1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በእሥር ላይ ስለሚገኙ ፖለቲከኞች መፈታት ጠ/ሚ ዐቢይ የሰጡት ፍንጭ

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ ሐምሌ 3 2018

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በልዩ ልዩ ፖለትካዊ ምክንያቶች በእሥር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከእሥር ሊለቀቁ የሚችሉበት ዕድል ስለመኖሩ ፍንጭ ሰጡ። መንግሥታቸው "የሃይማኖት አባቶችን እና ትልልቅ ሰዎችን" ተጠቅሞ "በተቻለ መጠን በእሥር ላይ ያሉ ሰዎችን ለመፍታት" ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል ።

https://p.dw.com/p/5GteK
እነማን እና በምን የሥራ ዘርፍ ላይ የነበሩ ሰዎች በእሥር ላይ ናቸው?
እነማን እና በምን የሥራ ዘርፍ ላይ የነበሩ ሰዎች በእሥር ላይ ናቸው?ምስል፦ Kim Ludbrook/dpa/picture alliance

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እሥረኞችን በሚመለከት የሰጡት ፍንጭ ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  በልዩ ልዩ ፖለትካዊ ምክንያቶች በእሥር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከእሥር ሊለቀቁ የሚችሉበት ዕድል ስለመኖሩ ፍንጭ ሰጡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ዕለት በነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ መንግሥታቸው "የሃይማኖት አባቶችን እና ትልልቅ ሰዎችን" ተጠቅሞ "በተቻለ መጠን በእሥር ላይ ያሉ ሰዎችን ለመፍታት" ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል።

የእሥረኞችን መፈታት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ የነበረው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ የትኞቹ እንደሆኑ ባይጠቅስም እሥረኞች ሊፈቱ እንደሚችሉ መረጃ እንዳለው ለዶቼ ቬለ ጠቁሟል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ በፊናው 'ርምጃው የሚወሰድ ከሆነ በበጎ የሚታይና "ከጥያቄዎቻችን መካከል አንዱ እንደተመለሰ አድርገን እንወስደዋለን" ሲል ዛሬ ዐርብ ለዶቼ ቬለ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እሥረኞችን በሚመለከት የሰጡት ፍንጭ ምንድን ነው?

የአምስት ዓመታት የሥራ ዘመኑ ማክሰኞ ዕለት ያበቃው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻ ጉባኤ ላይ ዘለግ ያለ ማብራሪያ የሰጡት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የንግግራቸው መቋጫ ላይ በእሥር ላይ ስለሚገኙ ፖለቲከኞች መፈታት ፍንጭ ሰጥተዋል።

"የሃይማኖት አባቶች፣ ትላልቅ ሰዎች [ን] ተጠቅመን በተቻለ መጠን በእሥር ላይ ይሉ ሰዎችን ለመፍታት፣ በውጭ ሀገር ያሉ ሰዎችን በይቅርታ ለማስገባት፣ ጫካ ያሉ ሰዎችን በይቅርታ ለማስገባት፣ ለመተው ልባችን ሰፊ መሆን ይኖርበታል።"

እነማን እና በምን የሥራ ዘርፍ ላይ የነበሩ ሰዎች በእሥር ላይ ናቸው?

ኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች፣ በሽብር እና መሰል ጥፋቶች ተጠርጥረው በእሥር ላይ የሚገኙ የተሰናባቹ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ፣ በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን የተዋቀረውን ሰላም ሚኒስትርን በሚኒስትር ድኤታነት ያገለገሉ፣ የክልል ምክር ቤት አባላት፣ ጋዜጠኞች እና በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ በርካታ ሰዎች በእሥር ላይ ይገኛሉ።

የፓርቲዎች አስተያየት

አሁን በተሰናበተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ይሄው የእሥረኞች መፈታት ጥያቄ ተደጋግሞ ተነስቷል። ጥያቄው በተለይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክለው ከተመረጡ የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም፣ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ሲቀርብ ነበር። የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው ኮከስ ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍንጭ በበጎ እንደሚመለከተው የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

"የተባለው ነገር ከሆነ ከጥያቄያችን አንዱ መልስ አገኘ ብለን በአወንታ ነው የምንወስደው።"

ኢትዮጵያ  ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ - ኢሕአፓ "ሁሉን አቀፍ ሐቀኛ ድርድር ይደረግ፣ የፖለቲካ እሥረኞች ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ ይፈቱ" ሲል መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ "በፖለቲካ እና በማንነት" ምክንያት ለእሥር የተዳረጉ ያላቸው ፖለቲከኛች እና የመገናኛ ብዘኃን ባለሙያዎች እንዲፈቱ ጠይቀል። ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተባለው ስብስብም ይህንን ጥያቄ በጉልህ ለመንግሥት ሲያቀርብ ነበር። የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት የትኞቹ እንደሆኑ ባይጠቅሱም ሊፈቱ የሚችሉ እሥረኞች ስለመኖራቸው መረጃ እንዳላቸው ዛሬ ለዶቼ ቬለ ጠቁመዋል።

ኢሰመጉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን አስመልክቶ ታኅሣሥ ላይ ባደረገው ጥሪ "መንግሥት በፖለቲካ እሥር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ክስ በማቋረጥ እንዲሁም ለተፈረደባቸው ታራሚዎች ይቅርታ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያሰፋ" ጠይቆ ነበር
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም (ኢሰመጉ) ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን አስመልክቶ ታኅሣሥ ላይ ባደረገው ጥሪ "መንግሥት በፖለቲካ እሥር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ክስ በማቋረጥ እንዲሁም ለተፈረደባቸው ታራሚዎች ይቅርታ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያሰፋ" ጠይቆ ነበርምስል፦ Ethiopian Human Rights Council

"ትብብራችን እሥረኛ እንዲፈታ ተደጋጋሚ ድምፆችን በመግለጫም እንዲሁም ከባለሥልጣናት ጋርም ብተለያዩ ስብሰባዎች ስንገናኝ አንስተናል። በቅርቡም ይህ ፍንጭ ተሰጥቶናል። እንደሚፈቱ ተነግሮናል።"

የእሥረኞች መፈታት ጥያቄ በመብት ድርጅቶችም ሲነሳ ቆይቷል

የእሥረኞችን መፈታት ጥያቄን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም (ኢሰመጉ) ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን አስመልክቶ ታኅሣሥ ላይ ባደረገው ጥሪ "መንግሥት በፖለቲካ እሥር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ክስ በማቋረጥ እንዲሁም ለተፈረደባቸው ታራሚዎች ይቅርታ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያሰፋ" ጠይቆ ነበር። የሕብር ኢትዮጵያው ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነገረው ፍንጭ በበጎ የሚታይ ቢሆንም ግን ለዘላቂ ሰላም እና የችግር አፈታት ሂደት ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን ያምናሉ።

"የሚባሉት ለአንድ ወቅት የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ነው ወይስ የምር ነው? የምርስ ከሆና ዘላቂ መፍትሔ በዚህ መልክ ነው የሚመጣው ወይስ ሁሉን አቀፍ፣ አሳታፊ - የምክክር እና ድርድር መድረክ ነው መዘጋጀት ያለበት?" ሲሉ ጠይቀዋል።

ከመንግሥት ጋር "የሰላም ስምምነት" የፈረሙ ታጣቂዎችም ይህንኑ ሲጠይቁ ነበር

ከመንግሥት ጋር "የሰላም ስምምነት" መፈረሙን የገለፀው "የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት" የተባለዉ ታጣቂ ኃይል አካል የሆነው ቡድን በ "ፋኖ ስም የታሠሩት እንዲፈቱ" ከመንግሥት ያደረገውን ስምምነት ውጤት እየጠበቁ መሆኑንም ማስረሻ ሰጤ ከወራት በፊት ገልፀው ነበር። ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እንደሚለው ደግሞ እሥረኞች ያለምንም ልዩነት ሊፈቱ ይገባል።

ወደ ሀገራዊ ጉባኤ ለመግባት ጫፍ ላይ የደረሰው  የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን  ይህንን ጉዳይ እንደሚያስፈጽም በተደጋጋሚ መግለጡ አይዘነጋም። ሆኖም ለምን የፖለቲካ እሥረኞችን አታስፈቱም በሚል በቅርቡ ራሳቸውን "ከማንኛውም ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ" እንደሚያገሉ እና "ለጊዜው በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በአባልነትም ሆነ በደጋፊነት" እንደማይሳተፉ ባስታወቁት የአብን የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ ጥያቄ የቀረበለት ኮሚሽኑ "እኛ አክቲቪስቶች አይደለንም" የሚል ምላሽ መሰጠቱ በወቅቱ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን መንግሥታቸው እሥረኛ የመፍታት ፍላጎት ያሳየበትን ምክንያት ማክሰኞ ዕለት ሳይጠቅሱት አላለፉም።

"ለኢትዮጵያ ሲባል ነው" በማለት።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ