ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቱ ስልክ ደውሎ ይወያያል ወይስ የጽሑፍና የድምፅ መልዕክት መላክ ያዘወትራል?
ዓርብ፣ ሚያዝያ 9 2018
"ሚስተር ዋትሰን፣ ኑ ላናግርዎ እፈልጋለሁ።" ሲሉ ነበር አሌክሳንደር ግራሃም ቤል ከ 150 ዓመታት በፊት ረዳታቸውን ስልክ በመደወል የጠሩት! እነዚህ በሚገርም ሁኔታ በርቀት የተላለፉ የመጀመሪያዎቹ ዝነኛ ቃላት ነበሩ - የመጀመሪያው የስልክ ጥሪ። አሌክሳንደር ግራሃም ቤል እጎአ 1876 የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ የሆነውን ስልክ በመፍጠር የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝተዋል።
ብዙ የመገናኛ አማራጮች
ስልክ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን አካል እስኪሆን በርካታ ዓመታት ቢፈጅም ዛሬ ላይ ግን ስልክ መደወል ከመቼውም ጊዜ በላይ ቀላል ሆኗል። እድሜ ለ ተንቀሳቃሽ ስልኮች አሁን ላይ ከቤት ውጪ ሆነን በማንኛውም ቦታ የስልክ ጥሪዎችን ማስተላለፍ እንችላለን። ይሁንና ስልክ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ለብዙዎች ተመራጭ የመገናኛ መንገድ መሆኑ እየቀነሰ መጥቷል። በተለይ በወጣቶች ዘንድ።
ከኢሜል አንስቶ አጭር የጹሁፍ መልዕክት መላላከያ መንገዶች ፤ እንደ ዋትስዓብ፤ ኢሞ፤ ቴሌግራም ያሉ የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች እንዲሁም ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መልዕክት የምንለዋወጥበትን መንገድ እየቀየሩ ያሉ ይመስላል። መጠይቆች እንደሚጠቁሙት የጽሑፍና የድምፅ መልዕክት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል።
በኢትዮጵያ የትኛው የመገናኛ ዘዴ ይዘወተራል?
በጹሁፍ ስሜትን መግለፅ ስለሚከብድም የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ለዚህ መፍትሔ አዘጋጅተዋል። ኢሞጂስ የሚባሉት! የፈገግታ፣ የማዘን ወይም የተለያዩ የፊት ገፅታዎች ስልኮቻችን ላይ ይገኛሉ።
ጀርመን ውስጥ ባለፈው ዓመት የተደረገ የዳሰሳ ጥናት እንደሚጠቁመው 52 በመቶ ያህሉ እድሜያቸው ከ 16 እስከ 29 ዓመት የሆኑ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስልክ ደውለው ከማናገር ይልቅ የጽሁፍ ወይም የድምፅ መልዕክት መላክ እንደሚያዘወትሩ ይናገራሉ። bitkom በተባለው በዚሁ ጥናት 1004 ሰዎች ተሳትፈዋል።
በጀርመን የኑርንበርግ ከተማ ነዋሪ እና መጤዎች ከሀገሪቷ ዜጋ ጋር ተዋሕደው እንዲኖሩ የሚሠራ የከተማዋ ምክር ቤት አባል የሆነው ወርቅነህ ሥዩሜ የዳሰሳ ጥናቱ እውነታውን የሚያሳይ እንደሆነ ያብራራል። ምክንያቱ ደግሞ ይላል።"የጊዜ ቁጠባ ነው። ለወጣቱ ይቀላል። 2ኛ ፈተና የለውም። መልዕክቱን ከሚለዋወጠው ሰው ጋራ ብዙ ጥያቄ አያነሳም። የራሱን ሀሳብ አስቀምጦ መልስ ይጠብቃል። 3ኛ ጊዜው የቴክኖሎጂ ስለሆነ ሰዎች ሀሳባቸውን ለረዥም ጊዜ እንዲቀመጥ ያስችላቸዋል። እንደ ዋስትና ይይዛሉ። "
ወርቅነህ እንዳለው የጽሁፍ ወይም የድምፅ መልዕክት "ምን ተባብለን ነበር" የሚለውን መለስ ብሎ ለመቃኘት እድል ይሰጣል ። ይህ ብቻ አይደለም። የስልክ ንግግር አፋጣኝ ምላሽ ሲሻ በጹሁፍ ወይም በድምፅ የሚላክ መልዕክት ግን በአንጻሩ ጊዜ ይሰጣል። ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ረጋ ብለው፤ አሰላስለው እና በፈለጉት መንገድ ገልፀው መላክ ይችላሉ። አንዳንድ የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች እንደውም ጹሁፉ ከተላከም በኋላ ሰዎች እንዲያሻሽሉ ወይም ጨርሶ መልዕክቱን እንዲሰርዙ እድል ይሰጣሉ። ስለሆነም ይላሉ የቢትኮም የቴክኖሎጂ ባለሙያ ዶክተር ሴባስትያን ክሎስ፤ በተለይ በጽሑፍ መልዕክት በመላላክ ያደጉ ወጣቶች፣ ብዙውን ጊዜ በድንገት የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች ያስደነግጧቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ በመጠይቁ የተሳተፉ 35 በመቶ ያህሉ ለጓደኞቻቸው ወይም ለቤተሰቦቻቸው ስልክ ከመደወላቸው በፊት አስቀድመው መደዋወል ይችሉ እንደው በጽሑፍ መልዕክት ያሳውቃሉ።
ይህ ለኢትዮጵያው ማህበረሰብ አይሰራም ይላል ጀርመን ሀገር ነዋሪ የሆነው ወርቅነህ።"ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አንፃፍ ከዚህ ተቃራሚ ይመስለኛል። አብዝቶ የእኛ ሰዎች ሀሳብ በድምፅ ሲለዋወጡ ስሜቱን ድምፁን ነው መስማት የሚፈልጉት። …ይኼ ያሉበትን ሁኔታ በደንብ ስሜቱን ለመረዳት በድምጽ ቢደዋወሉ ይመርጣሉ።…"
በተጨባጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል ስንል በዶይቸ ቬለ የቴሌግራም ገጽ እና በዋትስዓፕ ጠይቀን ነበር። ቴሌግራም ላይ ባደረግነው መጠይቅ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ 370 ሰዎች ተሳትፈዋል። 63 በመቶ ያህሉ የፁሁፍ ወይም የድምፅ መልዕክት መላክን ወጣቱ ያዘወትራል ባይ ናቸው። ተመሳሳይ ውጤት በኃትስአብ መጠይቃችን ላይም ተጠስቷል።71 በመቶ ያህሉ የጽሁፍ ወይም የድምፅ መልዕክት ይዘወተራል ባይ ናቸው። ዝም ብለን በቀጥታ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልክ በመደወል የጠየቅናቸው ወጣቶች ግን ከዚህ ለየት ያለ አመለካከት አላቸው፤
የስልክ መጠይቆች
ሳሙኤል እንደሁኔታው ነው ይላል "አባቴ እናቴ ታላላቆቼ ጋር ስልክ በመደዋወል ነው። በእኔ እድሜ አኳያ ካሉት ጋር የጹሁፍ እና የድምፅ መልዕክት በመላላክ እንግባባለን"
ሳሙኤል ለወላጆቹ ስልክ መደወል ያስፈለገበት በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንዱ ምክንያት ስልክ መደወል "የአክብሮት ማሳያ ስለሆነ ነው" ይላል። ሁለተኛ ደግሞ መልዕክቱን ወዲያው ላያዩት ይችላሉ። አለመዱትምም! ሌላው በስልክ ያገኘነው ወጣትም ከፁሁፍ መልዕክት ይልቅ ለቤተሰቡ ስልክ መደወልን እንደሚያስቀድም ገልፆልናል።
አለሙ ጎጃም ውስጥ በአዊ ዞን እንጂባራ ከተማ አቅራቢያ ነው የሚኖረው።እዚህ አባባቢ አብዛኛው ማህበረሰብ በድምጽ ነው መልዕክት የሚለዋወጠው። በፁሁፍ ምናልባት እንኳን አደረሳችሁ ለመባባል ነው።
ሌላው ያነጋገርነው ወጣት ቢንያም ይባላል። እሱም ስልክ ቶሎ ምላሽ የማገኝበት ስለሆነ መደወሉን አዘወትራለሁ ይላል። ሌላም ምክንያት አለው "ከቤተሰቦቼ ጋር ደውዬ በድምጽ ነው የምነጋገረው። እናቴ ቤተሰቦቼ ገጠር ነው ያሉት። መልዕክቱን ላላዩት ስለሚችሉ ደውዬ ነው መልዕክት የማስተላልፈው። አንዳንድ ቦታ ደግሞ አልፎ አልፎ በጹሁፍ የማደርገውም አለ።"
በአዲስ አበባ የሚኖረው ቀነኒሳ ግን የድምፅ እና የጹሁፍ መልዕክት መላክን ያዘወትራል። "አብዛኛውን ጊዜ ስራ ቦታ ስለሆንኩኝ የፁሁፍ መልዕክት እልካለሁ። ከተመቸኝ የድምፅ መልዕክት እልካለሁ። አሰሪዎቼ ሊያዩኝ ስለሚችሉ ጎንበስ ብዬ እፅፋለሁ። "
ከዋጋ አንፃርም ቢሆን ከመደበኛው ስልክ ይልቅ የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎችን መጠቀም የተሻለ ነው ይላል ቀነኒሳ፤ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ጓደኞች አሉት"እዚህም ቢሆኑ ቀጥታ ከመደወል በኦንላይ መደወል የተሻለ ነው።"
ዋጋው ቢቀንስም ኢትዮጵያ ውስጥ በገጠሩ አካባቢ ለሚኖሩት ወይም ቤተሰብ ላላቸው እንደ ቢንያም እና ሳሙኤል ላሉት ወጣቶች ለጊዜው መልዕክት በጽሁፍ መለዋወጥ የማይታሰብ ነው፤ ቢንያም "ለገጠር አይሆንም" ይላል፣"በገጠር ይኼ ሜሴች የሚባለው ነገር፤ ምንድን ነው ሲገባ እየበራ ባትሪዬን የሚጨርሰው እያሉ የሚወዛገቡበት ጊዜ አለ፤ ለገጠር አይሆንም"
ጀርመን ሀገር የሚኖረው ወርቅነህም ቢሆን ለቀድሞው ትውልድ ስልክ ላይ ከማንበብ እና መፃፍ መቸገር ባሻገር ቴክኖሎጂው ሌላ ፈተና እንደሚሆንበት እረዳለሁ ይላል፣" የቴክኖሎጂው ሁኔታ ከዛ በፊት ላሉት ትውልዶች ያስቸግራቸዋል። ይኼ ግልጽ ነው። "
ልደት አበበ /ክሪስቲና ቡራክ