸው እንዲሰፋ እንደሚያደርግ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

ተመጣጣኝ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ነውን?

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በሰብሳቢና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ከተመጣጣን ድምጽ የምርጫ ስርኣት አኳያ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው ብለዋል፡፡ «እስካሁን እኮ አንዱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሬት እንዳይዝ ያደረገው የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርኣት ነው» ያሉት ዶ/ር ራሔል፤ ምርጫው በተመጣጣኝ የምርጫ ድምጽ ስርኣት ቢመራ «ሁሉም በየአካባቢው ባገኘበት ድምጽ መጠን ስለሚካትት» ፍትሃዊ ምርጫ የማድረግ እድሉ ላቅ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የሕገመንግሥት ማሻሻያ እንደ ብርቱ ፈተና

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ፓርቲዎች አሁን በሥራ ላይ ያለው የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት በተመጣጣኝ ድምጽ የምርጫ ስርዓት እንዲተካ በጋራ ምክር ቤቱ መድረኮች እና በምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም በተዘጋጀው መድረክ ጥያቄዎችን በስፋት ማቅረባቸውን አስታውሰው አስተያየት የሰጡት የሕግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ፤ ለምርጫ ስርዓቱ ለውጥ ገቢራዊ አለመሆን ግን የሕገመንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ ትልቁ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

«ገዢው ፓርቲን ጨምሮ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች እና ሌሎችም የምክር ቤቱ አባል ያልሆኑ ፓርተዊች አሁን ሕገመንግሥቱ ላይ ተቀምጦ ያለውን የምርጫ ስርዓት ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት እንዲቀየር በሙሉ ድምጽ ያለምንም ልዩነት ስምምነታቸውን የገለጹበት ሁኔታ ነው የነበረው» በማለትም ለውጥ ለማምጣት ግን የሕገመንግሥትም ማሻሻያ ጭምር በማስፈለጉ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽንም እንደ ግብዓት መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

ለዚህ ዓለማ ሕገመንግሥቱን ማሻሻል ግን ቀላል ነገር እንዳልሆነ የሕግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛው ሲያስረዱ፤ የምርጫ ስርዓቱንም ለመቀየር ቀላል ካልሆነው የሕገመንግሥቱ ማሻሻያ መጠባበቅ የግድ ማለቱን አስገንዝበዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ሽዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር