የኢትዮጵያ ምርጫ የቀጥታ ዘገባ
ታትሟል ረቡዕ፣ ግንቦት 5 2018የመጨረሻ ማሻሻያ ረቡዕ፣ ግንቦት 26 2018
ማወቅ ያለብዎት
- ሰኞ፤ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ምርጫ ተካሂዷል
- በፀጥታ ምክንያት ወደ 143 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ” አለመከፈታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገልጧል
- ዐሥራ አንድ ክልሎች እና ሁለት ከተሞች በቦርዱ የምርጫ ክልል ስም ዝርዝር ውስጥ ተጠቅሰዋል
- በዝርዝሩ ውስጥ የትግራይ ክልል የለበትም
- ከቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው 24 አገር አቀፍ እና 45 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው
- 10438 ዕጩዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ እንደሚገኙ ምርጫ ቦርድ ጠቅሷል
- ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 02 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የምርጫ ውጤት ማረጋገጥ (በቦርድ)
ከታች ስለ ቀጣዩ የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተከታታይ ዘገባዎችን በቀጥታ እና ወዲያው መከታተል ትችላላችሁ ።
ምርጫ ያልተካሔደባቸው የምርጫ ክልሎች ድምጽ የመስጠት “ዕድል ይሰጣቸዋል” የሚል ተስፋቸውን የአውሮፓ ኅብረትና 25 ኤምባሲዎች ገለጹ
በኢትዮጵያ የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ እና በአዲስ አበባ የሚገኙ የኅብረቱ አባል አገራት ኤምባሲዎች ግንቦት 24 ቀን 2018 ምርጫ ያልተካሔደባቸው የምርጫ ክልሎች ድምጽ የመስጠት “ዕድል ይሰጣቸዋል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው አስታወቁ።
በኢትዮጵያ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ምርጫ መካሄዱን በበጎ እንደሚቀበሉ የኅብረቱ ተልዕኮ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ 25 ኤምባሲዎች ጋር በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ምርጫው በተካሔደ በሁለተኛው ቀን ዛሬ ረቡዕ መግለጫውን ከኅብረቱ ጋር ካወጡ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ኤምባሲዎች መካከል የጀርመን እና የፈረንሳይ የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎች ይገኙበታል። የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ያልሆኑት ካናዳ፣ ኖርዌይ እና ስዊትዘርላንድም ምርጫን በተመለከተ በመግለጫው አቋማቸውን ካንጸባረቁ መካከል ናቸው።
በመግለጫው “የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች እና የሲቪል ማኅበራት ተዋናዮች ያበረከቱትን አስተዋጽዖ እናደንቃለን” ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) እንደ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ያላቸውን ጠቃሚ ሚና እንገነዘባለን ያለው የጋራ መግለጫው ዘገባዎቻቸውን በጉጉት እንደሚጠብቅም አስታውቋል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ምርጫ ማካሄድ ያልቻሉ የምርጫ ክልሎች በሙሉ ይህን ለማድረግ እድሉ እንደሚሰጣቸው ተስፋ እናደርጋለን ሲል በኢትዮጵያ የኅብረቱ ልዑካንና የኅብረቱ አባል ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች የጋራ መግለጫ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምርጫ ጣቢያዎች ቆጠራ ላይ” ናቸው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአዲስ አበባ ምርጫ ጣቢያዎች [የድምጽ] ቆጠራ ላይ” እንደሆኑ ተናገሩ። ኃላፊዋ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በአማራ እና በሶማሌ ክልሎች ቆጠራ ያልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ዛሬ ማምሻ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ በምርጫ ጣቢያዎች የሚደረገው የድምጽ ቆጠራ ያልተጠናቀቀው ትላንት ግንቦት 24 ቀን 2018 በነበረ“ረጅም ሰልፍ ምክንያት” እንደሆነ ገልጸዋል። መራጮች ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ሲያመሩ “በቀረበው ዝርዝር እና መዝገብ ላይ የመፈለግ ሒደት ብዙውን ነገር እንዳረዘመው” ገልጸዋል።
ኃላፊዋ በዛሬው ማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ “በተሳካ ሁኔታ” እንዳካሔደ ተናግረዋል። የምርጫው ሒደት በጣቢያዎች የተሰበሰቡ ድምጾች ወደ ምርጫ ክልል ተሸጋግረው “የማዳመር ሥራ” የሚከናወንበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
በምርጫው ሒደት የቦርዱ የክትትል ቡድን የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ክትትል “ያልተገባ” ሥራ ሲያከናዉኑ የተገኙ የተባሉ ሁለት የምርጫ አስፈፃሚዎች መሰናበታቸው ተገልጿል። በአዲስ አበባ “አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች መግባት የሌለባቸው ሰዎች ታይተዋል” የሚል ጥቆማዎች ቀርበው “አንዳንዶቹ ትክክል” ሆነው እንደተገኙ ሜላተወርቅ ተናግረዋል።
በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ “ሰላማዊ፣ አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ያልተፈጸመበት” እንደነበር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማረጋገጡን ኃላፊው ብርሀኑ አዴሎ ተናግረዋል።
በሻሻ የምርጫ ጣቢያ የድምፅ ቆጠራ ውጤት
በኢትዮጵያ የተካሄደው የሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ የድምፅ ቆጠራ ውጤት፣ ዛሬ ማክሰኞ ከማለዳው ጀምሮ በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች እየተለጠፈ ይገኛል።
በጅማ ከተማም ሆነ በዞኑ ስር በሚገኙ የምርጫ ክልሎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በሰላም መጠናቀቁን የዞኑ የምርጫ አስተባባሪ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። የዶቼ ቬለ ዘጋቢ በጅማ፣ በአጋሮ እና በበሻሻ ከተሞች ተገኝቶ በምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተለጠፉትን የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶች ተመልክቷል።
እንደ ምርጫ ቦርድ መርሃ ግብር ከሆነ፣ ነገ ረቡዕ በምርጫ ክልል ደረጃ የቅድመ ውጤት ይፋ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ከበሻሻ የምርጫ ጣቢያ የተገኘውን የድምፅ ቆጠራ ውጤት ከፎቶው ይመልከቱ። #ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026
በሀዋሳ የምርጫ ውጤቶች እየተለጠፉ ነው
በሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላምርጫጊዜያዊ ውጤቶች በየምርጫ ጣቢያዎች በመለጠፍ ላይ ናቸው። የዶቼ ቬለ ዘጋቢ በተዘዋወረባቸውየምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ ውጤቶች ተለጥፈው ተመልክቷል። ነዋሪዎች በየምርጫው ጣቢያዎቹ በመገኘት ውጤቶችንእየተመለከቱ ይገኛሉ። #ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026
«40 ሚሊየን ሕዝብ ድምፅ ሰጥቷል» ምርጫ ቦርድ
ምርጫ 2018
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እስካሁን ምርጫ ቦርድ በገለጸው መሠረት 40 ሚሊየን ሕዝብ ድምፅ ሰጥቷል። ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ በሰጠው መግለጫ ነው። ምርጫው በታቀደው መሠረት ትናንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፤ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት በአንዳንድ አካባቢዎች እኩለ ሌሊት እስኪያልፍ በመዝለቁ ዛሬ የድምፅ ቆጠራና ቅድመ ውጤት መረጃዎች ይጠበቃሉ። ከአዲስ አበባ በደረሰን መረጃ መሠረት እስከጠዋት አራት ሰዓት ተኩል ድምፅ እየቆጠሩ የነበሩ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ለመረዳት ችለናል። በአንጻሩ ቆጠራ አጠናቀው ውጤት ለጥፈው የዘጉ መኖራቸውንም ለመረዳት ችለናል።
ትናንት አዲስ አበባ ላይ ድምፁን ለመስጠት በየምርጫ ጣቢያው የተሰለፈው መራጭ በመብዛቱ የድምፅ አሰጣጡ ሰዓት ከታሰበው አልፎ መራዘሙን የምርጫ ቦርድ አስታውቋል። እኩለ ሌሊት ያለፈባቸው አካባቢዎች መኖራቸውም ተገልጿል። #ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026
የአፍሪቃ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ኃላፊ ስለ ምርጫው ምን አሉ?
የአፍሪቃ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ኃላፊ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ የኢትዮጵያው ምርጫ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ሲሉ መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ከቀትር በፊት ዘግቧል። የኢትዮጵያን ምርጫ ከሚታዘቡት አንዱ የሆነውን የአፍሪቃ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎችን የሚመሩት ኬንያታ፦ «የታላቂቱ የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ዋና ከተማ» ባሏት በኢትዮጵያ፤ የምርጫው ሒደት ስርዓት ጠብቆ ይካሄደል ብለን ተስፋ እንደርጋለን፤ እናምናለንም ብለዋል። በምርጫው የ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ 10,438 ዕጩዎች ቀርበዋል። ይሁንና የትግራይ ክልልን ጨምሮ በ46 የምርጫ ክልሎች ዛሬ ድምፅ እንደማይሰጥ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ዐሳውቆ ነበር።
በኢትዮጵያ ምርጫ የድምጽ መስጫ ሰዓት እስከ ዕኩለ ሌሊት ተራዘመ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የድምፅ መስጫ ሂደት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች” የድምፅ አሰጣጡን እስከ ለሊቱ 6 ሰዓት አራዘመ። ቦርዱ ከውሳኔው የደረሰው “በሥምሪት ላይ ያለው የክትትል ቡድኑያቀረበለትን ሪፖርት ተመልክቶ” እንደሆነ ዐሳውቋል። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልዋና ከተማ አሶሳ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ከ20 ገደማ ድረስ መራጮች ተሰልፈው ድምፅ በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ዶይቸ ቬለ ተገንዝቧል። በአማራ ክልል ደሴ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች አሁንም ድምጽ እየተሰጠ ይገኛል።
በሐዋሳ ከተማ በሚገኝ ምርጫ ጣቢያ ተዘግቶ ድምጽ ቆጠራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የዶቸ ቨለ ዘጋቢ ታዝቧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የተመዘገቡ መራጮች መርጠው የተጠናቀቁባቸው ጣቢያዎች ላይ አስፈጻሚዎች የድምፅ ቆጠራ ሂደቱን እንዲያከናውኑ” አሳስቧል።
ቁጥሮች ስለ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ምርጫ ምን ያሳያሉ?
ለመሆኑ ለዘንድሮው 7ኛ ምርጫ ከፍተኛ ዕጩዎችን ያስመዘገበው ፓርቲ የትኛው ነው? ሰኞ ግንቦት 24 ቀን፣ 2018 ዓ ም ምርጫ በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች እየተከናወ ነው ። ከብልፅግና ፓርቲ በመቀጠል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ያቀረበው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ነው። በቅርቡ መሪው የነበሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋን አሰናብቶ በአቶ ኢዮብ መሳፍንት የተካው ኢዜማ በ291 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚወዳደሩ ዕጩዎች አስመዝግቧል። ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤት አባላት በብዛት በማቅረብ የኦሮሚያ ክልል ቀዳሚ መሆኑን የኢትዮጵያ ብራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው ዘገባ ይጠቁማል ።
ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ እና ታምራት ዲንሳ በምርጫው ዋዜማ ምን ታዝበው ነበር?
ስለ ምርጫ 2018 ዘገባ ለማቅረብ የዶይቸ ቬለ አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ እና ታምራት ዲንሳ ወደ ኢትዮጵያ አቅንተዋል ። በምርጫ ዋዜማ ነጋሽ በአዲስ አበባ እንዲሁም ታምራት ጂማ ከተማ እስኪደርስ የታዘቡትን ነቪዲዮ ዘገባ አካፍለውናል ። ከቦን ከተማ ማንተጋፍቶት ስለሺ ሁለቱንም ትናንት ማምሻውን አነጋግሯቸው ነበር ። ሁለቱም ስለ ፀጥታ ኹኔታ እና ሌሎች ጉዳዮች ያዩትን ያስተዋሉትን በቪዲዮ ውይይቱ ላይ አብራርተዋል ።
ይህን የቪዲዮ ዝግጅቱን እንዲመለከቱ ጋብዘናል ። የቪዲዮ ውይይቱ የተቀረጸው በትናንትናው ዕለት ነው ።
#ምርጫ2018
#Ethiopiaelection2026
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ፦ የፎቶ ዘገባ
ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2018 በተካሄደዉ የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ ገልጿል። ከዚህ ውስጥ 46 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ይህም በመራጮች ብዛት በጎርጎሪያኑ 2023 በናይጄሪያ እና በ2025 ደግሞ በግብፅ የተካሄዱ ምርጫዎችን ተከትሎ ከአፍሪካ ሦስተኛው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል። እስከአሁን ባለው መረጃ በናይጄሪያ 93 ሚሊየን ፣ በግብፅ ደግሞ 69 ሚሊየን የሚጠጉ መራጮች የተሳተፉባቸው ሆነው ተዘግበዋል። ባለሙያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በናይጄሪያና በግብፅ የታየው የመራጮች ቁጥር መጨመር አገራቱ ካላቸው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ይላሉ ፡፡
ስለ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ፦ የፎቶ ዘገባውን በዚህ ማገናኛ ይመልከቱ
የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች በምርጫው ዋዜማ ምን ታዝበው ነበር?
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች በትናንትናው ዕለት በምርጫ ዋዜማ ከያሉበት ቦታ ስለታዘቡት የፀጥታ ኹኔታ እና ሌሎች ጉዳዮች ያዩትን ያስተዋሉትን አካፍለውናል ። የፋኖ ታጣቂዎች ከአምቡላንስ ውጪ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸውን ባሳወቁበት የአማራ ክልል፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከአምቡላንስ ውጪ የተሽከርካሪ ገደብ እንደጣሉ በተናገሩበት የኦሮሚያ ክልል። በመዲናዪቱ አዲስ አበባ፤ ከመዲናዪቱ አዲስ አበባ ወጣ ብለው በሚገኙ ከተሞች፤ እንዲሁም በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በድሬዳዋ እና ሐረር ስላለው የፀጥታ ኹኔታ እና የምርጫ ዝግጅት በቪዲዮ ውይይቱ ላይ አብራርተዋል ።
የቪዲዮዝግጅቱን እንዲመለከቱ ጋብዘናል ። የቪዲዮ ውይይቱ የተቀረጸው በትናንትናው ዕለት ነው ።
«በሰላማዊ መንገድ የሚመጡ ወገኖቻችን ካሉ በራችን ክፍት መሆን አለበት» ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፦ «በሰላማዊ መንገድ የሚመጡ ወገኖቻችን ካሉ በራችን ክፍት መሆን አለበት» ሲሉ ዛሬ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከሥፍራው ተናገሩ ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው በበሻሻ ዛሬ ጠዋት ድምፅ ሰጥተዋል። አብይ ይህን የተናገሩት ዛሬ ድምፅ ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲያሰሙ ፓርቲያቸው ቢያሸንፍ በሀገሪቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ ለምርጫ ዘገባ በሻሻ በሚገኘው የዶቼቬለ ባልደረባ ታምራት ዲንሳ ተጠይቀው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ በ390 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ውስጥ በሚገኘው ጎማ 2 የምርጫ ክልል ከሁለት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ጋር ነው የሚወዳደሩት ።
መራጮች ዛሬ ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት ለሚወዳደሩ እጩዎች ድምፅ ሲሰጡ ውለዋል።
የድሬዳዋ ውሎ በምርጫው ቀን
ዛሬ ሲካሄድ በዋለው ሰባተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በድሬደዋ ድምፅ ሲሰጡ ዶይቼ ቬለ ካነጋገራቸው አስተያየት ሰጭዎች መካከል አቶ ብርሃኑ ስሜ እና አቶ ዘይኑ መሀመድ የምርጫውን ሂደት "ግርግርና ወከባ ያልታየበት ሰላማዊ" ነው ብለዋል። ዶይቸ ቬለ በድሬደዋ ምርጫ ክልል አንድ ያነጋገራቸው አቶ አምባቸው ካሴ በቂ መረጃ ተሰጥቷቸው በግልፅነት መምረጣቸውን ተናግረዋል። የሰባ አራት አመት እድሜ ባለፀጋው አቶ ሚሊዮን መንግሥቱ የምርጫውን ሒደት "ለኔ ልዩ ነው " በማለት ገልፀዋል።
"ድምፃችንን ሰጥተናል አሸናፊው ይቅናው" የሚል አስተያየት የሰጡት ደግሞ ወ/ሮ ፈሪሀ መሀመድ ናቸው። በምርጫ ጣቢያ ድምፅ ሲሰጡ ያገኘናቸው የድሬደዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስተባባሪ አቶ ዮናስ በትሩ በበኩላቸው የምርጫው ሂደት ሰላማዊ መሆኑን መመልከታቸውን ገልፀዋል። በድሬደዋ እየተካሄደ ባለው የምርጫ ሂደት የኢጋድ እና ሌሎች የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫ ጣቢያዎችን ተዘዋውረው ሲምታዘቡ ተመልክተናል።
“በፀጥታ ምክንያት ወደ 143 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ” አለመከፈታቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ “በፀጥታ ምክንያት ወደ 143 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች” አለመከፈታቸውን ተናገሩ። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የድምፅ አሰጣጥ ከተጀመረ በኋላ በጸጥታ ችግር መቋረጡን ተናግረዋል።
ሜላተወርቅ የምርጫውን ሒደት አስመልክቶ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የጸጥታ ችግር ያጋጠመን አካባቢዎች አሉ። በዚህም ምክንያት የድምጽ አሰጣጥ ሒደቱ የተቋረጠባቸው ምርጫ ክልሎች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ሌሎች 695 የሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች ዘግይተው መከፈታቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ተናግረዋል። በኃላፊዋ ማብራሪያ መሠረት በሰዓቱ የተከፈቱት የምርጫ ጣቢያዎች 50,188 ናቸው።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እየተካሔደ ባለው ድምጽ አሰጣጥ በ39,723 የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች ተገኝተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪ ወኪሎች በ41,978 ምርጫ ጣቢያዎች እንደተገኙ ሜላተወርቅ ተናግረዋል። “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች በመላ አገሪቱ ወጥተው ድምፃቸውን እየሰጡ መሆኑን” ምርጫ ቦርድ በሚያደርገው ክትትል መገንዘቡንም ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው የምርጫው ሒደት “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች ሰልፍ ላይ መሆን ያጋጠመን ትልቅ ችግር ነው” ያሉት ሜላተወርቅ በተለይ አዲስ አበባን ጨምሮ ዲጂታል ምዝገባ በተደረገባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ረጅም ሰልፎች መታየታቸውን አስረድተዋል።
መራጮች ዛሬ ከማለዳዉ 12 ሰአት ጀምሮ በደሴ ከተማ ድምፃቸዉን እየሰጡ ነዉ
110 የምርጫ ጣቢያ ባለዉ የደሴ የምርጫ ክልል ለ7ተኛዉ ሀገር አቀፍ ምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ከማለዳ ጀምሮ ድምፃቸዉን እየሰጡ ሲሆን ዘወትራዊ የሥራ እንቅስቃሴ ግን በከተማዋ ዐይታይም መራጮች ግን ድምፃችንን ለሚበጀን ሰጥተናል ይላሉ ። ድምፃቸዉን ሰጥተዉ ሲወጡ ዶይቸ ቬለ ያነጋገርናቸዉ መራጮች ለኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በእጂጉ ያስፈልጋታል ብለዋል ።
በምርጫ ሒደቱ ከወጣቶች እስከ አረጋዉያን የተሳተፉ ሲሆን፤ በሞቃታማ የአየር ፀባይ ዉስጥ በረጃጅም ሰልፎች ድምፃቸዉን ይበጀናል ላሉት ለመስጠት ተሰልፈዉ ተመልክተናል ። በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ዛሬ የወትሮዉ እንቅስቃሴዋ የለም አንድና አንድ በከተማዋ ዉስጥ 7ተኛዉ ሀገር አቀፍ ምርጫ ብቻ ነዉ እየተከወነ ያለዉ። ስለመራጮች አሀዛዊ መረጃ ለመሰጠት የከተማዋ የምርጫ አስተባባሪዎች ፈቃደኛ ባልሆኑበት የዘንድሮዉ ምርጫ ከማለዳዉ 12 ሰዓት ጀምሮ የከተማዉ ህዝብ ድምፁን ለወደደዉ እየሰጠ ነዉ ።