ሴቶች በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ምን ያህል ተቀባይነት አላቸዉ?
ማክሰኞ፣ ሰኔ 2 2018
የኢትዮጵያዉያት በፖለቲካዉ መድረክ ምን ያህል ተሳታፊ ናቸዉ? ተቀባይነታቸዉስ?
ኢትዮጵያዉያን ሴቶች በማኅበረሰቡ ዉስጥ ምን ያህል ተሳታፊ ናቸዉ? በፖለቲካዉ መድረክ የሴቶች ተሳትፎስ ምን ያህል ተቀባይነትስ ያገኛል? የምርጫዉ አሸናፊ ሴቶችን በካቢኔዉ ያካትት ይሆን? ኢትዮጵያዉያን ሴቶች በማኅበረሰቡ ዉስጥ ምን ያህል ይሳተፋሉ? ምን ያህል ተቀባይነትስ አላቸዉ? በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ የሴቶች ቁጥር መጨመር ለምን እውነተኛ ውክልናን ሊያሳይ አልቻለም?"የሴቶች ጥያቄዎች ፤በምርጫ ክርክሮችና በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ውስጥ ለምን ቅድሚያ አይሰጣቸዉም? በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ጾታ ከማንነትና ከስልጣን ጋር ያለው ትንቅንቅስ እንዴት ይፈታል?
በኢትዮጵያ 7ኛዉ ብሔራዊ ጠቅላላ ምርጫ ላይ የተሳተፉ ሴቶች፤ መብትን ለማስከበር፤ በልማድ እና ባህላዊ ልማድ ሴትን ገሸሽ የማድረግ ዝንባሌን ለመቅረፍ ሲሉ እንደተሳተፉ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ አንዳንድ በምርጫዉ የተሳተፉ ሴቶች ተናግረዋል። ቤት ማጀቴ ላይ ሞላልኝ ድህነቴን ላይቀርፍልኝ ደሞ የምን ምርጫ ያሉን በምርጫዉ የተሳተፉ ሴቶችም አሉ። ኢትዮጵያ የሴቶች በማኅበረሰቡ፤ በተለይ ደግሞ በፖለቲካዉ ዘርፍ ምን ያህል ተሳታፊ ናቸዉ? «እና ሴቶች ስንመርጥ ኖረናል። ይህ ምርጫ የሚያመጣዉ ፋይዳ የለም። ምናልባት ከዚህ በኋላ አዲስ ነገር የምናየዉ ካለ እንጠብቃለን። እስከዛሬ የምንተዳደረዉ በራሳችን ነዉ። ምንም አይነት ድጋፍ የለንም። ወደፊትም በራሳችን ነዉ የምንተዳደረዉ። በቻልነዉ አቅም ፤ አቅማችን በፈቀደ እየሰራን እንኖራለን።»
አድሎአዊ ልዩነትን ማስወገድ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ማለት በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሴቶች ያለ ምንም ልዩነት ከወንዶች እኩል ሃሳብ ከማበርከት እና ከመደመጥ እስከ ውሳኔ መስጠት ድረስ ትርጉም ባለው መልኩ እንዲሳተፉ ማድረግ ማለት ነው ይላል፤ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሎአዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት(CEDAW) . በኢትዮጵያ የሴቶች ተሳትፎ በማኅበረሰቡ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት አለዉ፤ ምርጫዉስ ? በሳምንቱ መጀመርያ ወደ ምርጫ ጣብያ ሄደዉ ድምፅ ከሰጡ መካከል አንዷ ሶፍያ ፤ እንደሚሉት መረጥኩ እንጂ፤ መምረጣቸዉ ለሳቸዉ ፋይዳ እንደሌለዉ ተናግረዋል።
«አስገዳጅ ሁኔታ ይኖራል፤ ግዴታ መምረጥ ስላለብንም እንመርጣለን። ብዙ ጊዜ ብዙ ነገሮች ላይ ሴቶች ነዉ የሚሳተፉት ፤ ስለዚህም እዚህ ምርጫ ላይም እንሳተፋለን። ጊዜዉ በአገር ቤት ብቻ ሳይሆን ዓለምም በመቀየሩ፤ ሴቶች በማጀት ብቻ የሚለዉ አስተሳሰብ እየቀረ ነዉ። አሁን ቢያንስ ራሳችንን ለማስተዳደር እንወጣለን» ሲሉ ሶፍያ አክለዋል። «ሴት ወደማጀት ይል የነበረዉ የቀድሞዉ አስተሳሰብ እቤት እንድንዉል አድርጎናል፤ ደካማ እንድንሆን በሆነ ሰዉ እጅ እንድንተዳደር ነበር። አሁን ቢያንስ ታግለን ራሳችንን እናስተዳድራለን።» ምርጫዉ ለሴቶች የተሻለ ነገርን ያመጣል ብለዉ አያስቡም? «ለእኛ ምርጫ ምንም ጥቅም የለዉም፤ እና የሚያዋጣን ሥራችን ብቻ ነዉ። የሚስተዳድረን ሥራችን ነዉ። ለኛ መምረጡ ምንም ጥቅም የለዉም። ግዴታ ሆኖብን ነዉ መምረጥ ስላለብን።»
ሴቶች እና የፖለቲካ ተሳትፏቸዉ
ሴቶች በፖለቲካዉ መድረክ እንዲሁም ማኅበረሰብ በሚሳተፍባቸዉ መድረኮች ብቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የወንዶች ሚና ከፍተኛ ነዉ የሚሉት ደግሞ በሃዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የጤና ባለሞያ እና ፖለቲከኛዋ ሐረገወይን ዘሪሁን ናቸዉ።
«የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ፤ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ወንዶች ናቸዉ ብዬ አስባለሁ። የወንዶች ድጋፍ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በጣም ያሰፋዋል። ከዝያ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት እና ተቋማቶች ብሎም የመንግሥት መስርያ ቤቶች በራሳቸዉ፤ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ አላቸዉ። እና ሴት ልጅ መምራት ትችላለች። ቤትዋን የመራች ሴት ፤ ትዳር ይዛ ትዳርዋን የመራች ፤ እና ትዳርዋን ያቆመች ፤ ልጆችዋን ያስተዳደረች፤ ልጅ ያበቃች ሴት ተቋም መምራት ትችላለች። አገርም መምራት ትችላለች ብዬ አስባለሁ። ስትመራም በጥበብ መምራት ትችላለች። ሴት ልጅ ትዳር ያልያዘችበት እድሜ ላይ ብትሆንም፤ ያልወለደችበት እድሜ ላይ ብትሆንም፤ ከናትዋ ያየችዉን መተግበር አይከብዳትም። እናም ሴትነት ፀጋ ነዉ። ሴትነት ጥበብ ነዉ። ስለዚህ ሴት ልጅ ለየት አድርጎ ፈጣሪ የሰጣትን ጥበብ ለመሪነት ብትጠቀም፤ አገር ታሻግራለች፤ አገር ሰላም እንድትሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። እናም እነዚህ ተቋማት በአንድነት፤ ወንዶቻችንም፤ አሁንም የሚታይባቸዉን ጭቆና አይነት ባህሪያቸዉን ትተዉ ሴቶችን ወደፊት ማዉጣት ይገባል። ሴቶችን ለመሪነት ማብቃት ስራዎችን ቢሰሩ የሴት ተሳትፎዋ በሁሉም ዘርፍ ይጨምራል። ይህ ደግሞ ለህብረተሰብ መጠንከር እና እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። በከተማ የሚገኙ ሴቶች በፖለቲካዉ መድረክ ላይ እታች ላይ ያሉትን ሴቶች የሚወክል፤ የገጠሪቱን ሴት የሚወክል መሆን ይኖርበታል። »
የአፍሪቃ የሰብአዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (Maputo Protocol, ሀገራት አካታች የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት የመገንባት እና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ አዎንታዊ የሆኑ የሕግ እና ሌሎች እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያስገድዳል ይላል። የሴቶች ድምፅ እንዲሰማ በሚዲያ ላይ በምታቀርባቸዉ ዝግጅቶችዋ የምትታወቀዉ፤ የሴቶች መብት ተሟጋቿ መልካም ሰዉ ሠለሞን በማኅበረሰብ ዉስጥ የሴቶች ተሳትፎ ለህብረተሰብ ሰላም እና አንድነት ምሶሶ መሆኑን ተናግራለች።
አጉል ባህል ወይስ ልማድ?
ሴትችን በአጉል ባህል ወይም ልማድ ምክንያት፤ ሴቶችን ወደኃላ የማድረግ፤ ሴቶች ወደ ማጀት የሚለዉ ጉዳይ አሁንም ቢሆን እንደሚስተዋል የሚናገሩ ጥቄቶች አይደሉም። ሴቶች በምርጫ መሳተፋቸዉ ምን ያህል አስፈላጊ ነዉ? አስተያየታቸዉን ለዶቼ ቬለ የሰጡት ሰናይት እንደሚሉት ምን ምርጫ ያስፈልጋል?በዘንድሮዉ ምርጫ ተሳትፌያለሁ፤ ግን ኑሮዬን ቤቴን ምንም አያሻሽልልኝም። ምርጫ ስለመረጥኩ በኑሮዬ በቤት ዉስጥ ባለብኝ ጫና ላይ የሚያመጣልኝ ምንም አይነት ድጋፍ እና እርዳታ የለም፤ የማገኘዉም ነገር የለም፤ ምርጫዉ የሚያመጣዉ ለዉጥ ይኖራል ብዬ አላስብም።» ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የሴቶች ቁጥር ከሃምሳ በመቶ በላይ አካባቢ መሆኑን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ሴቶችን በቅጡ ያላሳተፈ ማንኛዉም ማኅበረሰባዊ ጉዳይ ስኬት እንደሌለዉ የተናገሩት የሴቶች መብት ተሟጋችዋ መልካምሰዉ ገዳሙ ናቸዉ። የኢትዮጵያ 7ኛ አጠቃላይ ምርጫ ዉጤት አሸናፊ፤ በካቢኔዉ ሴቶችን በእዉን ያሳትፋል የሚል እምነት እናዳላቸዉ ጥቂት የማይባሉ ሴት መራጮች ተስፋ ሰንቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከ 2012 ምርጫ ማግስት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤታቸውን 50 በመቶ ሴቶች አድርገው ካዋቀሩ እና ሴቶችን ቁልፍ ስልጣን ላይ ካስቀመጡ በኋላ፤ በአገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን አትርፎላቸዉ ነበር፤ የሚታወስ ነዉ። ትልቅ መነጋገርያ ርዕስ ሆኖም ነበር። ይሁን እና ይህ ለይምሰል የሆነ ሹመት ነዉ በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሴቶች ሹመት ላይ ከፍተኛ ትችት ያቀረቡ እንደነበር የሚታወስ ነዉ። ዘንድሮስ ? በምርጫዉ አሸናፊ ካቢኔ በርከት ያሉ ሴቶችን እናይ ይሆን? በቅርቡ መልስ የምናገኝበት ይሆናል።
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026