1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ የኢሰመኮ መግለጫ

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2018

በትግራይ ክልል “በግዳጅ ከሚታፈሱ ሰዎች መካከል በአብዛኛው እድሜያችዉ ከ18 ዓመት በታች መሆናቸዉን” እንዳረጋገጠ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ። “ሕፃናትንና ሌሎች ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ ወይም ለጦርነት ማሰማራት” ሕገ መንግሥቱንና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችን እንደሚጥስ ተችቷል።

https://p.dw.com/p/5GZp1
Äthiopien | Ethiopian Human Rights Comission
ምስል፦ Solomon Muche/DW

በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ የኢሰመኮ መግለጫ

ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አደረኩ ባለው ክትትል በ2012 ዓ.ም. ምርጫን ለማካሄድ ሕገ መንግስታዊ ተቋም ከሆነው የምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ በክልሉ ተደርጎ በነበረው ምርጫ መሠረት የተቋቋመ ምክር ቤት “የትግራይ ሕዝብን ሕልውና ለመጠበቅ” በሚል ርዕስ ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ውትድርና የማሰማራት ደርጊት የሚያስፈጽመውን ሰነድ (“ሕግ”) በማውጣትም ከሶ፤ ይህ ተግባር የፕሪቶሪያውን ግጭት የማስቆም ስምምነት የሚጥስ ነው ብሎታል፡፡

ኮሚሽኑ በመግለጫው አክሎም ድርጊቱ የሀገርና የሕዝብ መከላከያ፣ የደኅንነት እና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን እንዲሁም መሠረታዊ የሰዎች ሰብአዊ መብቶችን የመወሰን ኃላፊነትን በተመለከተ የተደነገገውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51፣ 52 እና 55(7)ን የሚጻረር ነው ብሎታል።

ያሰጋው የሰነዱ ይዘት

በዚህ ላይ ለዶይቼ ቬለ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የክትትልና ምርመራ ሪጂናል ዳይሬክተር ዮናስ ሙሉጌታ፤ “በምክር ቤቱ አፈጉባኤ የተፈረመበት ሰነድ ተመልክተው የረቂቁን መውጣንና ስራ ላይ መዋል አረጋግጠናል” ብለዋል፡፡ ከችግሩ ሰለባ ተጠቂ የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጮችም መረጃዎች መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ መደረግ ጀምሯል ያለው የግዳጅ ውትድርና ሰነድ የክልሉ ተወላጅ የሆነ ማንኛውም ሰው የሚቀርብለትን ጥሪ የመቀበል ግዴታ እንዳለበት የሚደነግግ ነው ብሏል፡፡

በሰነዱ መሰረት ጥሪውን የማይቀበል ሰው ላይ ከ10 ሺ እስከ 50 ሺ ብር ቅጣት እንደሚጣል ማረጋገጡንም ኢሰመኮ በመግለጫው አብራርቷል። የጸጥታ አካላት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ግለሰቦችን እንዲይዙና ፍተሻ እንዲያካሂዱ ሥልጣን የሚሰጥ ነው የተባለው ይህ ሰነድ፤ በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጪ ሆነው ውሳኔዎችን የሚተቹ ወይም የሚቃወሙ ግለሰቦች ወደ ኃላ ጭምር በመመለስ ከ5 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እና በንብረት መውረስ እንደሚቀጡ ደንግጓልም ተብሏል።  

ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ምርህን የጣሰ ነው ስለተባለው ድርጊት

እንደ ኢሰመኮ መግለጫ፤ ሰነዱ ሕፃናትን እና ሌሎች ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በግዳጅ ለጦርነት ማሰማራት የሕገ መንግሥቱንና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች መርሖችና ድንጋጌዎችን የሚጥስ ነው በማለት እንደ የጦር ወንጀል ሊቆጠር የሚችል ነው ብሎታንም። አስተያየት ሰጪው የኮሚሽኑ ባለስልጣን አቶ ዮናስ በዚህ ላይ አክለው በሰጡን ማብራሪያም፤ “ከሰብዓዊ መብት አንጻር በተለይ አሳሳቢ የሚደርገው፤ አንደኛው ይህ እርምጃ ህግና ህገመንግስቱን መሰረት አለማድረጉ ነው” ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ
የህወሓት ቃል አቀባይ በክልሉ የወጣው ሕግ ሕጉ የህግ የበላይነትን እና የህዝብ ደህንነትን ለማስጠበቅ እንጂ ለግዳጅ ውትድርና የወጣ አይደለም ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል። ምስል፦ Liu Fangqiang/Xinhua/picture alliance

የግዴታ ወታደራዊ ምልመላው ተጠቂዎች የአእምሮ ሕሙማን፣ ከትምህርት ተቋማት እና ከሃይማኖት ተቋማት ጭምር የሚመለመሉ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ጭምር መሆናቸውም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አካሄዱ ወደ ግችት የሚመራ እንደመሆኑ ከሰብዓዊ መብት አንጻር አሳሳቢ ድርጊት እንደሆነም አክለው ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮች፣ የአእምሮ ጤና ሕሙማን፣ ከጸበል ሥፍራዎች፣ ከአብያተ ክርስትያናት የአብነት ትምህርት ቤት፣ የገበያ ስፍራዎች፣ የወጣቶች ማዘውተሪያ ማዕከላት እና ቤት ለቤት በሚደረግ አሰሳ አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላው እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽኑ አብራርቷል፡፡

ኢሰመኮ በክልሉ እና በአጎራባች ክልሎች በታጠቁ ኃይሎች መካከል የተከሰቱ ያለው ግጭቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑንም በዘገባው አካቷል፡፡ ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በአፋር ክልል አብዓላ ከተማ አስተዳደር ሙርጋ ቀበሌ ልዩ ስሙ “አሳልጌ” በተባለ ሥፍራ ጥቃት ተፈጽሞ በነዋሪዎችና በግመሎች ላይ ጉዳት ደርሶ በርካቶችም መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ ከጠቃቀሳቸው የቅርብ ጊዜው ግጭት ዳፋዎች ተጠቃሽ ነው።

በኢሰመኮ የቀረበው ምክረ ሃሳብ

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በትግራይ ክልል ያለው የፖለቲካ ውጥረትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከፕሪቶሪያ የዘላቂ ሰላም ስምምነት የከሚያርቅ በመሆኑ ሁሉም አካላት ሰላማዊ መንገድን ተመራጭ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ የግዳጅ ውትድርና ሰነድ የተባለው ሕግም የዓለም አቀፍ ሕግ እና ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት የሌለው በመሆኑ ተፈጻሚነቱ እንዲቆም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የክትትልና ምርመራ ሪጂናል ዳይሬክተር ዮናስ ሙሉጌታ እንዳሉትም፤ “ፌዴራል መንግስትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነት ተመልሰው ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ ጠይቃነል” ብለዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ ከአንድ ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል በፌዴራል መንግስት እውቅና በሌሌው ምክር ቤት ጸድቆ ገቢራዊ ሆኗል ስለተባለው ሕግ ለህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም ጥያቄ አቅርቦላቸው፤ ሕጉ ለክልሉ የህግ የበላይነት እና የህዝብ ደህንነት እንጂ ለግዳጅ ውትድርና የወጣ አይደለም በማለት ነበር ያስተባበሉት፡፡  

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ