1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተደጋጋሚ አፈናና ግድያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል

ማክሰኞ፣ መጋቢት 13 2014

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታግተው ከነበሩ 10 ሩ ሲያመልጡ 2 ቱ ህይወታቸው አልፈዋል። መገደላቸው ተገለጠ። ጊጶና በርበር ከተባሉ የገጠር ቀበሌዎች ታግተው ከነበሩት ዐሥሩ ሰዎች መካከል አንዷ የተለቀቁ ሲሆን ሌሎቹ ያመለጡ መሆናቸው ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/48pYO
Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

በተደጋጋሚ ጥቃት ሰዎች እየተገደሉ ነው

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታግተው ከነበሩ 13 ሰዎች መካከል ሁለቱን ጨምሮ በተለያዩ ጥቃቶች ሌሎች ሁለት ሰዎችም መገደላቸው ተገለጠ። ጊጶና በርበር ከተባሉ የገጠር ቀበሌዎች ታግተው ከነበሩት ዐሥሩ ሰዎች መካከል አንዷ የተለቀቁ ሲሆን ሌሎቹ ያመለጡ መሆናቸው ተነግሯል። ከተገደሉት ሁለት ነዋሪዎች ሌላ ሁለት ሰዎች ቆስለው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል። የወረዳው አስተዳደር ሰዎች ታግተው እንደነበር አረጋግጠው ዝርዝር መረጃውን ኮማንድ ፖስትን የሚመለከት ነው ብለዋል። በስፋራው ከሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር መረጃ ለማግኘት በስልክ የተደረገው ጥረትም ስልክ ባለመመለሱ አልተሳካም።  በድባጢ ወረዳ በጫቲ በተባለች ለላ ስፋራ ደግሞ ታጣቂዎች አንድ ሰው መግደላቸውን ነዋሪዎች አመልክተዋል። በትናንትው ዕለትም በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ማንኩሽ ከተማ አቅራቢያ አምስት ሰዓት ገደማ ታጣቂዎች በተኮሱት ከባድ ጦር መሣሪያ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉና ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በክልሉ ካማሺ ዞን ደግሞ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሸማቂዎችና መንግስት የእርቀ ሰላማዊ ጉባኤ ማካሄዳቸው እና የዞኑ ሰላም መሻሻሉን ባለፈው ቅዳሜ መዘገባችን ይታወሳል።

በመተከል ዞን ድባጢ ወረዳ ጊጶ ከተባለ ስፋራ ወደ ድባጢ ከተማና ግልገል በለስ  ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 13  ተጓዦች ታግተው እንደነበር ነዋሪዎች አመልክተዋል።  ታግተው ከነበሩት ሰዎች መካከል 10ሩ ማምለጣቸው የተነገረ ሲሆን፤ ካመለጡት መካከል በ2ቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን አንድ ወንድማቸውን እያሳከሙ የሚገኙ ነዋሪ ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናግረዋል። በስፍራው ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከጸጥታ ኃይሎች ፈቃድ ውጭ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንዳሉና የጸጥታ ኃይሎችም ክትትል እንዲያደርጉም ጥቆማ ተሰጥቶ እንደነበር አክለዋል። 

Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

በወረዳው ባለፈው ሐሙስ ታግተው ከነበሩት መካከል ልጃቸውን ጨምሮ በመንደራቸው የሚኖሩ ሌሎች አራት ሰዎች  እንደሚገኙ ሌላው የአካባቢ ነዋሪ ተናግረዋል። ከትናንት በስትያ የአካባቢው ማኅበረሰብ የታገቱ ሰዎችን ለመፈለግና ለማስለቀቅ ባደረደጉት እንቅስቃሴ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ እንደነበርና በአንድ ሰው ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም አብራርተዋል። ልጃቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ የተለቀቁ ሲሆን፤ ሕይወታቸው ካለፉት መካከል 2ቱ የቅርብ ዘመዳቸው መሆናቸውም አክለዋል። በመተከል ዞን የድባጢ ወረዳ አስተዳደር በወረዳው ሰሞኑን ሰዎች መታገታቸውን ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል። 

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሙላለም ዋቅወያ 15 ሰዎች ታግተው እንደነበር ገልጸው ዝርዝር መረጃውን አካባቢውን የሚቆጣጠረው አስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ወይም ኮማንድ ፖስትን የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል። ከዞኑ ኮማንድ ፖስት ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግሁት ጥረትም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳከም።
ድባጢ ወረዳ በመተከል ዞን ስር ከሚገኙት ሰባት ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ዞኑ በኮማንድ ፖስት መጠበቅ ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው በተፈጠሩት ጥቃቶችና ግጭቶች ምክንያት በሰዎች ሕይወት እና ንብረት ላይም ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል። ከዚህ ቀደም በተፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች ከዞኑ ብቻ ከ360ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ከዚህ ቀደም መዘገባችንም ይታወሳል።

ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ