1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስጊድ ፈረሳ በሸገር ከተማ

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015

የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ እስካሁን ቢያንስ ሰባት መስጊዶች በመንግስት ፈርሶብኛል ሲል አማረረ፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተዋቀረው በሸገር ከተማ ፈርሷል ያለውን መስጊዶች በማስመልከት ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በደብዳቤ ማመልከቱንም አሳውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/4RjlG
Äthiopien Stadt Sheger hat ersten Bürgermeister gewählt
ምስል Seyoum Getu/DW

በሸገር መስጊዶች እየፈረሱ ነው መባሉ

 

የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ እስካሁን ቢያንስ ሰባት መስጊዶች በመንግስት ፈርሶብኛል ሲል አማረረ፡፡

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተዋቀረው በሸገር ከተማ ፈርሷል ያለውን መስጊዶች በማስመልከት ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በደብዳቤ ማመልከቱንም አሳውቋል፡፡ የምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ ሼህ ሁሴን ሀሰን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት እስካሁን ቀጥሏል ባሉት የመስጊዶች ፈረሳ ቢያንስ ከ10 በላይ መስጊዶች መፍረሳቸው አሳስቦናል ብለዋል፡

የሸገር ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በየትኛውም አይነት ግለሰብም ሆነ ተቋም ስም ተገንብቶ ለሚፈርሱ ግንባታዎች ብቸኛው መስፈርት ህግን የመጠበቅ አለመጠበቅ ጉዳይ ነው ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ውስጥ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በጻፈው ደብዳቤ በሸገር ከተማ ውስጥ ይከናወናል የተባለው የመስጊዶች ፈረሳ ባስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል፡፡ “በቅርቡ ሸገር በሚል ስያሜ በተዋቀረው ከተማ ውስጥ በህገወጥ መንገድ የተገነቡ በርካታ መስጊዶች ፈርሰውብናል” ሲል ነው ምክር ቤቱ አቤቱታውን ያቀረበው፡፡ ደብዳቤው አክሎም የመስጊዶች መፍረስ የከተማ አስተዳደሩ “በህገወጥ መንገድ ነው የተገነቡ” ስላለ ብቻ በቀላሉ የሚተው ሳይሆን ጉዳዩ የሃይማኖቱ ተከታዮች የህልውና ጉዳይ ነውም ብሏል፡፡ ተግባሩ እንዲገታ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳት አቶ ሽመልስ አብዲሳም በደብዳቤ ተጠይቀው መልስ ሳይሰጡበት መቅረታቸው ተብራርቷል፡፡

በሸገር ከተማ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ተገነቡ በሚል ከፈረሱ ከ10 በላይ መስጊዶች አምስቱ በሰበታ ሁለቱ ደግሞ በቡራዩ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን የሰጡን የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ ሼህኽ ሁሴን ሀሰን፤ በለገጣፎ እና ኮዬፈጨ ክፍለከተሞችም መስጊዶች መመፍረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ “እስካሁን የፈረሱ መስጊዶች 15-16 ይደርሳሉ፡፡ ባለፈው ደብዳቤ ከጻፍንም በኋላ ፈረሳው ቀጥሏል፡፡ ዛሬም ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተናል፡፡ ለጊዜው ፈረሳውም ጋብ ያለ መስሏል፡፡”

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠየቀው የሸገር ከተማ አስተዳደር የእምነት ተቋማትን የመዳፈር እና የመጉዳት ዓለማ ኖሮት ሳይሆን ህጋዊነትን ብቻ መስፈርት አድርጎ የሚከናወን ስራ ይላል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሳ ደጀኔ በተለይም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረበውን ቅሬታ አስመልክተው ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡን መልስ፡ “ባጠቃላይ ለምናፈርሳቸው ቤቶች መስፈርታችን ህጋዊ ግንባታ ነው አይደለም የሚል ነው፡፡ ግንባታውን የፈጸመው አካል መሬቱን እንዴት አገኘ፣ ግንባተውንስ በምን መስፈርት ነው የገነባው፣ የግንባታ ፈቃድ አግኝቶበታል ወይ የሚል ነው መርህው፡፡ እነዚህ

የምናፈርሳቸው ግንባታዎች የተከናወኑት የከተማን ፕላን ባልጠበቀ መልኩ፣ ለግንባታ ራሱ ባልተፈቀዱ ተራራዎች፣ ወንዝ ዳሮች እና አንዳንዴም ለመኖሪያ መንደርነት የተፈቀዱ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ እነዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ነው ግንባታው የማንም ይሁን የማን የምናፈርሳቸው፡፡”

እነዚህ መስጊዶች ሲፈርሱ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ የተሰጠባቸው እና ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የፈረሱ መኖራቸውንም ያመለከቱት የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ ሼህ ሁሴን፤ መስጊዶች ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ሃይማኖታዊ ተቋማት እንደመሆናቸው በዘመቻ ማፍረስ ያልተገባ ነበር ብለዋል፡፡ “ሲያፈርሱ እንደተቋም አላወያዩንም፡፡ ለውይይት ገፍተን ስንሄድም እድሉን አልሰጡንም የመንግስት አካላት፡፡ እናቆማለን ብሉንም ከስር ፈረሳውን ቀጥለውበታል፡፡ እኛ እየጠየቅን ያለነውም፤ መስጊድ ማፍረስ እንዲቆም፣ የፈረሱም በከተማ አስተዳደሩ ወጪ መልሶ እንዲገነቡና ህዝበ ሙስሊሙ ይቅርታ እንዲጠየቅ ነው፡፡ ወደፊትም መፍትሄ ብለን የምናምነው ተነጋግሮ ችግሮቹን መፍታት ነው፡፡”

የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሳ ደጀኔ ግን የትኛውም ህገወጥ ግንባታዎች ለከተሞች እድገት አሉታዊ ሚና ያላቸው መሆኑን ከማህበረሱም ጭምር በውይይት ከመግባባት ላይ በመድረስ ነው ፈረሳው የሚከናወነው ሲሉ ሞግተዋል፡፡ “ህገወጥ ግንባታዎች የከተማ እድገትን ጎዱ መሆናቸው በመጀመሪያ ከማህበረሰቡ ጋር በተደረገው ውይይት ከመግባባት ተደርሶበታል፡፡ ይህ አካሄድ ተስተካክሎ ህጋዊነት መስፈን እንዳለበትም ተግባብተንበታል፡፡ ከእምነት መሪዎችም ጋር በጉዳዩ ተወያይተንበት ተግባብተናል፡፡ እነሱም ህግ መስፈን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ለእምነቶች የሚያስፈልጉ ቦታዎች ህግን በተከተለ መንገድ መቅረብ እንዳለበት የነሱ ጥያቄ እንደመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ይህን መመለስ ግዴታ አለበት፡፡”

በቅርቡ በአዲስ መልክ በተመሰረተው ሸገር ከተማ በህገወጥ መንገድ ተገነቡ የተባሉ የነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች ላይም መጠነሰፊ የማፍረስ ተግባር መከወኑ ይታወሳል፡፡

ስዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ፀሀይ ጫኔ