1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አሜሪካና እሥራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት የፈጠረው የነዳጅና ጋዝ እጥረት

ገበያው ንጉሤ
ዓርብ፣ መጋቢት 4 2018

የመካከለኛ ምስራቅ ጦርነት አውሮፓን ዋጋ የሚያስከፍለው የነዳጅ ዘይትና ጋዝ እጥረትና የዋጋ ጭማሬ ብቻ አይደለም።ይልቁንም በዩክሬን ምክንያት በተዘዋዋሪ ህብረቱን የምትታገለውን ሩሲያን እያጎለበተና በዩክሬን እርዳታ ላይ ተጽኖ እየፈጠረ መሆኑም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። የካውንስሉ ፕሬዝዳንት እስካሁን በዚህ ጦርነት አሸናፊ ሆና የወጣችው ሩሲያ ናት ብለዋል

https://p.dw.com/p/5ALqB
በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን የተካሄደ የአየር ድብደባ
በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን የተካሄደ የአየር ድብደባምስል፦ Fatemeh Bahrami/Anadolu/picture alliance

አሜሪካና እሥራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት የፈጠረው የነዳጅና ጋዝ እጥረት

አስራ አራተኛ ቀኑን የያዘው አሜሪካና እስራኤልበኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነትና ኢራን በአጸፋው በእስራኤልና  የባህር ሰላጤ አገሮች ላይ የምትወሰደው እርምጃ፤ በአካባቢው እያደረስ ካለው ውድመትና የበርካታ ሰዎች ህይወት ህልፈት ባለፈ፤ ዓለም አቀፍ የደህንነት ስጋትና የኢኮኖሚ ቀውስ የፈጠረ ሆኖ ቀጥሏል።  እስካሁን በእስራኤልና አሜሪካ የሚሳይልና ቦምብ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ ቴህራንን ጨምሮ ዋና ዋናዎቹ የኢራን ከተሞችና ተቋማት ወድመዋል፤ መሰረታዊ ልማቶችም ፈርሰዋል።  

ኢራን በበኩሏ ወደ እስራኤል፣ ሳኡዲ አረቢያና የገልፍ ባህረሰላጤ አገሮች በምትላከቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖችና ሚሳይሎች በርካቶች ሞተዋል፤ ቁስለኛ ሁነዋል። በእነዚሁ አገሮች ባሉ የነዳጅና ጋዝ ጉድጉዶችና ማጣሪይዎች ላይ የደረሰው ጉዳትም የነዳጅና ጋዝ ምርቱን በእጅጉ የቀነሰው ሲሆን፤

ከሁሉም በላይ ግን ነዳጅ ዘይትና ጋዝን  ጨመሮ ዋና የአለም ንግድ መተላለፊያ መስመር የሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ በመዘጋቱ አለም በሙሉ የነዳጅ ዘይትና ጋዝ እጥረት አጋጥሞታል። በአሁኑ ወቅትም የነዳጅ ዘይት ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ በበርሜል ከአንድ መቶ ዶላር በላይ እንደዘለቀ የሚነገር ሲሆን፤ ጦርነቱ ከተራዘመ በበርሚል እስከ አንድ መቶ ሀምሳ ዶላርና  ከዚያም በላይ   ሊደርስ እንደሚችል በሰፊው መነገር ይዟል።

የነዳጅና ጋዝ እጥረቱ ዋና ምክንያት

በኢራን፤ የተባበሩት አረብ ኤሚሪቶችና ኦማን መካከል የሚገኘው  የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አንድ አምስተኛው የአለም ነዳጅ ዘይትና ጋዝ፤ ማዳበሪያና ሌሎች ሸቀጠጦች የሚተላለፍበት ዋነኛ የእስያና አውሮፓ የንግድ መተላለፊያ መስመር ነው።  ኢራን በዚህ መስመር የሚያልፍ ማንኛውም መርከብ ለጥቃት የተጋለጠ መሆኑን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን በተወሰኑ መክርቦች ላይም ጥቃት የደረሰ  በመሆኑ በአሁኑ ውቅት መስመሩ  ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንደተዘጋ ነው የሚታወቀው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን መተላለፊያ መስመሩን የማወክ አቅም በማዳከም  መስመሩን እንደሚያስከፍቱ ቢናገሩም እስካሁን ግን ኢራንን በአካባቢው ጥቃት ከማድረስ እንዳላገዷት ነው የሚገለጸው። እውቁ አሜሪካዊው የኢኮኖሚ ባለሙያ ፕሮፌሰር ጀፍሬይ ዴቪድ ሳክስ እንደሚሉት የመተላለፊያ መስመሩን ከጥቃት መከላከልና ክፍት ማድረግ አስቸጋሪ ነው።

“ እኔ እንደሚገባኝ አሜሪካ የሆርሙዝ መተላለፊያን ክፍት አድርጋ ማቆየት አትችልም። ይህ በወታደራዊም ሆነ በሌላ ዘዴ የሚቻል አይደለም  የእስራኤልና አሜሪካ ቦምቦች ይህን ማድረግ አይችሉም። አሜሪካም ሆነች እስራኤል  ወታደር በአካባቢው ማሰማራትም  አይችሉም ብለዋል።  ፕሮፌሰር ጀፍሬይ ጦርነቱ ከተራዘመም ሊከሰቱ ይችላሉ ያሉዋቸውንም አመላክተዋል ። “ አንደኛ የሆርሙዝ መስመር እንደተዘጋ ይቆያል፤ ሁለተኛ በገልፍ የሚገኙ የንዳጅ ዘይት ጉድጉዶች ማጣሪያዎችና ወደቦችም ሊወድሙ ይችላሉ” በማለት ይህ ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ አለማቀፍ ቀውስ ሊከተል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የአውሮፓ ተጋላጭነት

አውሮፓ በተለይ የጋዝና ነዳጅ ግብይቱን ከሩሲያና  ዩክሬን ጦርነት በኋላ በሳኡዲ አረቢያና የገልፍ አገሮች ላይ ጥገኛ ማድረጉ፤ አሁን  በጦርነቱ ምክኒያት ለተከሰተውየነዳጅ ዘየትና ጋዝ እጥረትና የዋጋ መናር ተጋላጭና ተጠቂ እንዳደረገው ነው የሚታመነው። የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ኡርሱላ ቮንዴርለየን በመጀመሪያዎቹ  አስር የጦርነቱ ቀናት ብቻ አውሮፓ ለነዳጅ ዘይት ያወጣውን ሲገልጹ፤ “ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የጋዝ ዋጋ በ15 ክመቶ የነዳጅ ዘይት 27 ክመቶ ጨምሯል። የመጀመሪያዎቹ አስር የጦርነት ቀናት ብቻ  የአውሮፓ ታክስ ከፋዮች ለነዳጅ ዘይት ግዥ ተጨማሪ 3ቢልዮን ኢሮ አውጥተዋል” በማለት የጦርነቱ ጦስ በውሮፓ ግብር ከፋይ ህዝብ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ግልጽ አድርገዋል።፡

በጦርነቱ እያተረፈ ያለው ማነው?

የመካከለኛ ምስራቅ ጦርነት አውሮፓን ዋጋ እያስከፈለው ያለው በተከስተው የነዳጅ ዘይትና ጋዝ እጥረትና የዋጋ ጭማሬ፣ ብቻ አይድለም። ይልቁንም በዩክሬን ምክኒያት በተዘዋዋሪም ቢሆን ህብረቱን እየተፋለመች ያለችውን ሩሲያን እያጎለበተና ለዩክሬን በሚሰጠው እርዳታ ላይ ተጽኖ እየፈጠረ መሆኑ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ሁኗል።   የካውንስሉ ፕሬዝዳንት ሚስተር አንቶኒዮ ኮስታ ይህን ሲያስረዱ፤ “እስካሁን ድረስ በዚህ ጦርነት አሸናፊ ሆና የወጣቸው ሩሲያ ናት። ከአለም የነዳጅ ዘትና ጋዝ ዋጋ ጭማሬ ጦርነቱንን ለማስኬድ የሚያስችል ተጨማሪ ገቢ አስገኝቶላታል። ወደ መካከለኛው ምስራቅ በሚላከው  የጦር መሳሪያ ምክኒያት ለዩክሬን የሚደርሰው መሳሪያ እንዲቀንስ ሁኗል። የዓለም ትኩረትም በመካከለኛው ምስራቅ በመሆኑ የዩክሬን ጉዳይ የሚገባውን ያህል ትኩረት እያገኘ አይደለም” በማለት የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በህብረቱና አባል አገራቱ ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫናና ሊያስከትል የሚችለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጂኦፖለቲካዊ ቀውስ ዘርዝረዋል።

 

ገበያው ንጉሴ

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ