1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ምርጫ

ኢሳያስ ገላው
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2018

በደቡብ እና ሰሜን ወሎ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ64 ሺህ በላይ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች በሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በሁለት ተቃራኒ ስሜቶች የታጀበ ሆኗል። ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ሕይወታቸው ለመመለስ ተስፋ የሰነቁ እንዳሉ ሁሉ ከድምፅ መስጠት ይልቅ የዕለት ጉርስ እና የመጠለያ ጥያቄ ሲሉ ቅሬታ ያሰሙም አሉ ።

https://p.dw.com/p/5Cxdh
ፎሮ ከማኅ,ር፦ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በከፊል
ፎሮ ከማኅ,ር፦ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በከፊልምስል፦ North Gondar Disaster Prevention Department

የዕለት ጉርስ ወይስ ምርጫ?

በደቡብ እና ሰሜን ወሎ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ64 ሺህ በላይ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች በሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በሁለት ተቃራኒ ስሜቶች የታጀበ ሆኗል። የተወሰኑት ምርጫውን ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ሕይወታቸው ለመመለስ እንደ ትልቅ ተስፋ ሲመለከቱት፣ ሌሎች ደግሞ ከድምፅ መስጠት ይልቅ የዕለት ጉርስ እና የመጠለያ ጥያቄ ቀዳሚ ሊሆንልን ይገባል ሲሉ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው።

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ምርጫ

ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተለያዩ የኢትዮጵያ  ክፍሎች ተፈናቅለው በደቡብ እና ሰሜን ወሎ ቁጥራቸው ከ64 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች እና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ይኖራሉ። እነዚህ ተፈናቃዮች በመጪው ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያም ያላቸውን ተስፋ እና ቅሬታ ያነሳሉ።

ተፈናቃዮቹ ባሉበት የመጠለያ ጣቢያ አካባቢ የመራጮች ምዝገባ ካርድ እንዲያወጡ እየተደረገ ቢሆንም፣ በመጠለያ ጣቢያዎቹ የሚገኙ ዜጎች ስለ ምርጫው ያላቸው አመለካከት በሁለት ጎራ የተከፈለ ሆኗል። "ይህ ምርጫ ነገአችንን የምናስተካክልበት፣ ወደ ቀደመ ሰላማዊ ኑሮ የሚመልሰንን መንግስት የምንመርጥበት ነው ይላሉ  የጃራ ካምፕ ነዋሪዉ አቶ ጀማል ሰይድ

"የተሻለ ሃሳብ ይዞ የቀረበን መርጠን ከዚያ በኋላ ካለንበት ችግር የሚያወጣን፣ የሚቻል ከሆነ ሙሉ ዋስትናውን ወስዶ ወደ ቦታችን ቢመልሰን... ያ የማይቻል ከሆነም ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ ሀገር ሆና ጸንታ ባለንበት ቦታ ላይ አማራ ክልል ላይ ነው ያለነው፣ የተሻለ የምንኖርበት ቦታ ላይ ወስዶ ገበሬውን በገበሬ፣ ነጋዴውን በንግድ፣ ባለሙያም ወይም የተማረ አካል ብዙ አለ እነዛም በየሙያ ዘርፋቸው በየስራ ገብተው እንዲህ ቢሉ አንድ ነገር ነው፤ ይህን ያመጣልናል ብለን ነው የምናስበው"

የዕለት ጉርስ ወይስ ምርጫ?

በሌላ በኩል ደግሞ ከምርጫው ይልቅ የዕለት ምግብ እና መደበኛ መጠለያ ነው የሚያስፈልገን የሚሉ በቱርክ እና ገራዶ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ናቸው።  "አሁን እኛ ኑሯችን ላይ ነው በጣም ተቸግረን፣ ከፍተኛ ችግር ላይ ነው ያለነው እዚህ ከረመዳን በፊት ነው እርዳታ ያገኘው ማህበረሰቡ፣ እና አሁን ከፍተኛ ችግር ላይ ነው ያለው አሁን በጣም በጣም ሰው አሁን ግማሹ ተበትኖ ልመና ወጥቶ ነው የሚመጣው"

 "ምን ትጠብቃላችሁ እናንተ ከምርጫው አሁን?  'እንጃ ይፈታልን' ነው አሁን ደግሞ እምቢ ብንል እንደ እምቢተኛ ያደርጉናል የሚለውን ተገንዝበን ነው እና በጣም ጉዳት ላይ ነው ያለነው እኛ፣ አሁን በጣም ህዝቡ እየተራበ ነው፣  አሁን እራሱ እዛ አንድ የደከመ ሰው አለ እየተራበ" 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምስል፦ Ethiopian National Election Board

በጃራ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ተፈናቃዮች  በምርጫ ወቅት ድምጽ መስጠት የምትችሉት ተፈናቅላችሁ ለመጣችሁበት አካባቢ ነው መባሉ እንግዳ ነገር ሆኖብናል ሲሉም ይናገራሉ። "ያው ወለጋ ያለውን ሰው ነው የምትመርጡ ስላሉን እኛ ደግሞ እዚህ ያለነው እንጂ እንዴት እዚህ ተቀምጠን ወለጋን እንመርጣለን እያልን እየተጨቃጨቅን ነበረ እዚህ ሆነህ ወለጋ የነበርክበት የምርጫ ክልል ሆናችሁ ነው የምትመርጡ... ለምሳሌ እኛ ከምስራቅ ወለጋ ነው የመጣነው፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ኪረሙ ያለውን ተወካይ ነው የምትመርጡ ማለት ነው እዛ ያለውን ተወካይ እጩ"።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ የመራጮች ምዝገባን የሚከውንባቸውን ቦታዎች ይፋ ሲያደርግ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው መጠለያዎች ተካተዋል። ይህም ተፈናቃዮች ባሉበት ሆነው ህገ-መንግስታዊ የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ እድል ይሰጣል የሚሉት በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን እሸቱ ናቸው።

"የመጡበትን አካባቢ ነው መምረጥ ያለባቸው። ለምንድነው የመጡበትን አካባቢ የሚመርጡ ሲባል የሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ አንደኛ ሀብት ንብረታቸው፣ ማንነታቸው የሚታወቀው በዛ አካባቢ ስለሆነ ነው። ሁለተኛ በዛ አካባቢ በሚያደርጉበት የምርጫ ተሳትፎ የሚበጃቸውን፣ የሚመራቸውን አካታች መሪ እንዲመርጡ ያስችላል፣ ወደ ቀያቸው እና ወደ ቦታቸው የመመለስበትን እድል የማመቻቸት አንዱ ሂደት ስለሆነ ድምጻቸውን የሚሰጡት በየመጡበት ይሆናል ማለት ነው"።

ነገር ግን ተፈናቅለው ከመጡበት ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ያሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ግን ባሉበት ቦታ እንዲመርጡ ይደረጋል። ይህ ደግሞ አለምአቀፍ ህግ ነው ብለዋል ። ‘' ያረፉበት ወረዳ ወይም ክልል እነሱን ለማቋቋም የተለያዩ ስራዎችን ሰርቶ ምናልባትም እንደ ነዋሪ ቆጥሯቸው አስፈላጊውን መታወቂያ እንዲያሟሉ አድርገው፣ የቤት መስሪያ ቦታ፣ ሌሎች ለምሳሌ ማቋቋሚያዎቹን ሰጥቶ በዛ አካባቢ እንዲኖሩ  አድርጓቸው ከሆነ የሚኖሩበትን አካባቢ የመምረጥ ግዴታ አለባቸው በአለም አቀፍም ሕግም ሲታይ በዚህ ልክነዉ"።#ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026

ኢሳያስ ገላው

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ