1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የመንግሥት ኃይሎችና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ በላሊበላ

ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016

ትናንት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናገሩ። እንደ እማኞቹ ውጊያው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት የዘለቀ ነበር።

https://p.dw.com/p/4g9Kc
ፎቶ ከማኅደር፤ የፋኖ ታጣቂ በላሊበላ
ውጊያው በላሊበላ አራቱም አቅጣጫ እንደነበረ የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ፎቶ ከማኅደር፤ የፋኖ ታጣቂ በላሊበላምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

የላሊበላው ውጊያ

ትናንት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናገሩ። በየጊዜው በአካባቢው የሚደረገው ውጊያ የከባድ መሣሪያዎች ተኩስ የሚፈጥረው ንዝረት የዓለም ቅርስ በሆኑት የቅዱስላሊበላአቢያተ ክርስቲያናት ላይ የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ነዋሪዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

በአማራ ክልል ካለፈው ዓመት ሐምሌ ጀምሮ የተባባሰው ግጭት አሁንም መፍትሔ ሳያገኝ ወራትን አስቆጥሯል። ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ጋብ ሲል በሌሎቹ አካባቢዎች ደግሞ የማገርሸት ሁኔታ ይታይበታል። ትናንት በላሊበላ ከተማ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት የዘለቀ ውጊያ በመከላከያና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እንደነበር ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ውጊያው በላሊበላ ከተማ ዙሪያ ቢሆንም ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ግን ይሰማ የነበረው በላሊበላ አየር ማረፊያ አካባቢ እንደነበር አንድ አስተያየት ሰጪ አመልክተዋል።

«ውጊያው በላሊበላ አራቱም አቅጣጫ ነበረ፣... በባሰ ሁኔታ ግን ተኩስ የነበረው በላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ነው፣ ማሀል ላሊበላ ከተማ ላይ ደግሞ በጣም ከባድ ነበር፣ የመከላከያ ሠራዊት ራሱን ለመከላከል ይመስለኛል ከባድ መሳሪያ ከከተማዋ ወደ ውጪ ሲተኩስ ነበር፣ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ምሽት ድረሽ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ተኩስ ነበር።» ብለዋል።

ሌላ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ከመሀልላሊበላ ከተማ አደባባይ ከባድ መሳሪዎች ወደ ውጪ ሲተኮሱ እንደነበር ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል። በተመሳሳይ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንዱ የላሊበላ ነዋሪም እንዲሁ ከተማዋ በከባድ መሳሪያ ድምፅ ስትናጥ እንደዋለች ተናግረዋል። በየጊዜው በከተማዋና በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲናት ዙሪያ በሚደረጉ ውጊያዎች ከባድ መሳሪያዎች ሲተኮሱ በሚፈጥሩት ንዝረት ቤተክርስቲናቱ ለበለጠ አደጋ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እንዳላቸውም ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚያስረዱት።

የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ
የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ ምስል AFP via Getty Images

«... የንዝረቱ ጉዳይ ምንም አጠያያቂ አይደለም፣ ምክንያቱም ተኩሱ ከቤተክርስቲያናቱ በግምት መቶ ሜትር ያክል ቢርቅ ነው፣ ስለዚህ የከባድ መሳሪዎች ድምፅ ንዝረት በአቢያተ ክርስቲያናቱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።» ሌላ የላሊበላ ከተማ ነዋሪም ተመሳሳይ ስጋት እንዳላቸው ገልጠዋል።

በላሊበላ ከተማ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ የከተማ ውስጥ እንቅስቃሴዎችና ሱቆች በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም ከላሊበላ ከተማ መውጣትም ሆነ መግባት እንደማቻል አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል።

ከትናንት ቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በከተማዋና አካባቢው ተኩስ የቆመ ሲሆን አሁን ከተማዋ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ስር እንደሆነችም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። ትናንት በነበረው ውጊያ ስለደረሰው ጉዳት ከየትኛውም አካል ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። ከአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱና ለላክነው አጭር የጽሑፍ መልዕክት ምላሽ ባለማግኘታችን አልተሳካም። ከፋኖ በኩልም አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አድራሻ ማግኘት ባለመቻላችን አልሰመረም። የአማራ ክልል በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ከሐምሌ 2015 ዓ ም ጀምሮ ለስድስት ወራት በሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ከቆየ በኋላ ጊዜው ሲጠናቀቅ እንደገና ከጥር 2016 ዓ ም ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ለአራት ወራት ተራዝሞ አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንታት ይቀሩታል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ