1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የኢትዮጵያ የግጭት አዙሪትና የአሜሪካ የፖሊሲ ንግግር

እሑድ፣ ግንቦት 18 2016

ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት በተመለከተ ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ ለየት ያለ የፖሊሲ አቋሙዋን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ከአዲስ አበባ ዐሳውቃለች ። ጉዳዩ 33 ዓመት ወደ ኋላ ወደ ለንደኑ ስብሰባም ይወስደናል ። እንዴት? መልሱን ከሳምንታዊው የውይይት መድረክ ያድምጡ ።

https://p.dw.com/p/4gG0h
አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዓርማ
አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዓርማምስል Seyoum Getu/DW

ከ33 ዓመታት በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ

ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት በተመለከተ ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ ለየት ያለ የፖሊሲ አቋሙዋን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ከአዲስ አበባ ዐሳውቃለች ። አሜሪካ አዲስ አበባ በሚገኙት አምባሰደሯ ኧርቪንግ ማሲንጋ  በኩል ባስተላለፈችው መልእክት፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ታጣቂዎችን ጭምር ያካተተ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲደረግ አሳስባለች ። አምባሳደሩ፦ «በሰብአዊ መብቶች እና ውይይት የፖሊሲ ንግግር» በሚል ርእስ ያስተላለፉት መልእክት «ግጭትን ለማቆም እና» ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ያለመ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካል መሆኑንም ዐሳውቀዋል ።

በዚያው ሰሞን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት በአፍሪቃ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር ከኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ አመራር፤ ከትግራይ ክልል እና ከፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋ ተነጋግረዋል ። ከዩናይትድ ስቴትስ ማሳሰቢያ  በኋላ፦ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ተወካዮች፥ የአማራ ፋኖ እና ትግራይ ክልል ያሉ ፖለቲከኞች በየፊናቸው መልስ ሰጥተዋል ። ልዕለ-ኃያሏ አሜሪካ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዐውድ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ርምጃዋ ጎልቶ የወጣበት እና ጎሣ-መር የፖለቲካ ተዋንያን መድረኩን እንዲቆጣጠሩ ያመቻቸችበት የለንደኑ ስብሰባ በነገው እለት 33ኛ ዓመቱን ይደፍናል ። ባለፉት 33 ዐመታት በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች መሪዎች የተቀያየሩባት ኢትዮጵያ ረዘም ላለ ጊዜ ከግጭት እፎይ ያለችበት ጊዜ የለም ። የእርስ በርስ ጦርነት፥ ማንነት ተኮር ግድያና ማሳደድ፥ ብርቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች በተደጋጋሚ እንደሚፈጸሙ የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ያሳውቃሉ ። «የኢትዮጵያ የግጭት አዙሪትና የአሜሪካ የፖሊሲ ንግግር» የዛሬው እንወያይ ዐቢይ ትኩረት ነው ። በውይይቱ 3 እንግዶች ተሳትፈዋል ።

1- ኢሜረተስ ፕሮፌሰር ዳንኤል ተፈራ፤ የኢኮኖሚክስ መምህር ሆነው ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ ምሁርናቸው ። በኢትዮጵያ ጉዳይ የተለያዩ ጽሑፎችን ለንባብ አብቅተዋል ። የአምባሳደሩ ንግግር ላይ ተንተርሰው የጻፉትን ጽሑፍ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት ልከዋል። መረጃውንም ለዶይቸ ቬለ አካፍለዋል ።

ከአዲስ አበባ ከተማ ንግግር ያሰሙት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪንግ ማሲንጋ
የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪንግ ማሲንጋ፦ «በሰብአዊ መብቶች እና ውይይት የፖሊሲ ንግግር» በሚል ርእስ ከሰሞኑ ከአዲስ አበባ ከተማ ንግግር አሰምተዋልምስል Abebe Feleke/DW

2- ዶ/ር ታዬ ብርሃኑ፦ በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በዩኒቨርሲቲ መምህር፤ የፖለቲካል ሣይንስ እና ኤኮኖሚክስ ምሑር ናቸው ። በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የኤኮኖሚ እንቅስቃሴን በተመለከተ በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ መጻሕፍትን ጽፈዋል ። የተለያዩ መጣጥፎችንም ለንባብ ያበቃሉ ።

3- አቶ መስፍን ተገኑ፦ የአሜሪካ ኢትዮጵያ የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (AEPAC) ሊቀመንበር፤ እንዲሁም የአር ኤክ ፓራዳይም (RxParadigm, Inc.) ኩባንያ ሥራ አስኪኢጅ ናቸው ። የአሜሪካው (The Hill) የተባለው መጽኄት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽሑፎችን ያቀርባሉ ። የኢትጵያ የፖለቲካ ሁኔታ እና የአሜሪካን ሚናን በሚመለከት አንድ ጽሑፍ ለንባብ አብቅተዋል። 

ግንቦት 19 ቀን፣ 1983 ዓ.ም በለንደኑ ስብሰባ ጎሳ ተኮር የፖለቲካ ተዋንያን በኢትዮጵያ ሥልጣን እንዲቆጣጠሩ የዩናይትድ ስቴትስ ሚና ግንባር ቀደም ነበር ። አማጺያን በተኩስ አቁም ስምምነት ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን ፍቃድ የሰጡበት ቀን በነገው ዕለት ግንቦት 19 ልክ 33ኛ ዓመቱን ይደፍናል ።  ያ ውሳኔ ምን በኢትዮጵያ ቀጣይ የፖለቲካ ዐውድ ላይ ያመጣውን አንደምታ ምሁራኑ በመተንተን ነው ውይይታቸውን የሚጀምሩት ።  እና ማለት ነበር? ጥያቄው ለሁላችሁም ነው። የባይደን አስተዳደር ስለ ኢትዮጵያ የሚከተለውን የፖለቲካ መርኅ ምን እንደሚመስልም ቃኝተዋል ። ዩናይትድ ስቴትስ  በኢትዮጵያ ነፍጥ ያነገቡትንም ጨምሮ ሁሉም አካላት በብሔራዊ ምክክር ተሳትፈው እንዲነጋገሩ አሳስባለች ። ይህን ሐሳብ እንዴት ወደ መሬት ማውረድ እና ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል? የሚለው ጥያቄን አብራርተዋል ።

ሙሉ ውይይቱን በድምፅ ማእቀፉ ማድመጥ ይቻላል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ