1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትግራይ ክልል ከኢትዮጵያ ፌዴሬሽን እየራቀ ነው?

ሐሙስ፣ ግንቦት 20 2018

ከጥቅምት 2013 ጀምሮ የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች የሉትም። የፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ለጥልቅ ልዩነቶቻቸው መፍትሔ አበጅተው ምርጫ ካልተካሔደ የትግራይ ክልል በምክር ቤቶቹ ሳይወከል የሚቀርባቸው ዓመታት ወደ አስር ከፍ ሊል ይችላል።

https://p.dw.com/p/5ETJ8
Äthiopien Mekelle 2025 | Parade der Tigray-Verteidigungskräfte
ምስል፦ Million Haileslassie/DW

በትግራይ ክልል በሁሉም 38 የምርጫ ክልሎች ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 እንደማይደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ባለፈው ማክሰኞ አረጋግጠዋል። ሜላተወርቅ የሚመሩት ተቋም የትግራይ ክልልን ጨምሮ "አስቻይ ኹኔታዎች” ባሉባቸው ሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ምርጫ የማካሔድ ዕቅድ ነበረው።

ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ፣ ትንሳኤ ስርዓት ቃንጪ ሃቂ እና ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታን የመሳሰሉ ፓርቲዎች ለምርጫው ተመዝግበው ነበር።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቃል አቀባይ ሚኬኤለ አስገዶም ግን “እኛ ምርጫ የምናካሒድበት ሁኔታ ላይ አይደለንም ያለንው” ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ” የክልሉ ነዋሪዎች በ146 መጠለያዎች እና በስደት ሱዳን የሚገኙ መሆናቸው አንዱ ምክንያት ነው።

“በምዕራብ ትግራይ፣ በጸለምት ሌላ አካባቢዎችም እንዲሁ በጠላት ሥር ያለው ሕዝባችን ነጻነት የለውም” የሚሉት የህወሓት ቃል አቀባይ “ከ40% በላይ የትግራይ ሉዓላዊ ግዛት ጠላት ይዞት ነው ያለው” ሲሉ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት “ነባራዊ ሁኔታው ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል” እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሥት በበጀት እና የነዳጅ እጥረት ምክንያት ትምህርት ቤቶች አስቀድመው እንዲዘጉ ወስኗል። የጥሬ ገንዘብ እና የመድሐኒት እጥረት የክልሉን ሕዝብ እየተፈታተኑ ይገኛሉ። አቶ ሚኬኤለ “አሁን ስለምርጫ የምናወራበት ወቅት ሳይሆን ስለ ሕዝባችን ቀጣይ ህልውና፣ ከዚህ የህልውና አደጋ እንዴት መውጣት እንችላለን የሚለውን ነገር ነው እየሠራን ያለንው” ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ተወካዮች ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቼ ይመለሳሉ?

ላለፉት ስድስት ገደማ ዓመታት የትግራይ ክልል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ አልነበረውም። ውክልናውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያጣው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሕገ-መንግሥት ተተርጉሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ዘመን እንዲራዘም መደረጉን በመቃወም ህወሓት በወሰደው እርምጃ ነበር።

ህወሓት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ የትግራይ ክልል ተመራጮች እና በፌድራል መንግሥት ውስጥ የተሾሙ ባለሥልጣናት ሥራቸውን እንዲያቆሙ በመስከረም 2013 ትዕዛዝ ሰጠ። ወቅቱ ጳጉሜ 2012 በትግራይ ክልል የተካሔደው ምርጫ በፌድራል መንግሥት ተቀባይነት ባለማግኘቱ በአዲስ አበባ እና በመቐለ መካከል ሲብላላ የቆየው ፖለቲካዊ ውጥረት የተካረረበት ነበር።

ታደሰ ወረደ እና ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
ህወሓት ታደሰ ወረደ የሚመሩት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ የደብረፅዮን ገብረሚካኤል ነባር መንግሥት ወደ ሥራ መመለሱን አስታውቋል። ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ስድስተኛው የኢትዮጵያ ምርጫ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከሰባት ወራት ገደማ በኋላ የተካሔደ በመሆኑ በቅርቡ ሥራቸውን በሚያጠናቅቁት ምክር ቤቶች ውስጥ ለትግራይ የተመደቡ መቀመጫዎች ባዶ ሆነው ቆይተዋል።

በአሜሪካው ኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ ማወር የሕግ ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ፈንታው “አንድ የምርጫ ዘመን ትግራይ ሳትሳተፍ አልፋለች። አሁን ደግሞ ሌላ አምስት ዓመት ትግራይ አትሳተፍም። በድምሩ 10 ዓመት ይሆናል ማለት ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

በዩኒቨርሲቲው በሕገ-መንግሥት ሕግ እና ሕገ-መንግሥት ቀረጻ ላይ የፒኤችዲ ጥናታቸውን ጭምር በማከናወን ላይ የሚገኙት አቶ አለማየሁ “ከዚህ በኋላ ‘ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነች' ብሎ ማውራት ይቻላል ወይ?” ብለው በመጠየቅ መልሰው “እኔ እርግጠኛ አይደለሁም” ሲሉ ይመልሳሉ።

“ሁለት የምርጫ ዘመን ብቻ ነወይ ትግራይ ምርጫ የማትሳተፈው? የምትገለለው? በሚለው ነገር ላይ እርግጠኛ አይደለሁም። ሦስት ዘመን ቢሆን 15 ዓመት ነው። አራት ቢሆን 20 ዓመት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 ከተካሔደ ደም አፋሳሽ እና አውዳሚ ጦርነት በኋላ የተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት የትግራይ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በፌድራል መንግሥት የነበረው ውክልና ወደነበረበት እንዲመለስ ዕድል ከፍቶ ነበር።

የሥምምነቱ ፈራሚዎች “የፌድራል ተቋማት እና ኤጀንሲዎች ቁጥጥርን ጨምሮ የፌድራል መንግሥት ሥልጣን በትግራይ ክልል ወደነበረበት እንዲመለስ” ተስማምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሥምምነቱ አንቀጽ 9 “የፌድራል መንግሥት የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ የትግራይ ክልልን ውክልና በፌድራል ተቋማት ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ እና በሚመለከታቸው ሕጎች መሠረት ማረጋገጥ እና ማመቻቸት አለበት” በማለት ይደነግጋል።

ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ “ትግራይን ወደ ፌዴሬሽኑ መመለስ” እንዲሁም “የትግራይ የፖለቲካ ውክልና በፌድራል የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ማረጋገጥ” የመጀመሪያ እርምጃ መሆን እንደነበረበት አቶ አለማየሁ ይሞግታሉ።

“ይህንን ከማድረግ ይልቅ ግን ህወሓት ከሁለት ተከፈለ። ሁለቱም አንጃዎች ያተኮሩት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሬዝደንትነቱ ሥልጣን ‘ለእኔ ይገባኛል' በሚለው ላይ ነው እንጂ የትግራይ ሕዝብ ውክልና እንዴት እናረጋግጥ በሚለው ላይ አልነበረም” በማለት ይተቻሉ።

የትግራይ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ምርጫ እስከሚካሔድ ድረስ ሥራ ላይ የሚቆይ ነበር። በሥምምነቱ መሠረት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት የትግራይ ክልል ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካዮች መመረጥ ነበረባቸው።

በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተፈረመው ሥምምነት ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 የተካሔደውን ጦርነት ቢገታም ቁልፍ አላባዎቹ አልተተገበሩም።  የፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በአተገባበሩ ዘገምተኝነት አንዳቸው ሌላቸውን ሲከሱ ቆይተዋል።

“የሰላም ሥምምነቱ ፈርሷል” የሚሉት አቶ አለማየሁ "ህወሓት ይኸን የሰላም ሥምምነት የማፍረስ እርምጃ ቢወስድም የፌድራል መንግሥቱም የሰላም ሥምምነቱን እያከበረ አልነበረም” ሲሉ ይተቻሉ። “ለሰላም ሥምምነቱ መደናቀፍ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካበረከቱት ወገኖች አንዱ የፌድራል መንግሥቱ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶቸ ቬለ ለዚህ ዘገባ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት እና የመንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች አገልግሎትን በኢሜይል፣ በቀጥታ ስልክ በመደወል እና በዋትስአፕ መልዕክት በመላክ አስተያየት ጠይቋል። የሁለቱም ተቋማት ኃላፊዎች ምላሽ አልሰጡም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ታደሰ ወረደን የሥልጣን ዘመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘማቸውን ተከትሎ ህወሓት ከጦርነቱ በፊት የተመረጠውን የክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ መልሷል። ምክር ቤቱ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የክልሉ መንግሥት ወደ ሥራ እንዲገቡ ወስኗል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ታደሰ ወረደ የህወሓትን አካሔድ ቢቃወሙም ያስቆሙት አይመስልም። “አሁን ነባሩን ምክር ቤታችንን መልሰናል። ነባሩን መንግሥታችንን መሥርተናል” የሚሉት አቶ ሚኬኤለ “በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን እንድንፈታ በግልጽ በውሳኔ አስተላልፈናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የፓርቲው ዋና ትኩረት ግን የትግራይ ክልል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሚኖረው “ተሳትፎ” አይደለም። “አሁን የእኛ ፍላጎት ሕዝባችን ከህልውና አደጋ እንዴት ይውጣ? ነው። ከህልውና አደጋ ለመውጣት የሚያስችለንን ዕቅድ ነው የምንይዘው” ሲሉ አቶ ሚኬኤለ አስረድተዋል።

የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ወታደራዊ አመራሮች እና ግለሰቦች የተመሠረተው የትግራይ የሰላም እና የለውጥ ምክር ቤት በፊናው ምርጫ እስኪካሔድ ድረስ “አቃፊ የሆነ ጊዜያዊ መንግሥት” እንዲቋቋም ጥረት መጀመሩን ገልጿል።

ሌላ ዙር ጦርነት ይቀሰቀሳል?

በትግራይ የፖለቲካ ልሒቃን መካከል የተፈጠረው መከፋፈል፣ ከፌድራል መንግሥት ጋር ያለው ልዩነት እና በቀጠናው የሚታየው ፈጣን የአሰላለፍ ለውጥ ሌላ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ሥጋት የፈጠረ ነው። በተለይ በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ባለው ውጥረት ምክንያት አቶ አለማየሁ ግጭት “የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ ነው” የሚል ሥጋት አላቸው።

“በሁለቱም ወገን እንቅስቃሴዎች አሉ። የፌድራል መንግሥት ሠራዊቱን ወደ ሰሜን ካስጠጋ ቆይቷል። በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት መንግሥትም ከሻዕቢያ ጋር መነጋገር፣ ከዚያም በላይ ሔደው ‘ጽምዶ' የሚባለውን የጋራ ጥምረት እንደመሠረቱ እየሰማን ነው” የሚሉት አቶ አለማየሁ “ሁለቱም ተፋጠው” እንደሚገኙ ያምናሉ።

ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተባለው የሲቪል ድርጅት በትግራይ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች “የተመለሱ ታጣቂዎች” እና በባሕላዊ ወርቅ በማውጣት ሥራ ላይ የተሠማሩትን ጨምሮ በግዳጅ ወጣቶች “በኃይል ወደ ውትድርና”  ለማስገባት “አፈሳ” እየተካሔደ እንደሚገኝ የሚጠቁም መረጃ እንደደረሰው ዋና ዳይሬክተሩ ተስፋለም በርሔ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል።

“በእኛ በኩል ለግጭት የሚያስችሉ በጣም በቂ የሆኑ ምክንያቶች አሉ። ሕዝባችን በፌድራል መንግሥት እየተሰቃየ ነው” የሚሉት አቶ ሚኬኤለ ግን “ግጭት ስለማንፈልገው፣ የጦርነት ጠባሳም አሳምረን ስለምናውቅ ይኸን ነገር በሰላማዊ መንገድ የምንፈታበትን መንገድ እያፈላለግን ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ግጭት አንፈልግም ማለት ግን የተቃጣብንን ወረራ ወይም ደግሞ የሚቃጣብንን ወረራ አንመክትም ማለት አይደለም” የሚሉት የህወሓት ቃል አቀባይ “ለመኖር ስንል፣ ህልውናችንን ለማረጋገጥ ስንል ለማስቀጠል ስንል የሚፈጸምብንን ወረራ ለመመከት ዝግጅት ማድረጋችን አይቀርም” ብለዋል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከግንቦት 5 ቀን 2017 ጀምሮ “ከፖለቲካ ፓርቲነት” በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰርዟል። ፓርቲው በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ እንዳይሳተፍ ያደረገውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እርምጃ አቶ አለማየሁት “ትልቁ ስህተት” ይሉታል።

የፌድራል መንግሥት የህወሓት ሕጋዊ ምዝገባ ስለተሰረዘ “አልደራደርም ሳይል፣ ህወሓትን ለድርድር ቢጋብዝ” እንደ አዲስ ሊቀሰቀስ የሚችል ግጭትን ለማስቀረት ዕድል እንደሚሰጥ አቶ አለማየሁ ያምናሉ።

ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ከተካሔደ ከአንድ ዓመት በኋላ የአቶ ጌታቸው ረዳ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይን ጨምሮ ሁሉም ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የትግራይ ምርጫ ማድረግ “የተሻለ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

አርታዒ አዜብ ታደሰ

 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele