1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሥጋት ያጫረው አዲሱ የኤቦላ ተሐዋሲ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 6 2018

የአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከላት (CDC ) እጅግ እየተስፋፋ በመጣው ኢቦላ ተሐዋሲ ወጣቶች በዋናነት እየተጠቁ መኾናቸውን ዐሳውቋል ። በተሐዋሲው የተነሳ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከፍ ማለቱ ተነግሯል ።

https://p.dw.com/p/5FJCL
እስካሁን ድረስ አንድም የአፍሪቃ አገር ለቡንዲቡግዮ ተሐዋሲ ማከሚያ በሙከራ ላይ ያለ መድኃኒት የሚጠቀም የለም
እስካሁን ድረስ አንድም የአፍሪቃ አገር ለቡንዲቡግዮ ተሐዋሲ ማከሚያ በሙከራ ላይ ያለ መድኃኒት የሚጠቀም የለም ምስል፦ Benediction Murhabazi/AFP

አዲሱ የኤቦላ ተሐዋሲ፤ ቡንዲቡግዮ ያጫረው ሥጋት

የአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከላት (CDC ) እጅግ እየተስፋፋ በመጣው ኢቦላ ተሐዋሲ ወጣቶች በዋናነት እየተጠቁ መኾናቸውን ዐሳውቋል ። በተሐዋሲው የተነሳ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከፍ ማለቱ ተነግሯል ። ተቋሙ ይፋ እንዳደረገው ከኾነ፦ እስከ ሐሙስ ዕለት ከኢቦላ ተሐዋሲ ጋር በተገናኘ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 635 ደርሷል ። የሟቾች ቁጥር ደግሞ በኮንጎ እና ኡጋንዳ ውስጥ ወደ 127 ከፍ ብሏል ። ይህ ቁጥር ዘገባው ይፋ ከኾነበት ሐሙስ በኋላ ባሉት ሁለት ቀናት ለውጥ ሊኖረው ይችላል ።

በተጠቀሱት የአፍሪቃ አገራት የተቀሰቀሰው የኢቦላ ተሐዋሲ ብዙም ባልተለመደው የቡንዲቡግዮ ተሐዋሲ የተነሳ መኾኑም ተዘግቧል ። ይህን ተሐዋሲ ለመዋጋት ከቤተ ሙኩራ አልፎ በሰዎች ላይ ሊሞከር ከተዘጋጀው በስተቀር በይፋ ተግባራዊ የኾነ የተረጋገጠ ክትባት አለያም ሕክምና የለውም ። 

የአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከላት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ዦን ካሴያ እንደሚሉት፦ የቡንዲቡግዮ ተሐዋሲ ኢቦላ በሌላ ስሙ ከሚታወቅበት «የዛየር ተሐዋሲ» አይነት በተለየ መልኩ በ16 ቦታዎች ላይ ዳግም ለመቀስቀሱ ሰበብ ነው ። 

«እስካሁን ድረስ አንድም የአፍሪቃ አገር ለቡንዲቡግዮ ተሐዋሲ ማከሚያ በሙከራ ላይ ያለ መድኃኒት የሚጠቀም የለም ኾኖም ግን ያዘጋጀነው ክትባት፣ ያዘጋጀናቸው እጩ አካሚዎች አሉን በሰዎች ላይ የሚደረግ ሙከራ መጀመር፤ ለአገራትም በሰዎች ላይ ለሚደረጉ ሙከራዎች መስማማት ያስፈልገናል »

አዲሱ አይነት የኢቦላ ተሐዋሲ በፍጥነት መስፋፋቱን ለመግታት በሚደረገው ርብርብ ብርቱ ተግዳሮት የፈጠሩ ጉዳዮች አልታጡም ። ከነዚያ መካከል በተቆጡ የማኅበረሰብ አባላት የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በዋናነት ይጠቀሳል ። አንዳንድ የአካባቢው ማኅበረሰብም ተሐዋሲውን ለመግታት በሚደረገው ርብርብ ላይ ብርቱ ጥርጣሬ ማሳየታቸው ተጨማሪ ተግዳሮት ኹኗል ። በአካባቢው ያሉ ግጭቶች መቀጠላቸውም የኢቦላ ተሐዋሲን ለመግታት እንቅፋት እየፈጠሩ መኾናቸው ተጠቅሷል ። እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች የገጠሙት ይህ አዲስ አይነት የኤቦላ ተሐዋሲ በዋናነት እያጠቃ የሚገኘው ወጣቶችን መኾኑን ዶ/ር ዦን ካሴያ ተናግረዋል ።

«የምናወራው እጅግ ስለተጎዱ ዕድሜያቸው 15 እስከ 44 ዓመት ስለኾናቸው ወጣቶች ነው እነሱ እጅግ የተጎዱ መኾናቸውን ዕናውቃለን በእንቅስቃሴ እና በማዕድን ዘርፍ ላሉ የማኅበረሰብ ሚናዎች ተጋላጭ ናቸው »

የአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከላት ስለ አዲሱ ተሐዋሲ የግንዛቤ ለማስጨበጥ በጠራው ስብሰባ ላይ ዶ/ር ዦን ካሴያ የአካባቢው አገራት «አጋርነት በማሳየት ሚና እንዲኖራቸው» ግንዛቤ ማጨበጥም ወሳኝ መኾኑን ለመገናኛ አውታሮች ተናግረዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች በኢቦላ ተሐዋሲ ቢያዙ  ወደ ጀርመን አለያም ወደ ሌላ ለሕክምና ከመብረር ይልቅ ኬንያ ውስጥ ክትትል እንዲደረግላቸው 23 የለይቶ ማቆያ ማእከላት መዘጋጀታቸውንም ዶ/ሩ ይፋ አድርገዋል ።

የአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከላት ይፋ ባደረገው መረጃ፦ ለኢቦላ ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ ሊኾኑ ይችላሉ ያላቸውን ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 የአፍሪቃ አገራት ዘርዝሯል ። እንደ  ኬንያ ሁሉ ሌሎች የአፍሪቃ አገራትም ዝግጅታቸውን እንዲያጠናክሩ ተነግሯቸዋል ። የኢቦላ ተሐዋሲን ለመግታት ርብርቡ ሊፋጠን ይገባልም ተብሏል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti