1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢሕአፓ የጠራው ሰልፍ እና ያሰማው ተቃውሞ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 1 2018

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በመላው አገሪቱ ዐሥር ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን ዐሳወቀ ፡፡ ኢሕአፓ ዓርብ ሚያዚያ 30 ቀንä 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ መቐለ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ አሶሳ፣ አዳማ፣ አምቦ፣ ድሬዳዋ እና ሀረር ከተሞች በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ዜጎች እንዲታደሙ ሲል በመግለጫው ጠይቋልም፡፡

https://p.dw.com/p/5BvTm
«ምርጫው የይስሙላ እንዲሆን አንፈልግም» ኢሕአፓ
«ምርጫው የይስሙላ እንዲሆን አንፈልግም» ኢሕአፓምስል፦ Megabe Beluiey Abrham Haimanot/DW

«ለሰላማዊ ሰልፉ የማስፈቀድ ሂደት ጀምረናል» ኢሕአፓ

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በመላው አገሪቱ ዐሥር ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን ዐሳወቀ ፡፡ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ለኢትዮጵያ) በተሰኘ የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት ስር ዘንድሮ ለሚካሄድ ምርጫ ከሚፎካከሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢሕአፓ የተቃውሞ ሰልፍ በጠራበት መግለጫው፦ በምርጫው ሂደት ላይም ጥያቄ አንስቷል ።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በመላው አገሪቱ በሚገኙ ዐሥር ከተሞች ለሚያዚያ 30 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ በጠራበት የትናንት (ረቡዕ) መግለጫው፤ የሰልፉ አላማ "የንጹሃን ጭፍጨፋ እንዲቆም”፣ የዜጎችን ሕይወት አመሰቃቅሏል ያለው የኑሮ ውድነቱ በአስቸኳይ ርምጃዎች እንዲገታ፣ "ማንነት ተኮር” ያለው የንጹሃን ዜጎችን እስር፣  ወከባዎችና ግድያዎች እንዲቆሙ ነው ብሏል፡፡ ኢህአፓ በመግለጫው በሰልፉ የዜጎች መፈናቀል፣ ሙስና፣ አድላዊነትና አግላይነት እንዲወገዱ ጥሪ ይቀርባልም ነው ያለው፡፡ በምርጫ ሂደቱ በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ስር የምንቀሳቀሰው ኢሕአፓ ዓርብ ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ መቐለ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ አሶሳ፣ አዳማ፣ አምቦ፣ ድሬዳዋ እና ሀረር ከተሞች በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ዜጎች እንዲታደሙ ሲል በዚሁ መግለጫው ጠይቋልም፡፡

"ለሰላማዊ ሰልፉ የማስፈቀድ ሂደት ጀምረናል”

በመግለጫው ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየቶችን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የፓርቲው ሊቀመንበር መጋበ-ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፤ ሰልፍ ለማካሄድ አዲሱ የምርጫ ቦርድ የቃልኪዳን ሰነድ ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን ለማስፈቀድ ስለሚያስገድድ በዚያው ሂደቱን ስለመጀመራቸው አስረድተዋል፡፡ "በዚያው መሰረት ሕጉን ተከትለን ሰልፉን በምናካሂድባቸው 10ሩም ከተሞች ጥበቃዎች እንዲመደቡና መንግስትም ግዴታውን እንዲወጣ እየተየቅን እንገኛለን” በማለትም እስካሁን በትናንትናው እለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርቻ ቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡ የድጋፍ ሰልፍ እንደሚፈቀድ ሁሉ የተቃውሞ ሰልፍም መፈቀድ ኖርበታል ሲሉም አስተያየታቸውን የገለጹት ፖለቲከኛው፤ "ምርጫው የይስሙላ ምርጫ እንዳይሆን ተግዳሮት የሆኑ ነገሮችን ሕዝቡ ተቃውሞ ምርጫው ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲያልፍ በማሰብ የተጠራ ሰላማዊ ሰልፍ ነው” ብለዋልም፡፡

"ምርጫው የይስሙላ እንዲሆን አንፈልግም”

ኢሕአፓ በመግለጫው "በምርጫው ተሳትፎ በማድረግ” ኢትዮጵያን ተደቅኖባታል ካለው "የመፍረስ አደጋ” ለማዳን የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማበርከት ሙሉ ዝግጅት ቢኖርም፤ ገዥው ፓርቲ ፍላጎቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ አይደለም ሲል ትችቱን ሰንዝሮበታልም። "ጦርነት፣ መፈናቀል፣ የንጹሀን ግድያ እና እስር የኢትዮጵያመልኮች በሆኑበት የሚደረግ ምርጫ ትርጉም አይኖረውም” ሲል ወቅሷልም፡፡ በትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ በርካታ ስፍራዎች ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች የሉም ሲል በመግለጫው ያብራራው ፓርቲው፤ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ማድረግ አደገኛ አንድምታ ያለው ነው ሲል ጠቅሷልም፡፡

ኢህአፓ፦ «ሕጉን ተከትለን ሰልፉን በምናካሂድባቸው 10ሩም ከተሞች ጥበቃዎች እንዲመደቡና መንግስትም ግዴታውን እንዲወጣ እየተየቅን እንገኛለን» ብሏል
ኢህአፓ፦ «ሕጉን ተከትለን ሰልፉን በምናካሂድባቸው 10ሩም ከተሞች ጥበቃዎች እንዲመደቡና መንግስትም ግዴታውን እንዲወጣ እየተየቅን እንገኛለን» ብሏልምስል፦ Seyoum Getu Demissie/DW

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ኢሕአፓ ይፈልጋል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ለዚህም ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር መንቀሳቀሱን ጠቅሰው፤ መግለጫው ማስተላለፍ የፈለገው መልእክትም ይህ ነው ብለዋል፡፡ "በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ስፍራዎች ጭምር በርካታ እጩ በማቅረብ ሰፊ ዝግጅት አድርገናል መሰረታችንም ጠንካራ መሆኑን አሳይተንበታል” በማለት ነገር ግን ምርጫው የይስሙላ ሳይሆን እውነተኛ ምርጫ እንዲሆን ፍላጎታቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ "የሚዲያ ነጻነት፣ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ የፀጥታው ሁኔታ እንዲረግብ ቁርጠኛ የመደራደር ዝግጁነት ያስፈልጋል” በማለት በምርጫው ላይ የዓለማቀፍ ታዛቢዎች እንዲገኙም ጭምር ጥሪ መቅረቡን አንስተዋል፡፡

ኢሕአፓ ከምርጫው እራሱን እያገለለ ነውን?

የኢሕአፓ መሪው ፓርቲያቸው ላይ በተናጥል ጫናዎች እንደሚደረጉም ሲያስረዱ፤ "ባሁን ሰዓት እንኳ በድሬዳዋ የሚገኘው የኢህአፓ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊና የድሬዳዋ ምክር ቤት እጩ ታፍኖ ነው ያለው” በማለት እንዲህ አይነት እስረኞች ባልተፈቱበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ፍትህአዊ አይሆንም ብለዋል፡፡

"ከምርጫው እየወጣችሁ ነው ወይ” በሚል ከዶይቼ ቬለ ለቀረበላቸው ትያቄ መልስ ሲሰጡም "ኢህአፓ አስቻይ ሁኔታዎች የማይፈጠሩ ከሆነ የተለያዩ ‘ጠበቅ ያሉ' ውሳኔዎችን መወሰኑ አይቀርም” በማለት ውሳኔውም ለማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦ የሚታይ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመግለጫው ለመንግስት በቀረበው ጥሪ ላይ ምላሽ ካልተገኘ "ጠንካራ” ያሉት ውሳኔ እንደሚተላለፍም ገልጸዋል፡፡ ዶይቼ ቬለ በዚህ ዘገባ በመግለጫው ትችት ከተሰነዘረበት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምላሽና አስተያየት ለማካተት ጥረት አድርጓል፡፡ ለጥያቄያችን አጭር ምላሽ የሰጡን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ግን "እንደ ፓርቲ ተወያይተንበት ምላሽ የምንሰጥ ይሆናል” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ ከአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን)፣ እናት ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጋር ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት-ለኢትዮጵያ የሚል ቅንጅት ፈጥረው ለ2018ቱ የኢትዮጵያ ምርጫ በቅርቡ ማኒፌስቶአቸውን በይፋ ካስተዋወቁ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ