1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2015

በሸገር ከተማ የመስጊዶች ፈረሳ በመንግስት ኃላፊዎች በኩል የተፈጸመው ተግባር ስህተት መሆኑ እንደታመነበት ተገለጸ ። ብርቱ ተቃውሞ አስከትሎ ለዐርብ ጸሎት የወጡ ሙሊሞችን ሕይወት የቀጠፈው የመስጊዶች ፈረሳ ያጫረውን ውዝግብ ለመቋጨት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋር ትናንት መወያየቱ ተገልጿል ።

https://p.dw.com/p/4SLSd
Der äthiopische Rat für islamische Angelegenheiten Addis Ababa
ምስል Seyoum Getu Kori Addis Ababa

የተፈጸመው ስህተት መሆኑ እንደታመነበት ተገልጿል

በሸገር ከተማ የመስጊዶች ፈረሳ በመንግስት ኃላፊዎች በኩል የተፈጸመው ተግባር ስህተት መሆኑ እንደታመነበት ተገለጸ ። ብርቱ ተቃውሞ አስከትሎ ለዐርብ ጸሎት የወጡ ሙሊሞችን ሕይወት የቀጠፈው የመስጊዶች ፈረሳ ያጫረውን ውዝግብ ለመቋጨት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋር ትናንት መወያየቱ ተገልጿል ። በውይይቱ ላይ ስለተነሱ ጉዳች እና ስለተቀመጠው እልባት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል ። 

በሸገር ከተማ አስተዳደር የመስጊዶች ፈረሳ የፈጠረውን ቀውስ ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኃላፊዎች ጋር ትናንት ከከሰአት ጀምሮ እስከ ማምሻው ሰፊ ውይይት ማድረጉ ተነግሯል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የመሩት ልዑክ ቡድን የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በመገኘት ከአቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር እንዲሁም የኦሮሚያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በተገኙበት በተደረገው ውይይት፤ የመስጊዶች ፈረሳን ተከትሎ በተፈጠረው የተቃውሞ ሂደት «በሙስሊሙ ላይ የደረሰው በደል» በስፋት ተዘርዝሮ ቀርቦ በመንግስት ኃላፊዎች በኩልም የተፈጸመው ተግባር ስህተት መሆኑ ታምኖበታል ተብሏል ።

በዚሁ ውይይት ስለተነሱ ነጥቦች እና ስለተቀመጠው መፍትሄው በማስመልከት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋን ጨምሮ የተለያዩ የሃይማኖቱ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በቅርቡ በሸገር የመስጊዶች መፍረስን በመቃወም በአዲስ አበባ በተለይም በአንዋር መስጊድ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ቢያንስ የአምስት ሰዎች ህይወት ያለፈበትን ሂደት አሳዛን ያሉት ሼህ ኢብራሂም፤ አሁን ግን ለተፈጠረው ችግር እልባት መመላከቱን ጠቅሰዋል፡፡ “ተቀራርቦ በመነጋገር ለችግሩ መፍትሄ ተገኝቷል፡፡”

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳነቱ የአደረጃጀት እና ማህበራዊ ጉዳዮች ተጠሪ ኡስታዝ አህመድን ጀበል፤ አምስት ሰዓታት የፈጀ ባሉት ሰፊ ውይይት በሸገር ስለፈረሱት መስጊዶች ጉዳይ ዝርዝር መረጃ መነሳቱንም ባነበቡት መግለጫ አስረድተዋል፡፡ “የሸገር ከተማ አስተዳደር ከፕላን ውጪ ተሰርተዋል ያላቸውን መስጂዶች ለማፍረስ ሲነሳ የሚመለከተውን የእስልምና ጉዳይ ተቋማት አለመወያየቱና የቀረበለትን የውይይት ጥያቄ ችላ ማለቱ ተገቢ አለመሆኑ በቅሬታ ቀርቧል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ የሸገር ከተማ መስጂድ ፈረሳ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩት ሁኔታዎች እጅጉን መጎዳቱንና ማዘኑን በማብራራት ተገቢውን ካሳና የሞራል ህክምና እንደሚያስፈልገውም ተጠቅሷል፡፡”

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫምስል Seyoum Getu Kori Addis Ababa

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ሆነ ህዝበ ሙስሊሙ በሀገሪቱ የትኛውም ክፍል ለሚከወነው ልማት ድጋፍ እንጂ ተቃውሞ የላቸውም ያለው መግለጫው፤ በሸገር ከተማ ያለፕላን እና ሕጋዊ መሰረት ተሰርተዋል በሚል የፈረሱ መስጊዶች 22 በመድረሱ ለህዝበ ሙስሊሙ የመስጂድ ጥያቄን በአፋጣኝ መመለስ እንደሚያሻውም ጠቅሷል፡፡ መግለጫው “የጸጥታ ሃይሎች ንጹሃን ላይ መተኮሳቸውም የሚኮነን ተግባር ነው” ሲል ወቅሶ፤ “አስቀድሞ መነጋገር እየተቻለ እስከ ትናንት በቂ ውይይት ባለመደረጉ ችግሩ መንግስትና ህዝብ መካከል ቅሬታ ፈጥሮ እስከ ሰው ሕይወት መጥፋት አድርሷል” ብሏል፡፡ 

መግለጫው ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተነሱ ሃሳቦችን በማስመልከትም፤ የፊታችን ሐምሌ በሚጸድቀው የከተማዋ ፕላን ላይ መጅሊሱን በማማከር ደረጃቸውን የጠበቁ መስጊዶች እንደሚሠሩ፣ ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲና ግዙፍ ማዕከላዊ መስጊድን ጨምሮ መንፈሳዊ ማዕከላት እንደሚኖሩ፣ ነዋሪ ባለባቸው አካባቢዎችም ጊዜያዊ የመስገጃ ቦታዎች እንደሚዘጋጁ ከመንግስት በኩል ቃል መገባቱ ተነግሯል። ነገር ግን ሸገር ከተማ ከ20-30 ሚሊየን ነዋሪዎች ያላት መሆኗ፤ ግንባታዎችም በዘመናዊ ፕላን ብቻ የሚካሄድባት እንደመሆኑ ሕገወጥ ግንባታን መከላከል ብሎም በሕገወጥ የተገነቡትንም ማፍረስ እንደሚቀጥልና በሂደቱም የእምነት ተቋማት ተባባሪ እንዲሆኑ መጠየቁ ተነስቷል፡፡ 

በሸገር ከተማ ውስጥ ካሉ 800 ቤተእምነቶች 656 ያህሉ ከፕላን ውጪ የተሰሩ በመሆናቸው፤ የኦሮሚያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቅሙን አጠናክሮ በውይይት የእምነት ተቋማቱ ራሳቸው ማፍረስ ያለባቸውን እንዲያፈርሱ እንጂ ከአሁን በኋላ መንግስት በራሱ ማፍረሱን እንደሚያቆምም ከስምምነት መደረሱ ተነግሯል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተነሳው አለመረጋጋት የታሰሩ ሙስሊሞች እንዲፈቱ ቀጣይ ውይይቶች ከፀጥታ ተቋማት ጋር እንደሚደረጉም ተጠቅሷል፡፡ በሸገር ከተማ በምትክ በሚሰሩ መስጊዶች “የሸሒዶች መስጂድ” በሚል መታሰቢያው ባለፉት ሁለት ሳምንታት ህይወታቸው ባለፈው ሙስሊሞች እንደሚደረግም ነው የተገለጸው፡፡ ተጎጂዎችም እንዲረዱ ጥሪ ቀርቧል፡፡ 

ህዝበ ሙስሊሙ ይህንን የመፍትሄ ሂደት ከሚያስተጓጉሉ አካሄዶች ተቆጥቦ ነገሮች ወደነበሩበት መረጋጋት ይመለሱ ዘንድ ጁሙዓን የመሳሰሉ የስብስብ አጋጣሚዎችን መሪ ድርጅት ባስቀመጠው አቅጣጫ ብቻ እንዲካሄዱ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ ናቸው፡፡ “በግልም ሆነ በቡድን በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በሌሎች የመገናኛ መንገዶች የሚኖሩን ሂደቶች በተቻለ መጠን መፍትሄውን ተከታትሎ የማስፈጸም መንፈስ ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ እና ሙስሊሙን ወዳልሆነ አቅጣጫ መምራት ለሚፈልጉ አካላት በር የማይከፍት መንገድ እንከተል። የመሪ ተቋማችንን ትእዛዝ እና የትግበራ አቅጣጫ መከተል በዚህ መሰል የቀውስ ወቅቶች እጅግ አንገብጋቢ እና ብቸኛ አማራጭ ነው” ብለዋል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ