ለምርጫው የፀጥታና አስቻይ ኹኔታን የሚገመግም ቡድን መሰማራቱ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 19 2018
የተደራጀው ቡድን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ወደ ክልሎች በመሄድ የምርጫ ክልሎችን ጭምር ይገመግማል ተብሏል። ቡድኑ በየአካባቢዎቹ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን፣ የመራጮች ትምህርት የሚሰጡ እና ምርጫ የሚታዘቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እንዲሁም የቦርዱን ባለሙያዎች ያካተተ ነው። ጉዳዩን እንደሚያውቁ እና ተሳትፎም እንዳላቸው የገለፁ ፓርቲዎች፣ ይህ ቡድን ተመልክቶ የሚያመጣው የዳሰሳ ውጤት ለምርጫ ሥራቸው ወሳኝ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማድረግ በሀገሪቱ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ተወያይቶበታል። ምርጫ የሚደረግባቸውን ቦታዎችም አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ብሎ ለይቷል። ቀይ ምርጫ ሊደረግ የማይቻልበት ቦታ ነው። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ደግሞ በስድስት ክልሎች ሁለት ዐበይት ጉዳዮችን የሚዳስስ ቡድን በተቋማቸው ተደራጅቷል።
«በመሬት ላይ ያለውን፣ የፀጥታ ሁኔታ እና ጎን ለጎን አስቻይ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳሩንም ጨምረው የሚያዩ ቡድኖች ቦርዱ አዘጋጅቷል።»
የምርጫ «አስቻይ ሁኔታ ይኑር፣ በፓርቲ አባላት ላይ የሚፈፀም ማዋከብ ይቁም» የሚሉና ምቹ የውድድር ምኅዳር መኖርን የሚጠይቁ ጉዳዮች እንደ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ያሉ ቅንጅቶች በተደጋጋሚ ሲያነሱት የቆዩ ጉዳይ ነው። አብርሃም ሃይማኖት የቅንጅቱ ሰብሳቢ ፓርቲ - ኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ናቸው።
«መላው ሀገሪቱ ውስጥ አስቻይ ኹኔታ የለም ማለት ይቻላል»
ስምንት ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያሰባሰበው «ሰላም ለኢትዮጵያ» የተባለው ጥምረት ዋና አሥፈፃሚ አቶ ዳሮት ጉምአ በዛሬው ዕለት ባለፈው ሳምንት ገጠመን ያሏቸው ችግሮች ላይ መሻሻል መኖሩን ግን አሁንም የቀጠለ ችግር እንዳለ ነግረውናል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያደራጀው ይህ ፀጥታንና አስቻይ ሁኔታን የሚመለከት የተባለው ቡድን ይዞት የሚመጣውን ውጤት የሚጠብቁት በጎ ሥራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
«የፖለቲካ ምኅዳሩንም፣ የፀጥታውንም ሁኔታም የሚያጠና - አቤቱታ በቀረበባቸው አካባቢዎች የሚያጠና ቡድን መቋቋሙን እናውቃለን፣ እኛም ተሳትፈንበታል። አንድ ተስፋ ያደረግነው እንዲያውም እሱን ነው።»
በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላኛው አስተያየት የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ራሔል ባፌ ናቸው።
«ከምርጫ ቦርድ ከተሰጡን ተወካዮች ጋር የእኛም ተወካዮች ሄደዋል። የሌሎች ፓርቲዎች ተወካዮችም አሉ።»
የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የትግራይ ክልልን የምርጫ እምነት አለን» የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። በክልሉ የምርጫ እንቅስቃሴ እንደሌለ ከዚህ በፊት ያነጋገርናቸው ክልላዊ ፓርቲዎች ገልፀዋል።
አወዛጋቢ በሚባሉ ቦታዎችም ይህ ሥራ እየተከናወነ እንዳልሆነ እና ምንም የምርጫ እንቅስቃሴ እንደሌለ መረጃዎች ያመለክታሉ። ምንም እንኳን የፌደሬሽን ምክር ቤት እነዚያ ቦታዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው እንዲደረግባቸው ቢወስንም።
ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ የሚመዘግባቸውን መራጮች ማለትም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች እና በካምፕ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ምዝገባን መጀመሩን አስታውቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ