ነዳጅን ከመደበኛ ዋጋ የመሸጥ ፈተና
ዓርብ፣ የካቲት 13 2018
በኢትዮጵያ ነዳጅን መንግስት ከተመነው መደበኛ ዋጋ ውጭ የሚሸጡ ማደያዎች በእለት ተእለት ስራዎቻቸው ላይ ፈተና መደቀናቸውን አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ይገልጻሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በዚህ ከተመን በላይ ክፍያ በሚጠየቅባቸው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ ማደያዎች ጋር በሚፈጠር ንትርክ አንዳንዴ ስራቸው ይስተጓጎላልም፡፡
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የተሽከርካሪ ባለንብረት ነዳጅን መንግስት ካወጣው የዋጋ ተመን ውጭ በሚጠይቁ ማደያዎች ስራቸው ሁሌም እንደሚፈተን አስረድተዋል፡፡ በባንክ እዳ በገዙት ከባድ ተሽከርካሪ የቤተሰባቸውን ህይወት እንደሚመሩ የሚገልጹት አስተያየት ሰጪው የተሽከርካሪ ባለንብረት በዚሁ ሳምንት ውስጥ አጋጥሞናል ብለው በሰጡት አስተያየታቸው፤ ከህጋዊ ተመን ውጪ ሌላ የራሳቸው ተመን በሚጠይቁ “ህገወጥ” ባሏቸው የነዳጅ ማደያዎች መሰላቸታቸውን ገልጸዋል፡፡ “አሁን ከጅቡቲ ወደ ኮይሻ ግድብ ደረቅ ጭነት ጭነን እየመጣን ድሬዳዋ ላይ ነዳጅ ቀድተን በ140 ብር ሂሳብ ካልሆነ ክፍያ አንቀበላችሁም ብለውን የማደያ ሰራተኞች አስቁመውናል” ሲሉም አስተያየት ሰጪው አመልክተዋል፡፡
ጉዳዩ ደጋግሞ በተለያዩ አከባቢዎች የሚያጋጥማቸው መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪው፤ በ129 ብር ግድም እንዲሸጥ በመንግስት ዋጋ የተተመነለት የአንድ ሊትር ናፍጣ ዋጋ በ140 ብር ሂሳብ እንዲከፈል በመጠየቃቸው ከስራቸው ተስተጓጉለው ሙግት ላይ መሆናቸውን ነው ያመለከቱትም፡፡ “ከትናንት ጀምሮ በ 140 ሂሳብ ካልከፈላችሁ ብለው ለአከባቢው የድሬዳዋ ፖሊስ ለማመልከት ቆመናል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ በዚህም የስራ ሰዓታቸው በአልባሌ ነገር እንደሚቃጠል ነው የገለጹት፡፡
ዘላቂ መፍትሄውስ ከየት ይምጣ? እንዴትስ እናመልክት?
መሰል ከህጋዊ ተመን በላይ ዋጋ በነዳጅ ችርቻሮ ላይ የሚጠየቁት በአንድ አከባቢ ብቻ ሳይሆን በሚንቀሳቀሱበት በተለያዩ አከባቢዎች እንደሆነም አክለው ያስረዱት አስተያየት ሰጪው የተሽከርካሪ ባለንበረት የመፍትሄ ያለ ብለው የሚያመለክቱበትና ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጣቸውም የመንግስት አካል የትኛው እንደሆነ እንደማያውቁትም ጠቁመዋል፡፡ “ይህ አቤቱታ ራሱ ማንን ነው የሚመለከተው፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው ወይስ ፖሊስ ነው” የሚለውም ግራ እንደገባቸው ያመለከቱት አስተያየት ሰጪው፤ ባለማደያዎቹ “በኦንላይን” በቴሌብር ስያስከፍሉም ትክክለኛውን ቀዱትን የነዳጅ የሊትር መጠንና የቆጠረውን ገንዘብ መጠን ማስቀመጥ ላይም ክፍተት እንደሚታይባቸው በመግለጽ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ከህጋዊ ተመን በላይ መጠየቁ የነዳጅ እጥረትንም ያስከትላል
በመንግስት ከሚቀመጠው ህጋዊ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ተመን ውጭ በሚጠየቁ ክፍያዎች አብዛኛውን ጊዜ በየማደያዎች ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንደሚከሰት ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው አሽከርካሪና የተሽከርካሪ ባለንብረት፤ ችግሩ አንድ ቦታ መገታት እንዳለበት ግን ያምናሉ፡፡ “ባለማደያዎች ትንሽ መሸት ካለ ይዘጋሉ፤ ሆን ብለውም ያጉላላሉ” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ እንደ አገሪቱ በሰፊው በተለያዩ አቅጣጫዎች በሚታይ ባሉት በዚህ ድርጊት ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ስራቸውን ያለሃሳብ መከወን ብርቱ ፈተና እንደጋረጠባቸውም በአስተያየታቸው አመልክተዋል፡፡
የመንግስት የመፍትሄ አቅጣጫ
ዶይቼ ቬለ አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶቹ በማደያዎች ስለሚጠየቁት ከህጋዊ ተመን በላይ የሆነው ዋጋን በተመለከተ መንግስት ሊከውን ስለሚገባው ስራና የክፍተቱ መንስኤ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ለኢትዮጵያ ነዳጅ ባለስልጣን ዋና ስራ አስከያጅ ዶ/ር ደስታው መኳንንት የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ በመደወል ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡
ከሳምንታት በፊት ከነዳጅ ጋር ተያይዞ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ስለሚስተዋለው አለመረጋጋት ከኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ችግሩ በዋናነት የሚመነጨው ያለአግባብ የማይገባቸውን ትርፍ ለማጋበዝ በሚጥሩ በነዳጅ ሽያጭ ዘርፍ በተሰማሩ ነጋዴዎች መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱም ኢትዮጵያ ነዳጅን የምትሸጥበት የችርቻሮ ዋጋ ከጎረቤት አገራት አኳያ አነስተኛ መሆኑንም ጠቁመው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ነዳጅ በባቡር ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንደ አንዱ እልባት ተደርጎ እንደ መፍትሄ መቀመጡን መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
ያንን ተከትሎ በተያዘው የካቲት ወር መጀመሪያነዳጅን በኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ስራ መጀመሩን የኢትዮ-ጂቡቱ ባቡር መስመር ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ