ከኤኮኖሚዉ ዓለም፣ የግዙፉ አዉሮፕላን ማረፊያ ግንባታና ፈተናዎቹ
ረቡዕ፣ ጥር 6 2018
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባአጠገብ በቢሾፍቱ አካባቢ ለሚያስገነባዉ ግዙፍ አዉሮፕላን ማረፊያ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልገዉ አስታዉቋል።ከአፍሪቃ አቻ አይገኝለትም የተባለዉ አዉሮፕላን ማረፊያ ግንባታዉ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ይሁንና አዉሮፕላን ማረፈዉ በሚገነባበት አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ለችግር ይጋለጣሉ የሚለዉ ወቀሳና ለግንባታዉ የሚያስፈልገዉ 12.5 ቢሊዮን ዶላር ከየት ይገኛል የሚለዉ ጥያቄ ሁነኛ መልስ ያገኙ አይመስልም።የዛሬዉ ከኤኮኖሚዉ ዓለም ዝግጅት የአዉሮፕላን ማረፊያዉን ግባታና የተደቀኑበትን ችግሮች ያወሳል።
በ1954 ዓ.ም. የተመሰረተውን የቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያን እንደመተላለፊ በመጠቀም አንድ ብሎ የአቪየሽን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው አየርመንገዱ፤ ስራውን ስጀምር በዓመት 250 ሺህ ሰዎች ብቻ የማስተናገድ አቅም ነበረው፡፡ አሁን ላይ ግን በዓመት 250 ሚሊየን ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ላይ መድረሱ የተነገረለት በአዲስ አበባው ቦሌ ዓለማቀፍ አየርማረፊያ የሚተላለፉ፤ እያደጉ ከመጡ የደንበኞች ቁጥር አኳያ በ2020 ዓ.ም. ከአቅሙም ይሻገራል፡፡
የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እድገት መወሰን ሌላ አውሮፕላን ማረፊያ ፍላጋ
ይህ የአውሮፕላን ማረፊያው ወደፊት ከዚህ በኋላ የመስፋት አቅሙ ውስን መሆን ለአዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ቦታ መረጣ አየር መንገዱን ወደ ሌላ አማራጭ ፍለጋ አስገብቶታል፡፡ አየር መንገዱ እንደሚለው ከሰፊ የቦታ መረጣ በኋላ በብዙ ቴክንካዊ ምክንያቶች አሁን ለአዲሱ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያነት የተመረጠው የቢሾፍቱ አቅራቢያው አቡሴራ ቀበሌ ተመራጭ ስፍራ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደሚሉት በ3 ሺህ 900 ሄክታር ቦታ ላይ የሚያርፈው አዲሱ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በሙሉ አቅሙ ሲጠናቀቅ 110 ሚሊየን ደንበኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህም አሁን አገልግሎት ላይ ከሚገኘው ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር ስቀናጅ አየርመንገዱ አቅሙን በዓመት 135 ሚሊየን ደንበኞችን ወደ ማስተናገድ እንዲሸጋገር ይረዳዋል እንደማለት ነው፡፡ “በአውሮፕላኖች ብዛት እና እያደገ ከመጣው የመንገደኞች ብዛት አኳያ ማስፋፊያ እየተደረገለት የመጣው የቦሌ አየርማረፊያ ከዚህ በኋላ መስፋት የማይችል በመሆኑ እያደገ የመጣውን የደንበኞች እና አውሮፕላኖች ቁጥር ለማስተናገድ አዲስ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ አስልጓል” የሚሉት የኢትዮጵያ አየርመንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ ቢሾፍቱ ላይ ስራው የተጀመረው አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የተጀመረው በአየርመንገዱ ቀጣይ ስኬት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያለው በመሆኑ ነው ይላሉ።
ለኢትዮጵያ ሎጂስቲክ «የሰማይ ላይ መርከቦች”
ባሳለፍነው ቅዳሜ የቢሾፍቱ ዓለማቀፍ አየርማረፊያ ግንባታ በተጀመረበት መርሃግብር ላይ ተገኝተው የመሰረተድንጋይም ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ አየርማሪያውን 130 ሚሊየን ህዝብ የሚመጥን ብለውታል፡፡ “በሰማይ ላይ ለሚበሩ መርከቦች 130 ሚሊየን ህዝብ የሚመጥን ወደብ በዚህ ስፍራ አስጀምረናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ 700 ሄክታር ግድም ከሚሰፋው ከቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አኳያ አዲሱ ግንባታው የተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 3900፤ አጠቃላይ የአውሮፕላን ማረፊያ ከባቢን ስያካቲት ደግሞ 5000 ሄክታር ግድብ እጅግ ሰፊ ልዩነት ያለው እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ስብራት ያሉት የሎጂስቲክ ችግሮችን ለመጠገን እጅጉን አስፈላጊ ስራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ከነባሩ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር ይተሳሰራል
አዲሱ የቢሾፍ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከቦሌው ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የ38 ኪ.ሜ. ርቀት እንዳለው የተነገረ ሲሆን ሁለቱን የአውሮፕላን መሰረተልማት ለማገናኘት ዘመናዊ የፍጥነት መንገዶች እና የፈጣን ባቡር መሰረተልማት እንደሚዘረጉለትም ተነግሯል፡፡ “ከዚህ ወደ ቦሌ የሚሄደው 12 መኪና የሚያስተናግድ ቸጣን መንገድ እንገነባለን” ያሉት ዐቢይ፤ በተጨማሪም በሰዓት ከ120 እስከ 200 ኪሌሜትር የሚምዘገዘግ የፈጣን ዘመናዊ ባቡር መሰረተ ልማትም እንደሚዘረጋ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ግንባታም በርካታ አገርበቀል ኮንትራክተሮች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በሙሉ አቅሙ 110 ሚሊየን ደንበኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅም እንዳለው የተነገረለት አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ግንባታው የሚከወነው በሁለት ምዕራፎች ነው፡፡ 60 ሚሊየን ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው የአውሮፕላን ማረፊያው የመጀመሪያ ምዕራፍ 12.5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚደረግበት ሲሆን፤ በውስጡም አንድ ዘመናዊ ትልቅ እና አንድ መለስተኛ ተርሚናሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ሁለት በተጓዳኝ የሚሰሩ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች፣ 180 አውሮፕላኖችን በአንዴ የማቆም አቅም፣ 350 ማረፊያ ክፍሎች ያሉት ሆቴል፣ በዓመት 1.5 ሚሊየን ቶን ማስተናገድ የሚችል የካርጎ ተርሚናል እና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከላት ይኖሩታል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደሚሉት አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያን ለመገንባት ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት ሰፊ ያሉት ጥናትም ተደርጓል፡፡ “በሚመጡት ዓመታት በአዲስ አበባ በኩል የሚመጡ የመንገደኞች ቁጥር ምንያህል እንደሚጨምር ስንት አውሮፕላኖች እንደሚመጡና ያንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ፤ 12.5 ቢሊየን ዶላር ብናወጣ በዚህ ላይ እዳውን መክፈል ይቻላል የሚለውን የአዋጭነት ትናት ተሰርቶ ተረጋግጧል” ብለዋል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያውን ለምን አሁን?
አውሮፕላን ማረፊያውን አሁን ማስጀመር ያስፈለገበትም ምክንያት “የኢትዮጵያ አየርመንገድ በዓመት ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ አዳዲስ ደንበኞችን እያፈራ የሚመጣ ከመሆኑ የተነሻ በመሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ቦሌ አየርማረፊያ ተጨማሪ ሰው የማስተናገድ አቅም ስለሚያጣ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሰረተልማቶች እቅድና ልማት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ተስፋዬ ደግሞ አየርመንገዱ ይህን አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ እቅድን ከነደፈ ቆየት ብሏል ይላሉ፡፡ “ፕሮጀክቱን ካቀድን የጎርጎሳውያን 2014 ወዲህ ወደ አስር ዓመታት አልፎታል” የሚሉት አቶ አብራሃም፤ ለዚህም ደግሞ አዲስ አበባ ያለው ቦሌ ዓለማቀፍ አየርማረፊያ እየሰጠ ያለው አገልግሎት አየመንገዱ እየሰጠ ካለው አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን ባለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡ ከተማ የተከበበው ቦሉ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያም ተደርጎለት ደንበኞችን ያመስተናገድ የመጨረሻው ዓመታዊ አቅሙ 25 ሚሊየን ብቻ ነው የሚሉት አቶ አብርሃም፤ ወደፊት ለአየርመንገዱ ዓለማቀፋዊ ውስንነት የሚፈጥር በመሆኑ አማራጭ መፈለግ ግድም ነበር ባይ ናቸው፡፡
አቡሴራ ለምን ተመረጠ?
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሰረተልማቶች እቅድና ልማት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ተስፋዬ አየርማረፊያው አሁን ለግዙፍ የአውሮፕላን መሰረተ ልማት የመረጠው የቢሾፍቱ አቅራቢያው አቡሴራ ቀበሌ በብዙ ምክንያቶች ተመራጭም ነው ይላሉ፡፡ “አማካሪዎችን ቀጥረን በቦታ መረጣው ላይ በባለፈፉት 10 ዓመታት ጥናት ስናደርግ ነበር” ያሉት አቶ አብርሃም፤ አቡሴራ ከአዲስ አበባ አኳያ 400 ሜትር ዝቅተኛ አልቲትዩድ ላይ መገኘቱ አውሮፕላኖች በሙሉ አቅማቸው እንዲበሩ ከማስቻሉ ባሻገር ነዳጅ ፍጆታን ይቀንሳል ይላሉ፡፡ ሰፊ ሜዳማ አከባቢው ለወደፊትም ማስፋፊያ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር በማስገንዘብ፣ ከአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያው ጋር በተመጋጋቢነት ለመስራትም አመቺ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በስፍራው የነበሩ አርሶአደሮችን ማንሳት
አቶ አብራሃም አክለውም፤ የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ላይ ከመገባቱ በፊትም በትኩረት ላለፈው አንድ ዓመት የተሰራበት ጉዳይ አርሶአደሮቹን ከስፍራ ማንሳት ነው ይላሉ፡፡ “የግንባታ ልማቱን ከመጀመራችን በፊት በዚህ የነበሩ ነዋሪዎችን አስፍረን ተገቢውን በቀጣይነት ህይወታቸውን የሚመሩበትን አስቻይ ሁኔታ ፈጥረን ነው” በማለትም በቦታው ላይ የነበሩ 2 ሺህ 500 ግድብ ገበሬዎች ዛሬ ላይ ወደ አዲሱ ቤታቸው በመግባት አዲስ ምርታቸውንም ወደ ማምረት መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ላይ በቀጣይነት መስራት የአየርመንገዱ ኃላፊነት እንደሆነም እንዲሁ አመልክተዋል፡፡
አሁን ወደ ስራ የተገባው የቢሾፍቱ አየርማረፊያ በሚቀጥለው አንድ ዓመት የመሬት ድልዳሎ ስራው ተጠናቆ ወደ ቀጣይ የግንባታ ምዕራፍ እንደሚሸጋገርም ታምኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ አየርመንገዱ 610 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላርን ከካዝናው መድቦለታል፡፡ ለዚህም 3 የስራ ተቋራጮች ተመርጠው 400 ግድም ማሽኖች ወደ ስራ ተሰማርተዋል፡፡ ጥልቅ የአውሮፕላን ማረፊያው ዲዛይንም በተመረጡ ዓለማቀፍ አማካሪዎች አማካኝነት እስከ መጪው መጋቢት ወር ለኢትዮጵያ አየርመንገድ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ 2030 ማለትም ልክ የዛሬ አራት ዓመት 60 ሚሊየን መንገደኞችን የሚያስተናግደው የአውሮፕላን ማረፊያው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
አሳሳቢው የፋይናንስ ምንጭ ፍለጋ
በአውሮፕላን ማረፊያው መሰረተልማት ግንባታ ሂደት የሚፈለው 12.5 የመጀመሪያው ምዕራፍ ወጪ እንኳ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም፡፡ 30 በመቶውን የግንባታ ወጪ አዘጋጅቻለሁ ያለው የኢትዮጵያ አየርመንገድ 70 በመቶ ያህሉን ካለማቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ይጠባበቃል፡፡ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለዚህም ተገቢውን ዝግጅት አድርገናል ይላሉ፡፡ “እስካሁን ድረስ ፋናንሱን ለማግኘት የአዋጭነት ጥናቱን ለብዙ አበዳሪ ተቋማት አቅርበናል” በማለትም አዎንታዊ ምላሽን ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ “በርግጥ ሁሉም ዬራሳቸውን ጥናት ማካሄድ አለባቸው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ገንዘቡን ለማግኘት ያለው ተስፋ ጠንካራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሰረተልማቶችእቅድና ልማት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ተስፋዬም አውሮፕላን ማረፊያው የሚገነባበትን ፋይናንስ እስከሚቀጥለው ዓመት አስተማማኝ ለማድረግ ተስፋዎች አሉ ባይ ናቸው፡፡ “የፋይናንስ ጉዳዩን እስከ መጪው አንድ ዓመት አጠናቀን፤ የተቀረውን ወደማሰባሰብ እንገባለን ብለን እየሰራን ነው” በማለትም የአፍሪካ ልማት ባንክ ከዚህ አኳያ ሃላፊቱን ወስዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በተለያዩ መድረኮች በተደረረገው ገለጻም ከተለያዩ አገራት ማለትም ከማአከለኛው ምስራቅ፣ ከቻይና፣ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የተለያዩ አበዳሪ ድርጅቶች ለፕሮጀክቱ ገንዘብ ለማበደር መጠኑንም እየገለጹ ነው በማለት የኩባንያዎቹን ስምና ቃል የተገባው የገንዘቡን መጠን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
አስተያየታቸው ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የገነዘብ አስዳደር ባለሙያ ዶ/ር አብዱልመናን መሀመድ ግን ስለዚህ ጉዳይ አንድ አሳሳቢ ነጥብ ያነሳሉ፡፡ “ከአበዳሪዎች ይገኛል የተባለው የገንዘብ መጠን በወቅቱ ባይገኝ፤ ፕሮጀክት በጣም ይጓተታል” በማለትም፤ ይህ ደግሞ የፕሮጀክቱን ዋጋ እንደሚያንረው አስረድተዋል፡፡ በርግት የኢትዮጵያ አየርመንገድ መልካም ስም ያለው ኩባንያ ነው የሚሉት አቶ አብዱልመናን፤ የሚፈለገው የገንዘብ መጠን እጅግ ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በጥንቃቄ ካልተመራ ቀውስ ሊያመጣ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡
አበዳሪ ቢጠፋ ፕሮጀክቱን ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የምትወጣው ነውን?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፕሮጀክቱን ግንባታ ባስጀመሩበት በባለፈው ቅዳሜ ጥር 02 ቀን 2018 ዓ.ም. ንግግራቸው “አበዳሪዎች እግራቸውን ብጎትቱ ኢትዮጵያ ግንባታውን በራሷ አቅም ትወጣለች” ብለዋል፡፡ “ዛሬ 2018 በገናና ጥምቀት መሃል ያለና የማይረሳ ጊዜ ነው፡፡ በፈረንጆች 2030 ብዙዎቻችሁ በተገኛችሁበት የመጀመሪያውን ምዕራፍ በዚህ ቦታ እናስመርቃለን፡፡ በዚህ ጉዳይ የምተባበሩ ኩባንያዎች ጊዜ እንዳያልፍባችሁ፡፡ እኛ እገግራችሁን የምትጎትቱ ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ህዳሴን የገነባች አገር ስለሆነች ይህንንም ብቻዋን ትደግማዋለች” በማለት በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አብዱልመናን መሀመድ እንዳሉት ግን “በአገር ውስጥ አቅም ይሄ የሚከብድ ይመስለኛል” ይላሉ፡፡
በዓለማቀፍ ብርቱ ውድድር ላይ የሚገኘው አየርመንገዱ እንደሌላው የአገር ውስጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሊታይ የማይገባውና የተለየ ጥንቃቄ የሚፈልግም ስራ ነው ብለዋል፡፡ የተጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አበዳሪዎች የአገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት ሁናቴን ጨምሮ በርካታ የአዋጭነት ጉዳዮችን ከግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ እጃቸውን ሊዘገሩ እንደማይቸሉም በመጠቆም ሂደቱ ቀላል እንዳልሆንም አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ