1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውዝግብ ያስነሳው የሸገር መስጊዶች ፈረሳና መፍትሄው

ሰኞ፣ ግንቦት 28 2015

በአዲስ አበባ ዙሪያ ሸገር ከተማ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ተገነቡና የከተማዋን ማስተር ፕላን ያልጠበቁ በሚል ቢያንስ እስካሁን 19 መስጊዶች መፍረሳቸው ተነግሯል፡፡ ይህን ተከትሎም ለሁለት ተከታታይ የጁማ ሶላት ሳምንታት በአዲስ አበባ በታላቁ አኑዋር መስጊድ በተነሳው አለመረጋጋት ቢያንስ የ5 ሰዎች ህይወት ተቀጥፎ በርካቶች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4SDUv
Äthiopien | Feierlichkeiten zu Eid al-Fitr in Sheger
ምስል Seyoum Getu

”ቢያንስ አሁን ላይ የሚከናወነው የመስጊዶች ፈረሳ ቀንሷል፡፡”

በአዲስ አበባ ዙሪያ እንደ አዲስ በተመሰረተው ሸገር ከተማ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ተገነቡና የከተማዋን ማስተር ፕላን ያልጠበቁ በሚል ቢያንስ እስካሁን 19 መስጊዶች መፍረሳቸው ተነግሯል፡፡ ይህን ተከትሎም ለሁለት ተከታታይ የጁማ ሶላት ሳምንታት በአዲስ አበባ ታላቁ አኑዋር መስጊድ በተነሳው አለመረጋጋት ቢያንስ የ5 ሰዎች ህይወት ተቀጥፎ በርካቶች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ችግሩ በቀጣይ እልባት እንዲያገኝ ደግሞ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በተዋቀረው ኮሚቴ እና በመንግስት በካከል ንግግሮች እንደቀጠሉ ተሰምቷል፡፡

የክትትል እና ሕግ ጉዳዮች አስፈጻሚ ኮሚቴ በሚል ከፌዴራል፣ ከኦሮሚያ እና ከአዲስ አበባ መጅሊሶች በተውጣጡ ዘጠኝ አባላት የተዋቀረው ኮሚቴ በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ተቋቁሞ ከሚመለከተው የመንግስት አካላት ጋር መነጋገር ከጀመረ ሳምንት አልፎታል፡፡ የዚህ ኮሚቴ አባልና የኮሚቴው ቃል አቀባይ ሼህክ አብዱላኪም ሃጂ ሁሴን በዳሶ በተለይም ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት እስካሁን በሸገር ቢያንስ 19 መስጊዶች መፍረሳቸው እሙን ነው ብለዋል፡፡ “ከአንድ ሳምንት በፊት መግለጫ ካወጣን በኋላ ሙሉ በሙሉ ቆሟል ብለን በእርግጠኝነት ለመናገር ባንደፍርም ቢያንስ አሁን ላይ የሚከናወነው የመስጊዶች ፈረሳ ቀንሷል፡፡”

Äthiopien | Feierlichkeiten zu Eid al-Fitr in Sheger
የሸገር ከተማ ምዕመናንምስል Seyoum Getu

ኮሚቴው ከተዋቀረ በኋላ ለችግሩ የሰላም እልባት ለመስጠት ብዙ ርቀት ሄደናል ያሉት ሼህክ አብዱልሃኪም፤ “ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ከሚመለከተው አካል ጋር ንግግር ተደርጓል በሚል ያሰራጨው መረጃ ስህተት በመሆኑ በዚያ አዝነናል፡፡ ማናችንም አላነጋገሩንም፡፡ አሁን ግን በዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለን አፋችንን ሞልተን የምንናገረው ነገር ባይኖርም ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር የምናደርገውን ውይይት ቀጥለናል፡፡”

በንግግር ሂደቱ ስለተነሱት ቅሬታ እና የሂደቱን ተስፋ ሰጪነት በማስመልከትም፡ “አንዋር መስጊድ ላይ የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም ብለን ቅሬታችንን አቅርበናል፡፡ እርምጃ የወሰደው አካልም እንዲፈተሸልና እና የተጎዱትም እንዲካሱ ጠይቀናል፡፡ የፈረሱ መስጊዶች ፈንታ መተኪያ እንዲሰጥ እንዲሁም ይፈርሳሉ ህገወጥ ናቸው የተባሉም ህዝበ መስሊሙ ራሱ እንዲያነሳቸውና መተኪያ ቦታ ላይ እንዲገነባ የሚሉትንም ጥያቄዎች አቅርበን እየመከርንበት ነው” ብለዋል ሼህ አብዱልሃኪም፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ