1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የ7ኛዉ አጠቃላይ ምርጫ ዉጤት፣ እድምታዉና የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሰኔ 15 2018

በኢትዮጵያ የቅርብ ይሁን የሩቅ ዘመን ታሪክ የተደረጉ ለዉጦች በሙሉ የተደረጉት በምርጫ ሳይሆን በቤተ መንግሥት ሴራ፣ በመፈንቅለ መንግሥት፣በጦርነትና በሕዝባዊ አመፅ ነዉ።ምክንያቱ ብዙ ነዉ።ፕሮፌሰር መረረ «መሠረታዊ ችግራችን» የሚሉት ይጠቅሳሉ።

https://p.dw.com/p/5Frt0
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ እንደተጠበቀዉ በዘንድሮዉ ምርጫ አሸንፏል።
የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ (ብልፅግና ፓርቲ) ካደረጋቸዉ የምርጫ ዘመቻዎች አንዱ።በምርጫዉ አሸንፏልምስል፦ Prosperity Party

ማሕደረ ዜና፣ የ7ኛዉ አጠቃላይ ምርጫ ዉጤት፣ እድምታዉና የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ

የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በኃይል መዳከም፣ በዉጪ ጫና፣ በድርድር-ሥምምነትም ያበረዱት ጦርነት ዳግም ይጫራል የሚለዉ ሥጋት ብዙዎችን እያብሰከሰከ ነዉ። ኦሮሚያ ክልል የሸመቀዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ)ና አማራ ክልል የተደራጁት የፋኖ ታጣቂዎች ከፌደራልና ከየክልላዊ መንግሥታት ኃይላት ጋር የገጠሙት ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።አማፂያን ወይም ሌሎች ታጣቂዎች በየአካባቢዉ የሚደርሱት ጥቃት፣እገታና ዘረፋ የሰዎችን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እያወከዉ ነዉ።የአብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታ ሰሚ ያገኘ አይመስልም።በዚሕ መሐል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አገላለፅ ኢትዮጵያ መረጠች።እንደተጠበቀዉ ገዢ ፓርቲዋ አሸነፈም።እንዴት እና ከእንግዲሕ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የዘንድሮዉ ምርጫ «ልዩ» የሚሆንበት ምክንያትና ልዩነት

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ልሒቃን በየትኛዉም ጎራ ቢሰለፉ ለየድርጊት፣ብሒል ዕቅድ ዉጤታቸዉ «ልዩ» ማለትን ይወዳሉ።የዘንድሮዉም ምርጫ ልዩ የሚባልበት ብዙ ምክንያቶች አሉት።የገዢዉ ፓርቲ መሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ምርጫዉ ከቀዳሚዎቹ «ልዩ» ለመሆኑ ከሚሰጧቸዉ ምክንያቶች አንዱ ለመምረጥ የተመዘገበዉ ሕዝብ ቁጥር ከ54 ሚሊዮን መብለጡን ነዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ደግሞ የምርጫዉ አጠቃላይ ዉጡት ከመነገሩ አንድ ቀን አስቀድመዉ «የምርጫዉ ሒደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ የሐገር ፍቅር፣ የሰላምና የብልፅግና ጉጉት ያሳየበት ነዉ» ማለታቸዉ ተዘግቧል።ምርጫና ሒደቱ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች «ልዩ» የሚሆንባቸዉ እንደ የፓርቲዎቹ አቋም፣ ተስታፎና የመሳተፍ ወይም ያለመሳተፋቸዉ ምክንያት ለየቅል ነዉ።

ኢሶዴፓ ከተመሠረተ ከ1987 ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ አልተሳተፈም

ከተመሠረተ ከ1987 ጀምሮ በተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ ሲሳተፍ የነበረዉ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር ራሔል ባፌ እንደሚሉት በዘንድሮዉ ምርጫ እንዳይሳተፍ በመደረጉ ምርጫና ሒደቱን ሐገ-ወጥና ልዩ ያደርገዋል።

«እኛ እንደ ኢሶዴፓ ሁሉንም ምርጫዎች ከ1987 ጀምሮ ከምሥረታችን ጀምሮ እስካሁን ተወዳድረናል።ተሳትፈናል።በዘንድሮዉ ምርጫም ሁኔታዎች አስቻይ ባይሆኑም---መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አግባብ የአምስት ዓመቱን ምርጫ ማካሔድ አለብኝ ብሎ በወሰነዉ መሠረት፣ እኛም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የሕገ መንግሥቱ መከበር ግዴታ ነዉ ብለን ሥለምናስብ---ለህዝባችን አማራጭ መሆን አለብን ብለን ነበር ወደ ምርጫዉ የገባነዉ።»

ዶክተር ራሔል እንደሚሉት ኢሶዴፓ ከተመሰረተ ከ1987 ጀምሮ ዘንድሮ በምርጫ አልተካፈለም
ዶክተር ራሄል ባፌ።የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ምስል፦ Privat

ዶክተር ራሔል እንደሚሉት ፓርቲያቸዉ በምርጫዉ ለመሳተፍ ከ300 በላይ ዕጩዎች አቅርቦ ነበር።ይሁንና በምርጫዉ ለመሳተፍ እስከ ፍርድ ቤት የደረሰ ሙግት ቢገጥምም እንዳይሳተፍ ታግዷል።

ኦነግ በ50 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ተሳተፈ ግን አንድም መቀመጫ አላገኘም

በ1960ዎቹ አጋማሽ የተመሠረተዉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ባንፃሩ ከተመሠረተ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘንድሮዉ ምርጫ ተካፍሏል።የፖርቲዉ የፖለ,ቲካ ጉዳይ መኮንንና የሕዝብ ተወካዮች ምርክር ቤት ዕጩ ዳዊት አብደታ እንደሚሉት ፓርቲያቸዉ በምርጫዉ የተወዳደረዉ የፖለቲካ ፓርቲ ፍቃዱ እንዳይሰረዝ ነዉ።ይሁንና አጋጣሚዉ ኦነግ  ርዕይ፣ዓላማና ፕሮግራሙን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ ጠቅሞታል።

«በ50 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነዉ በኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ተሳትፎ ያደረገዉና ይህን አጋጣሚ እንደ ትንሽ ነገር መቁጠር አንችልም።በዚሕ አጋጣሚ ቢያንስ ለሕዝባችን ያለንን ርዕይ፣ ዓላማና ፕሮግራማችንን ለመናገር ችለናል።»

ይሁንና አቶ ዳዊት እንደሚሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነፃ ተቋማት የሉም።በዚሕም ምክንያት ምርጫና ሒደቱ ነፃና ፍትሐዊነዉ ማለት አይቻልም።የፀጥታዉ ሁኔታም ግንባሩ በፈለገዉ ልክ እንዳይወዳደር አግዶታል።

«አንድ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሔድ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች አሉ።እነዚያ መሠረታዊ ነገሮች ከሚዲያ አንፃር፣ ከሲቪክ ሶሳይቲ አንፃር፣ ፍርድ ቤትንም በተመለከተ እዚሕ አገር ነፃ ተቋማት የሉም።ሒደቱም ከዚሕ አንፃር የሚለካ ነዉ።ከዚሕ በተጨማሪ በሐገራችን ያለዉ ተጨባጭ የሰላም ሁኔታ የምርጫ ቅስቀሳም ሆነ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያመች ሁኔታ የለም።»

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በ50 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደረበት ምርጫ አቶ ዳዊት አብደታን ጨምር በሁለት የከተማና በአራት ክልሎች 163 ዕጩዎችን ለፌደራልና ለክልል ምክር ቤቶች አባልነት አወዳድሮ ነበር።ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገለፀዉ ዉጤት መሠረት ግን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድም የኦነግ ዕጩ በምርጫዉ አላሸነፈም።«ልዩ» እንበለዉ ይሆን?

በምርጫዉ «መሳተፋችን ርዕይ፣ዓላማና ፕሮግራማችንን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ ጠቅሞናል።» አቶ ዳዊት አብደታ
አቶ ዳዊት አብደታ።የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የፖለቲካ ጉዳይ መኮንን።«ኢትዮጵያ ዉስጥ ነፃ ተቋማት የሉም»ምስል፦ Negash Mohammed/DW

«የዘንድሮዉን ምርጫ ለእግዚአብሔርና ለ4 ኪሎ ትተናል»-መረራ ጉዲና

 

እንደ ኦነግ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲነት ፈቃዱን ላለማጣት በጥቂት የምርጫ ክልሎች የተወዳደረዉ የኦሮሞ ፌደራዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፕሬዝደንት መረራ ጉዲና እንደ የምርም፣ እንደ ቀልድም፣ እንደምፀትም እያሉ የዘንድሮዉን ምርጫ «ለፈጣሪና ለ4 ኪሎ ትተናል» ይላሉ።

«(የዘንሮዉ ምርጫ) ቅርጫ እንኳን ለመሆን ያልተዘጋጀ ምርጫ ዉስጥ መግባቱ ለራሳችንም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም በንደዚሕ ዓይነት ዉስጥ ገብተን ብዙ ላንለዉጥ፣ ላንጠቅም እንዲያዉም አንዳድ ጊዜ እኔ ሥቀልድ የዘንድሮን ምርጫ ለእግዚአብሔርና ለ4ኪሎ ትተናል ነዉ የምለዉ»

የፖለቲካ ሳይቲስቱ መረራ ጉዲና ከምፀቱ ጀርባየዘንድሮዉ ምርጫ ከዚሕ ቀደም የተደረጉትን ያክል እንኳን ዉድድር፣ ፉክክርና የምርጫ ሒደቶችን ያላስተናገደበትን ምክንያት ዘርዝረዋል።በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለምርጫዉ አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር ፓርቲያቸዉ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሆኖ ያቀረበዉ ጥያቄ መልስ አላገኘም።በሳቸዉ አገላለፅ መንግሥት «ዝግጁ አይደለም።»

«ነፃ ናቸዉ ከሚባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መንግሥትን በተደጋጋሚ ጠይቀናል።አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር፣ መንግሥት ዝግጁ አይደለም።በተለይም ከሁሉም በላይ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን የማይፈታ ምርጫ ዉስጥ መግባቱ አስጨነቀን።ሁለቱ ምርጫዉ የማይፈታቸዉ መሰረታዊ ነገሮች፤ አንደኛ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት አያመጣም።ሁለተኛ እዉነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አይፈጥርም።ሁለቱን ካልፈጠረ ምንድነዉ የምናገኘዉ?»

ጠየቁ ፕሬፌሰር  መረራ ጉዲና።ምርጫዉ የፕሮፌሰር መረረን ጥያቄ መመለስ አለመመለሱ በርግጥ አሁን በግልፅ አይታወቅም።

«የዘንድሮዉን ምርጫ ለእግዚአብሔርና ለ4 ኪሎ ትተናል» ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና።የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፕሬዝደንትምስል፦ Seyoum Getu/DW

ከ40 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተካፍለዋል

ከአምስት ዓመት በፊት በተደረገዉ ምርጫ በጦርነት ምክንያት ምርጫ ያልተደረገበት የትግራይ ክልል ዘንድሮም ምርጫ አልተደረገም።ከአምስት ዓመት በፊት ምርጫ ከተደረገባቸዉ የአማራ ክልል አካባቢዎች ቢያንስ በ8ቱ ዘንድሮ ምርጫ አልተደረገም።

በተቀሩት አካባቢዎች በተደረገዉ ምርጫ ከ40በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተካፍለዋል።አሸናፊዉ ግን ከምርጫዉ በፊት እንደተጠበቀዉ ገዢዉ ፓርቲ ነዉ።ትግራይ ክልል በሙሉ ወይም 38 የምርጫ ክልሎችና በአማራ ክልል 8 የምርጫ ክልሎች ምርጫ ሥላልተደረገ የፈደራዊዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች ምርጫ የተደረገዉ ለ501ዱ መቀመጫዎች ነዉ።አንድ የምርጫ ክልል አንድ መቀመጫን ይወክላል።

ድጋሚ ቆጠራና ምርጫ የሚደረግባቸዉ የምርጫ ክልሎች አሉ-ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢተስፋዬ ነዋይ ትናንት እንዳስታወቁት የድምፅ አሰጣጥ፣ የዉጤት አሞላል ችግር፣ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ቅሬታና የምርጫ ሕግ ጥሰት  በተከሰተባቸዉ የምርጫ ክልሎች አድም ድጋሚ ቆጠራ፣ ሁለትም ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ተወስኗል።

«ጉሉሕ የሆነ የድምፅ አሰጣጥና ዉጤት አሞላል ችግር በማጋጠሙ ድጋሚ ቆጠራ የሚካሄድባቸዉ---በተጠቀሱት ምርጫ ክልሎች ላይ ለሚመለከታቸዉ ምክር ቤቶች ድጋሚ ቆጠራ ቦርዱ ወስኖ የሚከናወን ይሆናል።ሁለተኛ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ቅሬታ በማቅረቡ የተሰጠዉ ድምፅ በድጋሚ እንዲቆጠር የተወሰነበት---»

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሠብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ።የምርጫዉን ዉጤት ይፋ ባደረጉበት ወቅት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሠብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ።የምርጫዉን ዉጤት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ዝርዝር መግለጫ ያሰሉ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ከ501ዱ የምርጫ ክልሎች የ15ቱ ዉጤት አልተገለፀም።ትናንት ይፋ የሆነዉ  የምርጫ ዉጤት የ486ቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ነዉ።ከ486ቱ መቀመጫዎች438ቱን ጠቅላይ ሚንስር ዓብይ አሕመድ የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ አሸንፏል።ወደ 90 በመቶ ግድም ማለት ነዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በምርጫ የመጣ ለዉጥ የለም

ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ ምርጫ ታደርጋለች።አሁን የሚሰራበት ሕገ-መንግሥት ከፀደቀ በኋላ ምርጫ ሥታስተናግድ ተዳድሞ እንደተባለዉ የዘንድሮዉ 7ኛዉ ነዉ።

በተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሸነፍ አይደለም፣ አንድ አይደለም ሁሉም ተቃዋሚዎች ተደምረዉ 40ና 30 ከመቶ የሚሆን ድምፅ እንኳን ማግኘታቸዉ በይፋ ተነግሮ አያዉቅም።የተደረጉት ምርጫ ሒደቶችና ዉጤታቸዉ ሁሌም እንዳወዛገቡ ነዉ።በኢትዮጵያ የቅርብ ይሁን የሩቅ ዘመን ታሪክ  የተደረጉ ለዉጦች በሙሉ የተደረጉት በምርጫ ሳይሆን በቤተ መንግሥት ሴራ፣ በመፈንቅለ መንግሥት፣በጦርነትና በሕዝባዊ አመፅ ነዉ።ምክንያቱ ብዙ ነዉ።ፕሮፌሰር መረረ «መሠረታዊ ችግራችን» የሚሉት ይጠቅሳሉ።

«ከመሰረታዊ ችግሮቻችን ልነሳ።ከሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ መሪዎች ሁለት አጀንዳ ነበራቸዉ አንደኛዉ በአዉሮጳ ላይ መድረስ (የዚያን ጊዜ አሜሪካ አልነበረችም) እና ከአዉሮጳዉያን ጋር እንስተካከል የሚል ነበራቸዉ።ሁለተኛዉ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን አንድ ሐገር አንድ ሕዝብ----ከሚንሊክ እስከ ዶክተር ዓብይ ሁለቱም አልተሳኩም-----።»

ብልፅግና ፓርቲ ቃል ገባ

ከ5 ዓመት በፊት እንደሆነዉ ሁሉ በዘንድሮዉም ምርጫ ያሸነፈዉ ብልፅግና ፓርቲ ከትግራይ ክልል እስከ አዲስ አበባ ጠረፎች የሕዝብን ሕይወት፣ ኑሮና እንቅስቃሴ ለአደጋ ያጋለጠዉን የፀጥታ መታወክ፣ የፖለቲካ ዉዝግብ፣ ሕዝብ ያማረረዉን የኑሮ ዉድነት፣ የባለሥልጣናቱን ሙስናና የአስተዳደር እዉቀት ጉድለትን ካላሻሻለ የትናንቷ ኢትዮጵያ ዛሬ እንደሌሎች ሁሉ ዛሬ ያለችዉ ኢትዮጵያ ነገ መኖርዋ በርግጥ ያጠራጥራል።

ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገዉ ዉጤት መሰረት ከ486 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 348ቱን ብልፅግና አሸንፏል።የ15 መቀመጫዎች ዉጤት ገና ነዉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛዉን ምርጫ አጠቃላይ ዉጤት ይፋ ያደረገበት ሥርዓትምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

የምርጫዉ ዉጤት ከተነገረ በኋላ ትናንት ብልፅግና ፓርቲ ባወጣዉ «የምሥጋና» መግለጫ «ዘላቂ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን በስፋት ለመፍጠርና የዜጎቻችንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ--» እያለ የዘረዘራቸዉን የሕዝብ ጥያቄዎች  ለመመለስ «በቁርጠኝነት የምንሰራ ይሆናል።» ብሏል።ያደርገዉ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ