1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ ህዝባዊ እምቢተኝነትን አሰመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ረቡዕ፣ መጋቢት 2 2018

ይህ ትዕይንተ-ሕዝብ በአገሪቱ የሚዲያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፣በዩትዩብ ከአንድ ሚሊዮን በሳተላይት ቴሌቪዥን ደግሞ ከ10 ሚሊዮን ያላነሰ ህዝብ በቀጥታ ሥርጭት እንዲከታተለው ታቅዶ የሚካሄድ መሆኑን የአዘጋጁ ግብረ ኃይል አስታውቋል።የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉት አቶ አያና ፊይሳ ደግፎ ሰልፍ ሊወጣላቸው የሚችል ሰው ስለመኖሩ ጥያቄ አላቸው ።

https://p.dw.com/p/5AA4j
ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው
ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ምስል፦ privat

በኢትዮጵያ ህዝባዊ እምቢተኝነትን አሰመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በኢትዮጵያ የሕዝባዊ እምቢተኝነትትግልንበአገር ውስጥ ለማነሳሳት የሚያስችሉ ትዕይንተ-ሕዝብ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን የአዘጋጁ ግብረ ኃይል የቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ። የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ልደቱ አያሌው፣ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት፣በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ፣አንድ ታላቅ የበይነ መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ-ሕዝብ እና ሁለት ሰላማዊ ሰልፎች በዋሽንግተን ዲሲና በለንደን ከተሞች ይካሄዳሉ። የትዕይንተ-ሕዝብ አዘጋጅ ግብረ ኃይል የቴክኒክ ኮሚቴ፣በትናንትናው ዕለት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ሽግግር ከምርጫ በፊት

ይኸው ግብረ ኅይል፣''ጦርነት ይቁም፣የግፍ አገዛዝ ያብቃ፣ሰላም ይስፈን፣ሁሉን አቀፍ ሽግግር፣ከምርጫ በፊት!'' የሚሉ መሪ ሃሳቦችን አንግቦ የተቋቋመ መሆኑን፣ለጋዜጠኞች አስታውቋል። የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ልደቱ አያሌው፣ግብረ ኅይሉ፣ያቀዳቸውን ተግባራት አስመልክቶ ዶቼ ቨለ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ እንደሚከተለው መልሰዋል።
''በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መካሄድ አለበት የሚል እምነት ያለን ስብስቦች፣አንድ ላይ ሆነን ወደ እዛ ሊያመሩ የሚችሉ አንዳንድ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለብን የሚል እምነት ኖሮን፣ እና አንድ በቅርቡ አንድ የበይነ መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ ሕዝብና በዋሽንግተን ዲሲና በለንደን ደግሞ፣ ሰፊ የሆነ የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የሚኖርበት ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረግን ነው እና ለዚህ ዓላማ የተቋቋመ ግብረ ኀይል ነው።''

ከሁለት ሳምንታት በኋላ፣ሊካሄድ በታሰበው፣ የበየነ-መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ ህዝብ፣ ከ15 እሰከ 20 የሚደርሱና፣ በሀገሪቱ ፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን ንግግር እንደሚያደርጉ የአዘጋጁ ግብረ ኃይል፣ለዶቼ ቬለ በላከው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።
ይህ ትዕይንተ ሕዝብ፣ በአገሪቱ የሚዲያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፣በዩትዩብ ከአንድ ሚሊዮን፣ በሳተላይት ቴሌቪዥን ደግሞ፣ከ 10 ሚሊዮን ያላነሰ ህዝብ፣በቀጥታ ሥርጭት እንዲከታተለው ታቅዶ የሚካሄድ መሆኑም ተገልጿል።
 

የግብረ ኃይሉ አወቃቀር

የትዕይንተ ሕዝብ አዘጋጅ ግብረ ኅይሉ፣ ከተለያዩ ተቋማትና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተውጣጡ፣ 25 የምክር ቤት አባላትና ሰባት የቴክኒክ ኮሚቴዎች ያቀፈ እና ሰፊ ማኅበራዊ መሰረት እንዲኖረው ተደርጎ የተዋቀረ መሆኑን አቶ ልደቱ ጠቁመዋል።
''ይሄ ግብር ኅይል፣ ሰፊ ማኅበራዊ መሰረት እንዲኖረው ተደርጎ፣ በሁሉን አቀፍነትና አሳታፊነት ተቋቋመ ነው፤ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ያላቸው፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት የህልውና ጥፋት መዳን አለበት የሚል እምነት ያላቸው ኅይሎች ተሰብስበው የፈጠሩት ግብረ ኅይል ነው።''
ስለጉዳዮ አስተያየት የጠየቅናቸው፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉት አቶ አያና ፊይሳ፣ እነዚህ የታሰቡት ተዕይንተ ሕዝቦች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት የላቸውም።

አቶ አያና ፈይሳ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የፖለቲካ ተንታኝ
አቶ አያና ፈይሳ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የፖለቲካ ተንታኝ ምስል፦ privat/DW

''ምንም አማራጮች ያጡ ይመስላሉ። እና እንደእዛ ነው። አገዛዝ አንቀጥቅጥ የሆነ ብለው ከዚህ በፊትም አድርገዋል። እንደእኔ ምልከታ፣ለተቃዋሚዎችም ለአገዛዙም ሰዎች ቅርበት ስላለኝ፣ብዙ ሰዎችን ስለማናግር፣ብዙዎቹን አውቃቸዋለሁ እና እንዳየሁት ከሆነ፣አገዛዝ በዩቲዩብ ሰው በመሰብሰብም ወይም በዲሲ በሚደረግ ሠላማዊ ሰልፍ ምንም ዐይነት መንቀጥቀጥ አይታይበትም፤ወደ ሽግግር መንግሥት አይደለም ወደ ምንም ዐይነት ነገር እንቅልፍ የሚያጡበት አይመስለኝም።''

ትዕይንተ-ህዝብ ለማዘጋጀት የተሰባሰቡ ኃይሎች ስብጥር ሲታይ፣ደግፎ ሰልፍ ሊወጣላቸው የሚችል ሰው ስለመኖሩም ጥያቄ እንዳላቸው አቶ አያና አመልክተዋል።
''ምን ያህል ሰው ይወጣላቸዋል? የተለያየ የትጥቅ ትግል የሚደግፉ፣የሰላማዊ ትግልየሚደግፉ፣በዓላማቸው አንዳንዶቹ ቀኝ ዘመም፣ግራ ዘመም፣መሐል ሰፋሪም፣ ብዙ ዐይነቶች ባሉበት ሁኔታ፣ ደግፎ ሰልፍ የሚወጣውስ ሰው ምን ይመስላል? የሚለውን
ለማየት፣ ለመታዘብ እንቸኩላለን።ከእዛ የዘለለ የፖለቲካ ለውጥ የሚያመጣ ነው የሚለው ብዙ አሳማኝ አይደለም።'' ብለዋል። 

ታሪኩ ኃይሉ

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር