1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአፍሪካ አገራት በሰብዓዊ መብት ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን እንደማይተገብሩ ተገለፀ

እስክንድር ፍሬው
ዓርብ፣ ሚያዝያ 16 2018

የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈፀምባቸው አገራት ላይ የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች፣ በአባል አገራት እንደማይተገበሩ የፀጥታ ጉዳይ ተመራማሪዎችና ዲፕሎማቶች ተናግረዋል። አባል አገራት፣ከሕብረቱ ጋር ከመተባበር ይልቅ፣ ውሳኔው ከተላለፈበት አገር ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ጥቅም ያስቀድማሉ ብለዋል።

https://p.dw.com/p/5CmIF
የአፍሪካ ሕብረት በተለያዩ አገራት በሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ለመስራት መዋቅሮቹን ይበልጥ መጠቀም አለበት ተባለ
የአፍሪካ ሕብረት በተለያዩ አገራት በሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ለመስራት መዋቅሮቹን ይበልጥ መጠቀም አለበት ተባለምስል፦ Eskinder Firew/DW

የአፍሪቃ ኅብረት አባል አገራት አለመተባበር

በእንግሊዘኛ ምህጻረ ቃል አይ.ኤስ.ኤስ. ተብሎ የሚጠራው የፀጥታ ተቋም በኢትዮጵያ ከሚገኘው የኔዘርላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ሴሚናር ላይ የተናገሩ ተመራማሪዎችና ዲፕሎማቶች እንዳሉት፣ የአፍሪካ ሕብረት በተለያዩ አገራት በሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ለመስራት መዋቅሮቹን ይበልጥ መጠቀም አለበት። በአህጉሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ ግጭቶችና በሌሎችም ሁኔታዎች ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ መኾናቸውን የገለፁት ተሳታፊዎቹ፣ሕብረቱ በጉዳዩ ላይ ከመስራት አንጻር እንቅፋቶች እየገጠሙት መኾኑን ጠቁመዋል።

የተጠያቂነት አለመኖር

የአይ.ኤስ.ኤስ የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ፖል ሲሞን ሃንዲ ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት፣አባል አገራት ውሳኔዎችን ከመተግበር አንጻር የሚያሳዩት ትብብር አነስተኛ ነው።ሕብረቱ የመንግስታት ሕብረት መኾኑ፣ለዚህ አንዱ ምክንያት መኾኑንም ገልፀዋል። ውሳኔዎችን በማይተገብሩት ላይ ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል ። "አባል አገራት ውሳኔዎችን እንዲተገብሩ ማነቃቃት፣ ማሳመንና ማስገደድ ያስፈልጋል።የአንድ ድርጅት አባል የምትኾነው፣በሌሎች ላይ ተፈጻሚ የሚኾነው የድርጅቱ መመሪያ በአንተም ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ስትስማማ ነው።ይህ ማለት የሚወሰኑ ውሳኔዎች በሁሉም ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ ማለት ነው።በአፍሪካ ሕብረት ደረጃ ያለው ችግር ውሳኔዎችን አለመተግበር የግድ ተጠያቂነት አለማስከተሉ ነው" ብለዋል።

እናም መፈንቅለ መንግስት የሚካሄድባቸውን አገራት ከአባልነት ከማገድ በዘለለ፣በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ሕብረቱ ርምጃ እንደማይወስድ ኃላፊው አብራርተዋል። የአፍሪካ ሕብረት ራሱን መመርመር እንዳለበትም አስረድተዋል።

የአባል አገራት አለመተባበር

አገራቸው ለነጻነትና ለእኩልነት ያደረገችውን ጉዞ ምሳሌ በማድረግ የተናገሩት፣ በአፍሪካ ሕብረት የደቡብ አፍሪካ ምክትል ቀሚ ተወካይ ማቴኮ ኡርሱላ ሌትሲ፣ የትብብርን አስፈላጊነት አብራርተዋል። የደቡብ አፍሪካን አፓርታይድ ያስወገደው ፣የአፍሪካ አገራት የጋራ አቋም መያዛቸው፣ የተቀረውም አለም ማዕቀቦችን መተግበሩና ጫናዎችን ማድረጉ እንደኾነ ገልፀዋል።አሁን ግን በርካታ አገራት  የአፍሪካ ሕብረት  በአንድ አገር ላይ የሚያስተላልፈውን ውሳኔ ከመተግበር ይልቅ የሁለትዮሽ ጥቅማቸውን እንደሚያስቀድሙ ምክትል ተወካይዋ ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ አባል በሆነችበት የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ስር የተደራጀ የማዕቀብ ኮሚቴ መኖሩን ያስታወሱት ሌትሲ፣በአባል አገራት አለመተባበር ፈተና እየገጠመው መኾኑንም ለዶይቸ ቨለ በምሳሌነት አስረድተዋል። "የማዕቀብ ኮሚቴው፣በበርካታ አባል አገራት የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚቀርፉ ማዕቀቦችን ከመተግበር አንጻር ፈተና እየገጠመው ነው።የተወሰኑት መሠረታዊ ችግሮች ውሳኔውን በመተግበር ዙሪያ ያሉ ናቸው" በማለት ነው የገለፁት።

የአባል አገራት አለመተባበር እንደተግዳሮት
የአባል አገራት አለመተባበር እንደተግዳሮትምስል፦ Eskinder Firew/DW

የደቡብ አፍሪካዋ ዲፕሎማት እንዳብራሩት፣አገራት ከምንም በላይ ውሳኔው ወይም ማዕቀቡ ከሚመለከተው አካል ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያስቀድማሉ ። "የጉዘ እገዳ ማድረግ ወይም በባንክ ያለ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ከተፈለገ፣ይሄ መተግበር ያለበት በአለምአቀፍ ደረጃ ነው ።ነገር ግን አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ከኾነ፣ ማዕቀብ መጣል አሰቸጋሪ ይኾናል።ምክንያቱም አባል አገራት በሌሎች አገራት እየተፈፀሙ ባሉ  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ከማነጣጠር ይልቅ፣ ከአጋሮቻቸው የሚያገኙትን የኢኮኖሚ ጥቅም ያስቀድማሉ" ብለዋል።

የቅንጅት ችግር

የአፍሪካ ሕብረት፣ በአባል አገራት ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከታተልና ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ በቂ አደረጃጀቶችና መዋቅሮች እንዳሉት፣ በሴሚናሩ ላይ የተናገሩ የፀጥታ ተንታኞችና ዲፕሎማቶች አመልክተዋል።

ይሄም ኾኖ ግን በእነዚህ መዋቅሮች መካከል የቅንጅት ችግር እንደሚታይ ጠቁመዋል። የሕብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች አለመተግበርም ከዚሁ ከቅንጅት አለመኖር ጋር የተያያዘ መኾኑን፣ዶ/ር ፖል ሲሞን ሃንዲ ያምናሉ። "ዛሬ የምናየው ምንድን ነው፣የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቱ ውሳኔዎች ያስተላልፋል፣አንዳንዴም እነዚህን ውሳኔዎች ማስተላለፉን ይረሳና ከሁለት አመታት በኋላ ተመሳሳይ ውሳኔ ሊያስተላልፍ ይችላል-ከዚህ ቀደም ያስተላለፋቸው ሳይተገበሩ።ስለዚህ አሁንም ክፍተቱ ያለው በትግበራ፣በክትትልና የተወሰኑ ውሳኔዎችን በመገምገም ላይ ነው"" በማለት አብራርተዋል።

አይ.ኤስ.ኤስ በመባል  የሚታወቀው የጸጥታ ጥናት ተቋም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2023 ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፣የአፍሪካ ሕብረት  የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት እ.አ.አ. ከ2004 ጀመሮ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች 90 በመቶው ተግባራዊ አልተደረጉም።

እስክንድር ፍሬው

ሸዋዬ ለገሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ