1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትኢትዮጵያ

ሳዑዲ አረቢያ 4 ኢትዮጵያውያንን በሞት ቀጣች፤ 1655 ዜጎች ደግሞ በምህረት እንዲለቀቁ ተደረገ

ዓርብ፣ ሰኔ 5 2018

አራቱም ኢትዮጵያውያን በሞት የተቀጡት ወደ ሳዑዲ አረቢያ አደንዛዥ ዕፅ ይዘው በመግባታቸው ነው መባሉም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ እስር ቤት የሚገኙ 1655 ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲሰጣቸው ማድረጉን በዚሁ ሳምንት አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/5FIyr
ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤት
ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤትምስል፦ Privat

ሳዑዲ አረቢያ 4 ኢትዮጵያውያንን በሞት ቀጣች፤ 1655 ዜጎች ደግሞ በምህረት እንዲለቀቁ ተደረገ

ሳዑዲ አረብያ በዚህ ሳምንት 4 ኢትዮጵያውን በሞት ስትቀጣ፣  ኢትዮጵያ ደግሞ 1655 ዜጎቿ  በምህረት እንዲለቀቁ ማደረጓን አስታውቃለች። በሳዑዲ አረብያ የሞት ቅጣት ተበይኖባቸው ፍርዳቸውን በተለያዩ እስር ቤቶች ሆነው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዳሉም ከቤተሰቦቻቸው አንዱ ለዶቼቬለ ተናግሯል። ኂሩት መለሰ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች።  
ሳዑዲ አረቢያ በዚህ ሳምንት አራት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቅጣቷን አስታውቃለች። በሳዑዲ አረብያ  የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃ መሠረት ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓም ሁለት ኢትዮጵያውያን በናጅራን ግዛት፣ እንዲሁም ሰኔ 3ቀን 2018 ዓ.ም. ሌሎች ሁለት ኢትዮጵያውያን በአሲር ግዛት በስቅላት መገደላቸው ተዘግቧል።

አራቱም ኢትዮጵያውያን በሞት የተቀጡት ወደ ሳዑዲ አረቢያ አደንዛዥ ዕፅ ይዘው በመግባታቸው ነው መባሉም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ እስር ቤት የሚገኙ 1655 ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲሰጣቸው ማድረጉን በዚሁ ሳምንት አስታውቋል። በሳዑዲ አረብያ በስቅላት ስለተገደሉትም ሆነ በምኅረት ስለተለቀቁት ኢትዮጵያውያን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ዶቼቬለ ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነበያት ጌታቸው የእጅ ስልክ ላይ ቢደውልም ስልካቸው አልተነሳልንም። 

ኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ እስር ቤት የሚገኙ 1655 ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲሰጣቸው ማድረጉን በዚሁ ሳምንት አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ እስር ቤት የሚገኙ 1655 ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲሰጣቸው ማድረጉን በዚሁ ሳምንት አስታውቋል። ምስል፦ Solomon Muche/DW

ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁት  አንዱ፣ሳዑዲ አረብያ ለብዙ ዓመታት የኖረው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ   ሰሞኑን የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ውሳኔ ተላልፎባቸው ከነበሩት በርካታ ኢትዮጵያን መካከል መሆናቸውን ያስታውሳል። የተገደሉትም  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጡ አዳዲስ ሕጎችን በሚጻረሩ  ድርጊቶች ተወንጅለው እንደሆነ ገልጿል። 

«ከዚህ በፊት ናጅራን በሚባል የሳዑዲ ክፍል  ከ45 በላይ ኢትዮጵያውያን የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ይታወቅ ነበር።  የፍርድ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያውያውያን አንገታቸው እየተቀላና እየተሰቀሉ ፍርዱ መከወኑን ሰምቻለሁኝ ብሏል ነብዩ። በዚህ ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት የሚገኙ 1655 ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት ቢደረግላቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ተናግሯል።

ሦስት ኢትዮጵያውያንባለፈው ሚያዚያም የሞት ቅጣት እንደተፈጸመባቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂዩመን ራይትስ ዋች አስታውቆ ነበር። በወቅቱ የሞት ቅጣት ተፈርዶባቸው በሳዑዲ እስርቤቶች ቀናቸውን የሚጠባበቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ሂዩመን ራይትስ ዋች ገልጿል።  ሳዑዲ አረብያ የሚገኘው ዓለሙ መኮንን ለዓመታት በሳዑዲ እስር ቤት ሞታቸውን ከሚጠባበቁት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ መሆኑን እዚያው ሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው ታላቅ ወንድሙ ኃይሌ መኮንን ለዶቼቬለ ተናግሯል። ኃይል እንደተናገረው ዓለሙ መኮንን ሳዑዲ አረብያ በገባ በሦስት ወሩ ነው የታሰረው። ከታሰረም 6 ዓመት አልፏል። ሞት ተፈርዶበት ቀኑን እየተጠባበቀ ነው። ስራ ፍለጋ በሄደበት ሰው ገለሀል ተብሎ  ወንድሙ ዓለሙ መኮንን ሞት እንደተፈረደበት የሚገልጸው ኃይሉ፣ ወንድሙ ፍትህ እንዲያገኝ ቢጥርም እንዳልተሳካለት ነው የተናገረው።   

ኂሩት መለሰ 

ፀሐይ ጫኔ