1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለወራት የሚያገለግለው የHIV ተሐዋሲ መድኃኒት

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ማክሰኞ፣ ግንቦት 18 2018

የጤና ሚኒስቴር በኦመት ሁለት ጊዜ በመርፌ የሚሰጥ የHIV ተሐዋሲ መድኃኒት ሀገር ውስጥ አስገብቶ ለመስጠት መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል። የተባለው መድኃኒት በመርፌ የሚሰጠው በተሐዋሲው ለመያዝ ታጋላጭ ለሆኑና ተሐዋሲው በደማቸው ለሌለ ሰዎች የሚሰጥ ነው። ለምን?

https://p.dw.com/p/5ELnu
ሌና-ካፓቨር በመርፌ የሚሰጠው የኤች አይ ቪ ተሐዋሲ መድኃኒት
ሌና-ካፓቨር በመርፌ የሚሰጠው የኤች አይ ቪ ተሐዋሲ መድኃኒት ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Nardus Engelbrecht/AP/picture alliance

ለወራት የሚያገለግለው የHIV ተሐዋሲ መድኃኒት

 

ኢ የኤች አይ ቪ ተሐዋሲን ለመከላከል ያስችላል የተባለ መድኃኒትን ኢትዮጵያ በቅርቡ ለማስገባት እየሠራች መሆኗን የጤና ሚኒስቴር ይፋ ካደረገ ሰነበተ። በመርፌ መልክ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚሰጥ የተገለጸውን ይህን መድኃኒት የሚወስዱ ደግሞ ተሐዋሲው በደማቸው ውስጥ የማይገኝ፤ ሆኖም ግን ለተሐዋሲው ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ የኅብረሰብ ክፍሎች ናቸው። ቀደም ሲልም በእንክብልና በመርፌ መልክ የሚሰጡ የኤች አይቪ መድኃኒቶች እንዳሉ ይታወቃል፤ ሌና-ካፓቨር የተሰኘው ይህ መድኃኒት በምን ይለያል የሚለውን ለዶቼ ቬለ ያብራሩት በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስከያጅ አቶ ፍቃዱ ያደታ፤ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የነበረው በዓመት አራት ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

ተጋላጭ ካሏቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴተኛ አዳሪዎችን በዋናነትየጠቀሱት ባለሥልጣኑ፤ ከባል ወይም ከሚስት አንዳቸው ተሐዋሲው በደማቸው መኖሩ ተረጋግጦ ላልተያዘው አካል ተሐዋሲው እንዳይተላለፍ ለማድረግ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት። በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን አሞኘም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

ስለመድኃኒቱ ምንነት

ብዙዎች መድኃኒት የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ከፈዋሽነት ጋር በማዛመድ ስለሚገነዘቡ ስለ ኤች አይቪ መድኃኒቶች ሲነገር ተሐዋሲውን የሚያጠፋ እንደሆነ አድርገው የመውሰድ ነገር እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ወገኖች ያነሳሉ። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው መስከረም ወር ወደ ሀገር እንደሚያስገባ የገለጸው በመርፌ የሚሰጠው የኤች አይ ቪ መድኃኒትም ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዳያስይዝ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስከያጅ አቶ ፍቃዱ ግን የተባለው መድኃኒት ለኤች አይቪ ያድናል የሚባለው ስህተት መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።  

ኤችአይቪ ገና ፈዋሽ መድኃኒት አልተገኘለትም

ዶክተር ወንድወሰንም በግልጽ መነገር አለበት ያሉት ምንም እንኳን በምርምሩ ዘርፍ ብዙ ሥራዎች ለመሠራት ቢሞከርም ለኤች አይቪ ተሐዋሲ ገና የሚያድነው ወይም የሚያጠፋው መድኃኒት አልተገኘም የሚለው ነው።

በአፍ የሚዋጠው የመድኃኒቶች ድብልቅ
ባለፉት ዓመታት ኤች አይቪ ተሐዋሲ በደማቸው ለሚገኝ ወገኖች በብዛት የተዳረሰው በአፍ የሚዋጠው የመድኃኒቶች ድብልቅ ነበር።ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ NIH-NIAID/IMAGE POINT FR/BSIP/IMAGO

 

ለኤች አይቪ ተገኙ የሚባሉ መድኃኒቶችን በሚመለከት በተለይ ክትባት የሚለው አገላለጽ፤ ተገቢ እንዳልሆነ የተናገሩት የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ለኤች አይቪ ያለው በመርፌ እንደኢንሱልን ሆድ ላይ የሚሰጥ የተሐዋሲውን አቅም የሚያደክም መድኃኒት መሆኑን አብራርተዋል።

የቅስቀሳ መቀዛቀዝ

በአሁኑ ወቅት የኤች አይቪ ተሐዋሲ ስርጭት እንዲገታ ይደረጉ የነበሩ ቅስቀሳዎችና ልዩ ልዩ ትኩረትን የሚስቡ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ የዘመኑ ወጣት ትውልድ ይህ ተሐዋሲ ያደረሰውና እያደረሰ ያለው ጉዳትን እንዳይገነዘብ እንዳደረገው ነው ዶክተር ወንድወሰን ያመለከቱት። ለዚህ ደሞ ዋነኛው ምክንያት አንድም ለዘርፉ ይደረግ የነበረው የበጀት ድጋፍ መስተጓጎል እና የሚወሰዱ መድኃኒቶች በገፍ ይከሰት የነበረው ሞት ድግግሞሹ በመቀነሱ መሆኑን ያነሳሉ።

ዶክተር ወንድወሰን እንደተናገሩት ዛሬም የኤች አይቪ ተሐዋሲ ስርጭት አልተቆረጠም። ከገጠር ይልቅ በንጽጽርም በተለይ ደግሞ በከተሞች አካባቢ መዛመቱ እንደሚበዛም መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ጠቁመዋል። በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ደግሞ ከአስራዎቹ እስከ አርባዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

መድኃኒቶቹን ጥቅም ላይ መዋል ተከትሎም በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ኤች አይቪ ተሐዋሲ በደማቸው ውስጥ እያለም ጤናማ እንደሆነው ረጅም ዕድሜ መኖር መቻላቸውንም አንስተዋል። በዚህ ምክንያትም አንዳንዶች የተሐዋሲውን መኖር ችላ ብለው እንዲዘናጉ ማድረጉን በማመላከት የተቀዛቀዘውን የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከዚህም ሌላ መድኃኒቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን የገለጹት ዶክተር ወንድወሰን ለሚፈልጓቸው ወገኖች የማዳረሱ ሥራ ግን ገና ይቀረዋል ነው የሚሉት።

ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ወገኖች የተሐዋሲውን መጠንና የመዛመት አቅም የሚገቱ መድኃኒቶች ዛሬ በእርግጥም የሞት ወሬን መቀነስ አስችለዋል። ተሀዋሲው ግን አለ፤ እየተዛመተ ነው ዛሬም ማስተዋል፤ ጥንቃቄን ይጠይቃል። ለሰጡን ማብራሪያ ባለሙያዎቹን እናመሰግናለን። 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ