1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ለኢትዮጵያው ግጭት መፍትሄ የአሜሪካ ጥሪ፦ የአምባሳደሩ ንግግር

ሐሙስ፣ ግንቦት 8 2016

በኢትዮጵያ የተኩስ አቁም ተደርጎ ሁሉም በግጭት ውስጥ ያሉ አላካት ለዘላቂ ሰላም እንዲደራደሩ ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች ። በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በትናንትናው እለት ባሰሙት ንግግራቸው የኢትዮጵያ መንግስትም ፖለቲከኞችን ጭምር ከእስር በመልቀቅ እንዲመክር ጠይቀዋል ።

https://p.dw.com/p/4fvqP
Äthiopien US-Botschafter Ervin J. Massinga
ምስል Abebe Feleke/DW

በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ተፋላሚዎች ከአሜሪካ የቀረበ ጥሪ

በኢትዮጵያ የተኩስ አቁም ተደርጎ ሁሉም በግጭት ውስጥ ያሉ አላካት ለዘላቂ ሰላም እንዲደራደሩ ስትል ዩናይትድ ስቴትስ  ጠየቀች ። በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በትናንትናው እለት ባሰሙት ንግግራቸው የኢትዮጵያ መንግስትም ፖለቲከኞችን ጭምር ከእስር በመልቀቅ እንዲመክር ጠይቀዋል ። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በታንዛንያ ዳሬሰላም ጀምሮት የነበረውን ድርድር አወድሰው እንዲገፋበት ጠይቀዋል ። በአማራ ክልል ፋኖን በተመለከተ ሲናገሩም፦ «እራሳቸውን ፋኖ ብለው ለሚጠሩ» ሲሉ በመንደርደር መልእክት ያሉትን አስተላልፈዋል ። በትግራይ በተለይ ሕወሓትን ጠቅሰው ንግግር አሰምተዋል ። 

የአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ መልእክት

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በትናንትናው እለት ከመርካቶ ቅርብ ስፍራ ላይ የሚገኘውን የአሜሪካ ጊቢ ለመጀመሪያ ጊዜ መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ ይህ ስፍራ ከ87 ዓመታት በፊት በ1937 ዓ.ም 20 ሺህ ኢትዮጵያውያን በየካቲት 12 በፋሽስት ቅኝ ገዢ ከመጨፍጨፋቸው ጋር ያለውን ታሪካዊ ቁርኝት አስታውሰው ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡

ከ87 ዓመታት በፊት ሰብአዊነትን የገፈፈ አስነዋሪ ያሉት ድርጊት የለምንም የሕግ ሂደት በጅምላ በያኔው የካቲት 12 መፈጸሙን «ኢትዮጵያውን ከኔ በበለጠ ያውቁታል» ያሉትአምባሳደር ማሲንጋ፤ በጦርነት ወቅት ላይ እንኳ ቢሆን ለሰብአዊ መብቶች እና ክብር ብሔር፣ ሃይማኖት እና ቋንቋ ሳይለይ ጥብቅና መቆም አስፈላጊ መሆኑን ከዚህ በላይ አስተማሪ ክስተት ያለ አይመስልም ብለው ወደ ዋና ጉዳያቸው ለመግባት ታሪክ አጣቅሰዋል ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ተፋላሚዎች የቀረበ ጥሪ

ዛሬም ኢትዮጵያ በውስጣዊ ችግር ፈተና ላይ መሆኗን ያነሱት አምባሳደር ማሲንጋ፤ የታጠቁ ኃይሎች የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ከውይይት ይልቅ በአመጽ ለመፈጸም መሞከራቸው ችግሮች መልካቸውን ቀያይረው እንዲቆይ አድርገዋል ብለዋል፡፡ አገራቸው አሜሪካ መሰል ታሪኮችን በአንድ ወቅት ማሳለፏን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ "አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሰላማዊ ዜጎች ያለፍርድ ሂደት መገደል፣ ሕገወጥ እስር፣ በኃይል መሰወር፣ ግጭት ጋር የተያያዙ የጾታ ጥቃት እና ሌሎችም ጥሰቶች መፈጸማቸው ሲሰሙ ሐዘን ይሰማናል” ብለዋል፡፡ ችግሮቹም የሚፈቱት ፈጣን ተጠያቂነት በማስፈን ግልጽ እና ሀቀኛ የሽግግር ፍትህ በማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡

"እዚህ ጋ ግልጽ ልሁን፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ያላችሁ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) በታንዛንያ ዳሬሰላም የጀመራችሁትን መግባባት ላይ ለመድረስ ያደረጋችሁት የድርድር ጥረት ላይ ተስፋ አትቁረጡ፡፡ በርካታ ሕዝብ በግጭት ተሰቃይቷልና ለሕዝቡ ፍላጎት ስትሉ ተስፋችሁን በማደስ የሰላዊ መንገድ ሻቱ ።» ብለዋል ። 

አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፥
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፥ ቆመው ንግግር የሚያሰሙት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

"በአማራም እራሳቸውን ፋኖ ብለው ለሚጠሩና እየተዋጉ ላሉት መልእክቴ ተመሳሳይ ነው፡፡ የድርድር ሀሳብ ማጣጣል አይጠቅምም፡፡ በመላ አገሪቱ እየቀጠለ ባለው ግጭት ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ሰላማዊ ዜጎች እንደመሆናቸው፤ ያላችሁን ጥያቄ በውይይት እና አመጽን ባልተከተለ መንገድ ብትፈቱት እላለሁ» ሲሉ ተናግረዋል ።

"በትግራይም ላላችሁ በተለይም ለሕወሓት ያለኝ መልእክት በጦርነት ወቅት የተፈናቀሉትን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ጉዳዩ አስቸጋሪ ጉዳይ መሆኑን ዐውቃለሁ፡፡ ግን መፍትሄው ግዛቶቹን በኃይል በመመለስ መሆን የለበትም፡፡ በብሔራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትህ ሂደት ላይ መሳተፋችሁ በክልላችሁ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እጅግ ወሳኝ ነው፡፡»

"ኢትዮጵያን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጣችሁ ማለትም ለመንግስትም ሀገሪቱ በጦር ሜዳዎች ይልቅ በሰላማዊ መንገድ የምታተርፋቸው ይበዛል ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ የጸጥታ ኃይልን መገንባት ላይ በማተኮር ብቻ ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግር አይፈታም፡፡ መንግስትን የሚወቅሱትን ሁሉ ማሰርና ማሰቃየት ሊቀረፍ የሚገባውን ችግር አይፈታም፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት የፖለቲካ ውይይት ፖለቲከኞችን በመፍታት ጭምር መደገፍ አለበት፡፡… ” ሲሉ የአገራቸውን አቋም ዘርዝረዋል፡፡

በግጭት ወቅት ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሊሰጥ ስለሚገባው ጥንቃቄ

አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ቀጠሉ፡፡ እያንዳንዱ የታጠቁ ቡድኖች በኢትዮጵያ እየቀጠለ ባለው የሰዎች መፈናቀል እና ስቃይ ላይ አስተዋጽኦአቸው ጉልህ መሆኑን አስረዱ፡፡ "ይህ መቆም አለበት” ያሉት አምባሳደሩ "በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት፣ በውሃ መሰረተልማቶች እና የእርዳታ አቅርቦት መስመሮችን በመዝጋት የሚደሩ ጥቃቶ እንዲቆሙ” ሲሉም አጽእኖት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት በርካቶች ለጉዳኅ ተዳርገዋል
ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት በርካቶች ለጉዳኅ ተዳርገዋል፥ በተ,ለይ ደግሞ ሴቶች እና ሕፃናት የችግሩ ዋነና ገፈት ቀማሾች ናቸውምስል Nariman El-Mofty/AP/picture alliance

"አሁንም አጽእኖት የምሰጠው ነገር፤ በየትኛውም  የኢትዮጵያ አቅጣጫ በሚደረገው የጦር ሜዳ ውጊያ አሸናፊነት የለም፡፡ በግጭት ላይ የሙጥኝ ማለቱ ምናልባት ድካምና መሰላቸትን ያመጣ እንደሆን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ አያተርፉም፡፡ ለዚህ ነው የውይይት ጊዜ አሁን ነው የምንለው፡፡ ምንም እንኳ አሁን ላይ ሙሉ ባሆንም በሂደት ሊሆን ስለሚችል ሁሉም አካላት በብሔራዊ መግባባት ምክክር ሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ነው የምንጠይቀው፡፡ እነሱ የታጠቁ አካላትን ጨምሮ ሁሉም ደድምጾች በሂደቱ እንዲሰሙ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ለተሻለች ኢትዮጵያን መነሻ መንገድ ሊሆን ይችላል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባሁን ወቅት በጥላቻ ንግግሮች በመፈተን ብቸኛ አገር አይደለችም ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ቁምነገሩ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት በመመካከር በጋራ መፍታት ላይ ማተኮር ነው ብለዋል፡፡

የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ አፍሪካን ወክላ በዓለም መድረክ የምትታይ ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ያላት ተፈላጊነትም አጽእኖት የሚሰጠው መሆኑንም ጠቁመው፤ ግልጽና ገንቢ በሆነ መርህ የተረጋጋ ሀገር እንዲገነባ፤ ሰብዓዊ መብቶችም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዲከበሩ ጠይቀዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ