በግጭት ጥላ ውስጥ የሚካሔደው የኢትዮጵያ ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ በእርግጥ ምን ይፈይዳል?
ረቡዕ፣ ግንቦት 19 2018
ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች በግጭት ጥላ ውስጥ በሚካሔደው የኢትዮጵያ ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ሰኞ ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለክልል፣ ለአዲስ አበባ እና ለድሬዳዋ ምክር ቤቶች ለሚካሔደው ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ10,000 በላይ ዕጩዎች ይወዳደራሉ።
ይሁንና በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ያለው ጥልቅ ልዩነት ባለመፈታቱ በትግራይ ክልል ምርጫ አይካሔድም። የፋኖ ታጣቂዎች ከፌድራል እና የክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት እየተዋጉ በሚገኙበት በአማራ ክልል በስምንት የምርጫ ክልሎች ግንቦት 24 ቀን 2018 ድምጽ እንደማይሰጥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚያደርገው ውጊያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች የምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ ዕጩዎችን እና ድምጽ ሰጪዎችን ሥጋት ላይ የሚጥሉ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሔደው ምርጫ “ያለውን ሁኔታ” (status quo) ከማስቀጠል የዘለለ ኢትዮጵያ ለገባችበት የግጭት አዙሪት መፍትሔ ማምጣት እንደማይችል ዶክተር ግርማቸው ዓለሙ ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ግርማቸው እንደሚሉት ጦርነት እና ግጭት ከምርጫ “ተቃራኒዎች ናቸው።” ምርጫ የሚካሔደው በጠብ መንጃ ሰው የሚጠፋበት፣ ንብረት የሚወድምበት እና አገር የሚፈርስበት “ግጭት እንዳይመጣ ነው።”
የተዳከሙ ተቃዋሚዎች
የፌድራል መንግሥቱን እና ከትግራይ በቀር ሁሉንም የክልል መስተዳድሮች ሥልጣን የተቆጣጠረው ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ የሚፎካከረው ከተዳከሙ እና ከተከፋፈሉ ተቃዋሚዎች ጋር ነው።
ባለፉት ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ለሁለት ተከፍለዋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር የነበሩት በቴ ኡርጌሳ በሚያዝያ 2016 የተገደሉ ሲሆን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ አቶ ክርስቲያን ታደለ አሁንም እስር ላይ ናቸው።
የፍራንክፈርት የሰላም ጥናት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ከባቢ የሥጋት ደረጃ (Political Environment Risk Level) እንደ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ሁሉ ከፍተኛ እንደሆነ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሐተታ አሳይቷል።
በአሜሪካው ፍሪደም ሐውስ የ2026 ዓመታዊ ሪፖርት ኢትዮጵያ በምርጫ ሒደት፣ የፖለቲካ ብዝኃነት እና ተሳትፎ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነጻነት እና የሕግ የበላይነት በመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮች ተመዝና “ነጻ ያልሆነ” ተብላለች። አገሪቱ በፕሬስ ነጻነት በሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ ከ180 አገራት 148ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የሚሠራ ምርጫ?
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ሙሉ በሙሉ ነጻ እና ፍትኃዊ ምርጫ አካሒዳ አታውቅም። የፌድራል መንግሥት ከህወሓት ጋር የገጠመው ጦርነት ጋብ ባለበት ቅጽበት በሁለት ዙሮች በተካሔደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 96 በመቶውን አሸንፎ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን “የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍታኃዊ፣ አካታች” ለማድረግ መንግሥታቸው አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ከጥቂት ወራት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረው ነበር። ዐቢይ “ይኸ ፓርላማ አሁን ካሉ አምስት እና አስር ሰዎች በአምስት እና አስር እጥፍ ያደገ ድምጾች ይሰማሉ” ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቃዋሚዎች በርከት ያሉ መቀመጫዎች ሊያገኙ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ዐቢይ እንዳሉት የምክር ቤቱ ስብጥር ተቃዋሚዎችን እንዲያካትት መንግሥታቸው “አውድ ማስፋት ብቻ ሳይሆን ይሁነኝ ብሎ ይሠራዋል።” ለዚህም “ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው” በፓርላማው የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች ዳግም እንደማይወዳደሩ ገልጸው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዒድ አል አድሐ በአልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ምርጫውን “ሀገረ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን የሚጠነክርበት” ብለውታል። ከዚህ በተጨማሪ “የቀጣይ ዓመታት የሀገራችንን እጣ-ፈንታ የምንበይንበት፣ ከምንም በላይ ብዝኃ ድምጽ የሚሰማበት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የምንመሰርትበት ወሳኝ አጋጣሚ” እንደሚሆን ገልጸዋል።
ተቃዋሚዎች ምን አሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድምጽ ከመሰጠቱ ከወራት በፊት ተቃዋሚዎች በሕግ አውጪው ምክር ቤት መቀመጫ እንደሚኖራቸው ቢናገሩም ዶክተር ሳሙኤል ዘውዴ ግን ምርጫው አገሪቱን ሰንቆ ለያዛት ችግር መፍትሔ መፍጠር ይችላል የሚል ዕምነት የላቸውም። የኢኮኖሚ ጉዳዮች ጥናት ባለሙያው ዶክተር ሳሙኤል እንደሚሉት ምርጫ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔ መፍጠር ቢችል ኖሮ የቀድሞው ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሳለ የተካሔዱት “አገሪቷን የት እና የት ያደርሷት ነበር።”
“በማስፈራራት፣ የፖለቲካውን አውድ በማጥበብ፣ ብቻ ተወዳድሮ ማሸነፍ እና አሐዙን ብቻ በማቅረብ ‘ልዕልና አለኝ' ብሎ ማለት ሊበጅ አይችልም” የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል በመሰል አካሔድ ኢትዮጵያ ከገባችበት “አዙሪት መውጣት” አትችልም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ዶክተር ሳሙኤል “ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለችው” የሚል እምነት አላቸው። ከችግሩ የምትላቀቀው በሀገራዊ ዕርቅ እና በሥምምነት “አማካኝ መንገድ” በመፈለግ ነው። “የሚሊዮኖችን ሲቪል ሰዎች ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የፖለቲካ አውድ በመሠረታዊ ደረጃ ሊቀይር የሚችል፣ አገሪቱን ወደ ሰላም፣ ወደተረጋጋ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ አውድ” የሚመራ መፍትሔ እንደሚያሻ ዶክተር ሳሙኤል ይሞግታሉ።
ገዥው ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ጋምቤላ፣ ሐዋሳ እና ድሬ ዳዋን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በተካሔዱ ሰልፎች የምረጡኝ ቅስቀሳዎቹን ትላንት ማክሰኞ ሲያጠናቅቅ ግን አገሪቱ በተሻለ ጎዳና ላይ እንደምትገኝ አመራሮቹ ሲናገሩ ተደምጧል።
ከ10 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉትን ፓርቲ በፕሬዝደንትነት የሚመሩት ዐቢይ አሕመድ በመገናኛ ብዙኃን በተካሔዱ ክርክሮችም ይሁን በአደባባይ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች እስከ አሁን አልተሳተፉም።
ፎቶግራፎቻቸው ግን በአዲስ አበባ በተካሔደው የፓርቲው የቅስቀሳ ሰልፍ ላይ ከፍ ብለው ታይተዋል። በሰልፉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ እንዲሆን ማድረግ ዋናው ግባችን እንደሆነ እንድትረዱልን እንወዳለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
በሺሕዎች የሚቆጠሩ አባላት እና ደጋፊዎች ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ፣ ተመሣሣይ ቲ-ሸርት ለብሰው መፈክሮች አንግበው የታዩባቸው ሰልፎች በገዥው ፓርቲ እና ለምርጫ በተመዘገቡ ተቃዋሚዎቹ መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት የሚያሳዩ ናቸው።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለበት የጥሞና ጊዜ ሲቃረብ ከገዥው ፓርቲ በተጨማሪ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብንን የመሳሰሉ ፓርቲዎች በተለያዩ ከተሞች የድምጽ ሰጪዎችን ቀልብ ለመግዛት ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ባካሔደው ቅስቀሳ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፕሬዝደንት አብርሀም ኃይማኖት “አስቻይ ሁኔታዎች አልተፈጠሩም። የታሠሩ እስረኞች እስካሁን አልተፈቱም። በሒደቱም ብዙ ውስብስብ ችግሮች አሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ እዮኤል ሰለሞን “እየገጠሙን ካሉ ተግዳሮቶች አኳያ የምርጫው ሒደት ሙሉ በሙሉ ፍትሐዊ እና ነጻ ነው ማለት አንችልም” ሲሉ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
“በብዙ ቦታዎች በነጻነት የምርጫ ቅስቀሳዎችን ማካሔድ አንችልም” ያሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ዕጩ ተወዳዳሪ ይሱፍ ኢብራሒም በበኩላቸው የፓርቲያቸው ዕጩዎች እና ደጋፊዎች በፋኖ ታጣቂዎች “ማስፈራራት፣ ማዋከብ እና የግድያ ዛቻ” እንደደረሰባቸው ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።
ዶቸ ቨለ ያነጋገራቸው ተቃዋሚዎች ከብልጽግና ፓርቲ የሚስተካከሉ የምርጫ ቅስቀሳዎች ማካሔድ እንዳልቻሉ አልሸሸጉም። የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ፣ ክልከላዎች እና ገዥው ፓርቲ ከቀበሌ እስከ ፌድራል በተዘረጋው መዋቅር ያለው ቁጥጥር ሒደቱ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ እንዲሆን አድርጎታል።
ዶክተር ግርማቸው ዓለሙ በአሁኑ ወቅት “መንግሥት እና ፓርቲ ልዩነቱ አይታይም” ሲሉ ይተቻሉ። “በደርግም ኢሠፓ ማለት መንግሥት ነው። ኢሕአዴግ ማለት መንግሥት ነው። ብልጽግናም ማለት መንግሥት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የመንግሥት ሥልጣን በሚቆጣጠሩ ፓርቲዎች ዘንድ “በምርጫ እንለቃለን የሚል አስተሳሰብ የለም” የሚሉት የሕግ ባለሙያው ይህ የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ጦርነት እና የኃይል አማራጭ እንደሚገፋ አስረድተዋል።
“በእንዲህ ዐይነት ሁኔታዎች ውስጥ ምርጫ ማካሔድ መንግሥት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ የተመረጠ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳየት የታለመ ልማድ እንደሆነ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይተቻሉ። ፕሮፌሰር መረራ የሚመሩት ኦፌኮ በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሳይሳተፍ ቀርቷል።
በሰኞው ምርጫ የሚያደርገው ተሳትፎም ቢሆን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላለመሠረዝ ብቻ ነው። በ50 ዓመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፈው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ካሉት ጽህፈት ቤቶች በሥራ ላይ የሚገኘው አንዱ ብቻ እንደሆነ የፓርቲው ኃላፊዎች ለዶቸ ቨለ ተናግረዋል።
አርታዒ አዜብ ታደሰ