1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አሸናፊው ከወዲሁ የታወቀው የጅቡቲ ምርጫ፤ የሳምባ ነቀርሳ ሥርጭት

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 3 2018

ጅቡቲ ምርጫ አንድ ብላ አሁን ስድስተኛ እስክትደርስ ድረስ በሚደረጉ ምርጫዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ያለመኖር ፕረዚደንቱ፤ የስልጣን ዘመናቸውን ሕገመንግስቱን እያሻሻሉ ጭምር እንዲቀጥሉ እንዳስቻላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/5Bzqu
የጅቡቲ የምርጫ ቅስቀሳ በከፊል
የጅቡቲ የምርጫ ቅስቀሳ በከፊልምስል፦ Tony Karumba/AFP/Getty Images

የመጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም፤ ትኩረት በአፍሪካ

አሸናፊው ቀድሞ የተለየበት የጅቡቲ ምርጫ


የምስራቅ አፍሪካዋ ትንሽዬ ሐገር ጅቡቲ በትላንትናው ዕለት 6ኛው ፕረዚንታዊ ምርጫ አካሂዳለች። ጅቡቲ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የተላቀቀችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በሰኔ 27 ቀን 1977 ዓ.ም ነው። ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ «የጅቡቲ ሪፐብሊክ» በሚል መጠሪያ እንደ ነጻ ሐገር  ከተመሰረተች በኋላ የመጀመሪያው ፕረዚደንት ሐሰን ጉሌህ ኦፕቲዶን ናቸው። እሳቸው ከ1977 እስከ 1999 በስልጣን ላይ ቆይቷል። በ1999 በተካሄደ ምርጫ አጎታቸውን ሐሰን ጉሌህ ኦፕቲዶንን ያሸነፉት እስማኢል ኦማር ጉሌህ ተመረጡ፤ ያው ላለፉት 27 ዓመታት በብቸኝነት ጅቡቲን እየመሩ እንዳሉ አሉ። 
የሕገመንግስት ማሻሻያዎች
ፕረዚደንቱ የዕድሜ ልክ ፕረዚደንት ለመሆን የሚያስችላቸው ሁለት የሕገ መንግስት ማሻሻያዎችን አድርገዋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 ዓ.ም የአንድ የፕረዚደንት የስልጣን ወሰን ሁለት የምርጫ ወቅቶች መሆናቸውን የሚደነግገውን የሕገመንግስቱ አንቀጽ በምክርቤታቸው በማሻሻል ያለገደብ መወዳደር እንዲያስችላቸው አድርገው መቅረጻቸውን ይነገራል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በአለፈው ዓመት ጥቅምት 26 ቀን 2025 የአንድ ፕረዚደንት የዕድሜ ጣሪያ 75 ዓመት እንዲሆን የሚደነግገውን የሕገመንግስቱ ድንጋጌ 65 አባላት ያሉት የምክርቤት አባላት ያለምንም  የድምጽ ልዩነት በሙሉ ድምጽ እንዲያልፍ ተደርጎ የዕድሜ ገደቡ እንዲነሳ ተደርጓል። ምክርቤቱ በሙሉ ድምጽ ይህን ሕግ ማፅደቁን ሳያንስ በወቅቱ ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ይህን ሕግ ቢጸድቅ ለጅቡቲ መረጋጋት ይበጃል ማለታቸውን አጀብ አሰኝቶ ነበር።

የጅቡቲውፕረዚደንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ
የጅቡቲውፕረዚደንት እስማኤል ኦማር ጉሌህምስል፦ Simon Maina/AFP/Getty Images

የጠንካራ ተፎካካሪ እጦት


ጅቡቲ ምርጫ አንድ ብላ አሁን ስድስተኛ እስክትደርስ ድረስ በሚደረጉ ምርጫዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ያለመኖር ፕረዚደንቱ፤ የስልጣን ዘመናቸውን  ሕገመንግስቱን እያሻሻሉ ጭምር እንዲቀጥሉ እንዳስቻላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ትላንት የተካሄደው ፕረዚደንታዊ ምርጫም አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙትን እስማኤል ኦማር ጉሌህን ስልጣን የሚያስቀጥል እንደሆነ መቀመጫውን በናይሮቢ ኬንያ ያደረገው የአለምአቀፍ የስልታዊ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሐሰን ካኔንጂ ለአዲስ አበባው ወኪላችን እስክንድር ፍሬው ገልጸውለታል።

«ብዙ ለውጥ የማይኖርበት ምክንያት፣ከአሁኑ ፕሬዝደንት ጋር የሚወዳደሩት ተቀናቃኝ መሐመድ ፋራህ፣ በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ከስርዓቱ ጋር የሚስማሙ ሆነው መገኘታቸው ነው።ሰለዚህ ከትክክለኛና ፉክክር ካለበት ምርጫ ይልቅ እንደ የይስሙላ ምርጫ እየታየ ነው።»
የአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ብዙም ያልሳበውየጅቡቲ ምርጫ የምረጡኝ ዘመቻውም ያን ያሕል በፖሊሲ ልዩነቶች ላይ ተመስርቶ ፍትግያ የነበረበት እንዳልነበረ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።ፕረዚደንት እስማኤል ኦመር ጉሌህ ባካሄዷቸው የምረጡኝ ዘመቻዎችም ስለሚያራምዱት ፖሊሲ፤ አልያም በፕረዚደንት ቢቀጥሉ ሊሰሩት ስለአሰቡት አዲስ ነገር ከመቀስቀስ ይልቅ የሐገሪቱ የደህንነት ስጋትና የሕዝቡን አንድነት አስፈላጊነት ላይ የተመሰረቱ እንደነበሩ ተነግሯል።

« ሁላችሆም! የምትከተሉት የፖለቲካ ፓርቲ ምንም ይሁን ምን ዋናው ነገር እኛ ጅቡቲያውያን ነን። እና ወንድማማቾችና እህትማማቾች ነን፤ ልናብር ይገባል፤ አንድነት!  አንድነት!»
አንድ መራጫ በበኩሉ እኛ የምንመርጠው ኢስማኢል ኦማር ጉሌህን ነው ሲል ተደምጧል። የስሞቻቸው የመነሻ ፊደላትን በማሳጠር IOG እያለ፤ ደግሞም እንደስልጣናቸው ሁሉ ረዥም ዕድሜም እየተመኘ።

«እኛ በኢትዮጵያና ሶማሊያም ጭምር እንኖራለን። ይሁንና በነዚያ አገራት ጦርነት አለ። በኛ ሐገር ግን አንድነት አለ። ፕረዚደንታችንን እወዳቸዋለሁ፤ IOG ብለን ነው አቆላምጠን የምንጠራቸው። ረዥም ዕድሜ ለ IOG ፣ረዥም ዕድሜ ለ IOG! ረዥም ዕድሜ ለ IOG!»

የጅቡቲ ወደብ
የጅቡቲ ወደብምስል፦ Solomon Muche/DW

«አዲስ ነገር አይኖርም»
 
የአለምአቀፍ የስልታዊ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሐሰን ካኔንጂ በጅቡቲ ጠንካራ ተፎካካሪ አለመኖር አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይገልጻሉ። የፖለቲካ ምሕዳሩ መጥበብ ብቻ ሳይሆን ይገዳደራሉ የሚባሉ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በማባበል ጭምር ከተፎካካሪነት ወደ ተባባሪነት እንዲለወጡ እንደሚደረግ በማከል።

"በጂቡቲ ጠንካራ ተፎካካሪዎች አለመኖራቸው ከቅርብ ጊዜ ታሪክ የመጣ ነው-አንደኛ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉትን በማባበል ተባባሪ የማድረግ፣ሁለተኛው ደግም ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲኖር የሚያደርግ ምህዳር ያለመፍጠር" በማለት አአብራርተዋል ።
በጅቡቲ የምርጫ አካሄድና ውጤት በተለይ ወጣቶች በሐገራቸው ንቁ ተሳትፎ እንዳያደርጉ እንዳገዳቸው ይነገራል። አዲስ ነገር ላይመጣ፤ አዲስ ገፅ፣ አዲስ ሐሳብ፣ አዲስ ፖሊሲ ላይኖር የነሱ ተሳትፎ የሚፈይደው የለምና በሐገራቸው ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎታቸው እምብዛም ቢሆን አያስደንቅም በማለት የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። ሐሰን ካኔንጂም በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ይመስላል።

«ወጣቶች ትርጉም ባለው መልኩ በፖለቲካ ሂደቱ እንዳይሳተፉ እድላቸውን ይዘጋል።ለተቀሩት የጂቡቲ ዜጎችም እንደዚሁ።ይህ ደግሞ በጂቡቲ ብቻ ሳይሆን በቀጠናው ሁሉ በመንግስት ላይ ያለውን የተወሰነ ተስፋ መቁረጥ ይጨምራል»
የዩናይትድ ዴሞክራቲክ ማዕከል የተባለው ፓርቲ ሊቀመንበር መሐመድ ፋራሕ ስማትራ ከጉሌህ ጋር ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል። የአገሩ ፖለቲከኞች መናጆ ይሏቸዋል። ለውጥ ለማያመጣና አሸናፊው ማን እንደሆነ ከወዲሁ ለሚታወቀው ምርጫ ለተሳትፎ ያህል የሚወዳደሩ መሆናቸውን ለመግለፅ። የፕረዚደንት ኦማር ጉሌህ አሸናፊነት የማያጠራጥር ቢሆንም በምክርቤት አባላት ምርጫ ለውጥ የሚኖር ከሆነ ግን ምናልባት የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ተፅዕሮ ሊፈጥር እንደሚችል ሐሰን ካኔንጂ ይገልጻሉ።

«አሁን ያሉት ፕሬዝደንት ተመልሰው የሚመረጡ በመሆናቸው፣በአፍሪካ ቀንድ እየሆነ ያለው ነገር ትርጉም የለውም።አሁን ያለውን ነገር እንደሚያስቀጥሉ ይጠበቃል።ያም ሆኖ ቀጠናው ይሄንን ምርጫ ይከታተላል።ምክንያቱ ደግሞ በተለይ በፓርላማ ደረጃ ለውጥ የሚኖር ከሆነ፣ በመንግስት ፖሊሲና ከፕሬዝደንቱ አቅራቢያ ባሉ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማድረግ ይችላል»
እስማኤል ኦማር ጉሌህ በአለፈው የ2021 ምርጫ «99 በመቶ የሕዝቡ ድምጽ አግኝተው» መመረጣቸውን ተገልጾ ፕረዚደንትነታቸውን ቀጠለ። ሕገመንግስቱንና የምርጫ ሕጉን ያሻሻሉት ጉሌህ አሁን ጥያቄው በምርጫው ይሸነፋሉወይ? ሳይሁን ስንት የመራጮች ድምጽ አግኝተው የፕረዚዳንትነት ወንበራቸውን ያስቀጥላሉ? የሚል ሆኗል። 

የጅቡቲው ፕረዚደንት ኦማር ጉሌህ
የጅቡቲው ፕረዚደንት ኦማር ጉሌህምስል፦ Mohammed Dhaysane/AA/picture alliance

የደቡብ አፍሪካ ሐገራት እየጨመረ የመጣውን የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ለመቆጣጠር እየታገሉ ነው። 


በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳንባ ነቀርሳበከፍተኛ ሁኔታ ከተስፋፋባቸው አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካና ሞዛምቢክ ይጠቀሳሉ። በሁለቱም ሐገሮች  አሁንም  በሽታው የሚያስከትለውባ ስቃይና ሞት ትርጉም ባለው መልኩ እንደቀጠለ ነው። ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ በሽታውን ለመከላከልና ለማከም የሚደረጉ ጥረቶች  በተወሰነ መጠን እድገት ቢያሳይም በሽታው የሚያስከትለውን  ሞትን ለመቀነስ ግን ከዚህ የበለጠ ብዙ መስራት  ያስፈልጋል ።

የሳምባ ነቀርሳ የቤተ ሙከራ ምርመራ
የሳምባ ነቀርሳ የቤተ ሙከራ ምርመራምስል፦ Alfredo Zuninga/AFP

ደቡብ አፍሪካ


ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳንባ ነቀርሳ ከተስፋፋባቸው ሐገሮች ስሟ በፊተኛው ረድፍ ትጠራለች። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2023 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ54,000 እስከ 56,000 የሚደርሱ ሰዎች በበሽታው የሞቱ ሲሆን  በየዓመቱ 270,000-326,000 አዲስ ሰዎች በበሽታው ይያዛሉ ።
በሞዛምቢክ  የሚንቀሳቀሰው አንድ ምግባረሰናይ ድርጅት ከፍተኛ የጤና ባለሙያ የሆኑት ሄለን ሃልስትሮም ደቡብ አፍሪካ የሳንባ ነቀርሳ ስርጭትን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት የተሻለ ስኬት እንዳታመጣ ዕንቅፋት የሆናት የኤች አይ ቪ ስርጭት እንደሆነ ይናገራሉ። 
ደቡብ አፍሪካ  በዓለም  ከፍተኛ የሳንባ ነቀርሳ ሥርጭት አለባቸው ከሚባሉ  30 ሐገራት አንዷ ነች። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንደሚባለው በሐገሪቱ ከተመዘገቡ የሳምባ ነቀርሳ በሽተኞች 54 በመቶው የኤች አይ ቪ  ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሲሆን፤ ይህም ሕክምናውን ውስብስብ እንዳደረገው ይነገራል። 
የጤና ባለሙያዋ ሃልስትሮም  እንደሚሉት «ከኤች አይ ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሕክምናውን ካልተከታተሉ በሽታውን የመከላከል አቅማቸው ይቀንሳል፤ በዕለታዊ እንቅስቃሴያቸው ለሳንባ ነቀርሳ የሚጋለጡበት ሁኔታ ሲፈጠር በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው እጅግ ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም በደማቸው የኤች አ ቪ ቫይረስ ስላለባቸው በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ስለሚዳከም።» በማለት ያስረዳሉ።
 
 ሞዛምቢክ


ሞዛምቢክ ከባድ የሳንባ ነቀርሳ በሽታም ሥርጭት ካለባቸው ሐገሮች ሌላኛዋ ናት። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2023 ብቻ ወደ 112,000 የሚጠጉ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ እንደተጠቁ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከነዚህ 17,400 ያህሉ ከበሽታው እንዲፈወሱ የሚያስችላቸውን የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ችግር እንደገጠማቸው ይታወቃል።  በሞዛምቢክ «ገዳይ» ተብለው ከተዘረዘሩት በሽታዎች አንዱ የሳንባ ነቀርሳ ነው። እንደ ደቡብ አፍሪካ ሁሉ በሞዛምቢክም በተለይም የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ሰዎችን ክፉኛ እያጠቃ እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።
በሞዛምቢክ የሳንባ ነቀርሳ ሥርጭትን ለመከላከል ሌላኛው ዕንቅፋት ተብሎ የሚጠቀሰው በተለይ በገጠር አካባቢ የጤና መሰረተ ልማቶች ባለመስፋፋታቸው በሽታው ያለባቸውን በአግባቡ መለየት አለመቻሉ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የሳምባ ነቀርሳ የራጂ ውጤት መመልከቻ
የሳምባ ነቀርሳ የራጂ ውጤት መመልከቻምስል፦ Luke MacGregor/REUTERS

ሥር የሰደደ የተመጣጠነምግብ እጥረት

በደቡብ የአፍሪካ አህጉር የሚገኙት ነዋሪዎች በየጊዜው በሚያጋጥም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችና የፖለቲካ ብልሽውና ምክንያት ሥር የሰደደ ድህነት ተንሰራፍቷል። በዚህም ምክንያት ዜጎች ለረሐብ ይጋለጣሉ። በደቡብ አፍሪካ 23.2 ሚልዮን ሰዎች ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖሩ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2025 የወጣው መረጃ ያመላክታል። ይህም ከአጠቃላይ ሕዝቧ 37.9 በመቶ ከድህነት ወለል በታች ይኖራል ማለት ነው። በተለይም የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የሚገባቸው የሳንባ ነቀርሳ ታማሚዎችና  የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ ስለማያገኙ በሽታውን የመከላከልና የማከም ሥራውን ውስብስብ እንዳደረገው የሕክምና ከፍተኛ ባለሙያዋ ሄለን ሃልስትሮም ያስረዳሉ።
« የሳምባ ነቀርሳን ለመከላከልና ለማከምበምናደርገው ጥረት ከፍተኛ ችግር ገጥሞናል። ይኸውም ታማሚዎች የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የማይችሉ ዝቅተኛ የሕብረተሰብ ክፍል በመሆናቸው ነው። ይህ የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት በድህነት ሥር የሚኖሩ የሳንባ ነቀርሳ ታማሚዎች በቀላሉ እንዲሞቱ ምክንያት ሆኖብናል። ለምን ቢባል የተመጣጠነ ምግብ ካላገኙ ሰውነታቸው በሽታን የመከላከልና  የመቋቋም አቅም ስለሚያጣ።» 

መድሃኒቱን መላመድ፣ አድሎና ማግለል


ከኤች.አይ.ቪና ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ባሻገር  የሳንባ ነቀርሳ ሥርችትን ካወሳሰቡ ሌሎች ጉዳዮች፤ ታማማሚዎች የሚሰጣቸው ሕክምና በተገቢው መንገድ ስለማይከታተሉና የሚሰጣቸውን የረዥም ጊዜ መድሃኒት በተደጋጋሚ ስለሚያቋርጡት በሽታውን ለማከም ቀድሞ ሲሰጥ የነበረውን መድሃኒትን ይላመዳል። በሽታው መድሃኒቱን ሲለማመድ ይህን ለማከም የሚደረጉ የሕክምና ጥረቶች እጅግ ከማወሳሰቡም በላይ በሽታውን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት እያመከነባቸው እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 
የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች የሚደርስባቸው አድሎና መገለልም ሌላ የሕክምና ሂደቱን ከሚያወሳስቡ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ታማሚዎች ከሕብረተሰቡ አንዳንዴም ከጤና ባለሙያዎች ሳይቀር የሚደርስባቸው አድሎና መገለል ታማሚዎቹ ሕክምናቸውን በደንብ እንዳይከታተሉና የተሰጣቸውን የረዥም ጊዜ መድሃኒት በአግባቡ ጨርሰው እንዳይድኑ ያግዳቸዋል። ይህ በራሱ በሽታውን ለማከም ቀድሞ ሲሰጥ የነበረውን መድሃኒት እንዲለመድውና ሕክምናውን እንዲወሳሰብ እንደሚያደርገው የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች እራሳቸውን ገልጠው ወደ ሕክምና ተቋማት እንዳይሄዱ ስለሚያደርጋቸው ለበሽታው ሥርጭት ከፍተና አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ ነው የጤና ከፍተኛ ባለሙያዋ ሄለን ሃልስትሮም የሚገልጹት። 
«የሳንባ ነቀርሳ በሽታ በቀላሉ ሊከላከሉትና ከያዘም አልፎ ሊድን የሚችል ቢሆንም ታማሚዎች በሚደርስባቸው አድሎና መገለል ምክንያት ወደ ህክምና ተቋማት እንዳይሄዱ፤ የሄዱትም ሕክምናቸውን እስከመጨረሻ ተከታትለው እንዳይጨርሱ ያደርጋቸዋል» በማለትም ያክላሉ።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ሰዎች ስለ ሳንባ ነቀርሳ ምልክቶች ያላቸው እውቀት ውስን በመሆኑ ወደ ሕክምና ሳይሄዱ ሕይወታቸው ያልፋል። በመሆኑም የሳንባ ነቀርሳ እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ በሽታው ከያዘን ደግሞ ሕክምናውን እንዴት መከታተል እንደሚገባ የማንቅያ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል።

የሳምባ ነቀርሳ የምርመራ አገልግሎት
የሳምባ ነቀርሳ የምርመራ አገልግሎትምስል፦ Alfredo Zuninga/AFP

ደቡብ አፍሪካ የጀመረችው የማንቃት ሥራ


በደቡብ አፍሪካ  አክቲቪስቶች ፣ የጤና ባለሙያዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት የሳንባ ነቀርሳ ምርመራና ሕክምናን ለማበረታታት የተጠናከረ ዘመቻ እያደረጉ ይገኛል። የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕረዚደንት ፓውል ማሻትሊ የሳንባ ነቀርሳ ሥርጭት በየአመቱ እየቀነሰ አስፈላጊው ውጤት እስኪመጣ ድረስ ሕብረተሰቡን የማንቃት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
«ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲመሩ እናበረታታቸዋለን። የሳንባ ነቀርሳ ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ እንዲሄድ የጀመርነውን የማንቃት ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን።» ነው ያሉት።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ሁለቱም አገሮች ለሳንባ ነቀርሳ በቂ መረጃ የሚሰጡ ሰዎችን ይበልጥ ማሠልጠን ይኖርባቸዋል። የሞዛምቢክ ነዋሪ የሆኑት ሞዴስታ አንቶኒዮ የ67 ዓመት አዛውንት ናቸው። አሳቸው ምንም እንኳን የሕክምና ዕውቀቱ ባይኖራቸውም የማሕበረሰብ መሪ በመሆናቸው፤ የማሕበረሰቡ አባላት ስለ ሳንባ ነቀርሳ የሚመለከቱ መረጃዎች ከባለሙያዎች እንዲያገኙ፤ በበሽታው መያዝ አለመያዛቸውን ለማወቅ ምርመራ እንዲያደርጉ፤ አለባቸው ከተባሉም ያለምንም መሸማቀቅ ሕክምናቸውን እስከመጨረሻው እንዲከታተሉ በመምከር የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በወጣቶች ዘንድ የማንቃት ሥራው በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ተደርጓል። ወጣቶቹ በእጅ ስልካቸው ስለበሽታው አስፈላጊውን ትምሕርት እየተሰጣቸው ይገኛል፤ በመሆኑም የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ ነው ይላሉ የጤና ባለሙያዋ ሄለን ሃልስትሮም።
«ከፍተኛ መሻሻል እየታየ ነው። ይህ ደግሞ በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚሰጡ ትምሕርቶች ተቀባይነት እያገኙ በመምጣታቸው ነው። ስለዚህ ማሕበረሰቡ በባለቤትነት ስሜትና አካባቢያዊ መፍትሄዎችንም ሥራ ላይ በማዋል የሳንባ ነቀርሳን መቀነስ ብሎም ማጥፋት ያስችላል።»

ክላድዚ አይዛክ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ፀሐይ ጫኔ