በቤኒን መፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ
በቤኒን መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ገለፀ።የቤኒን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አላሳኔ ሲዱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በታጠቁ ሃይሎች የተሞከረውን መፈንቅለ መንግስት እንዳከሸፉ ተናግረዋል።ሚንስትሩ ይህን የገለፁት እራሱን የወታደራዊ መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው የወታደራዊ ቡድን በሀገሪቱ የመንግስት ቴሌቪዥን ቀርቦ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎን ከስልጣናቸው መነሳታቸውን፣ ድንበር መዘጋቱን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዱን ካስታወቀ በኋላ ነው።
የመፈንቅለ-ሙከራው መክሸፉን የገለጹት የቤኒን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ወታደሮቹ “መንግሥትን እና ተቋማቱን ለማተራመስ አመጽ መጀመራቸውን የገለፁት ሚንስትሩ የቤኒን ጦር ለሪፐብሊኩ አሁንም ታማኝ መሆኑን ተናግረል። የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው የተደረገው ቤኒን በሚያዝያ ወር ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት ሲሆን ይህም ከ 2016 ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩት የፕሬዚዳንት ታሎን የስልጣን ዘመን የሚያበቃበት ነው።ባለፈው ወር ቤኒን የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ጊዜ ከአምስት ወደ ሰባት አመታት ያራዘመውን አዲስ ህገ መንግስት ያፀደቀች ሲሆን ተቺዎች የገንዘብ ሚኒስትሩን ሮዋልድ ወዳግኒን በእጩነት ያቀረበውን ገዢውን ፓርቲ የስልጣን ሽሚያ ነው ሲሉ ተችተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት እና ኢኮዋስ በቤኒን የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት ማውገዛቸው
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት እና ኢኮዋስ በቤኒን የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት አውግዘዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማሕሙድ አሊ ይሱፍ “በመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው የተሳተፉ ሁሉም ተዋናዮች በአፋጣኝ ሁሉንም ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲያቆሙ እና በአፋጣኝ ወደ ሕጋዊ የጦር ሠፈሮቻቸው እና ሙያዊ ግዴታዎቻቸው እንዲመለሱ” አሳስበዋል።ለፕሬዝደንቱ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጭ ፓትሪስ ታሎን ደሕና መሆናቸውን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ “የቴሌቭዥን ጣቢያ ብቻ በሚቆጣጠሩ ጥቂት ሰዎች” ተጠነሰሰ ያሉትን መፈንቅለ-መንግሥት እንዳወገዙ የዜና አገልግሎቱ ዘግቧል። በምዕራብ አፍሪካ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ጊኒ እና በቅርቡ በጊኒ ቢሳው በወታደራዊ ሀይሎች መፈንቅለ-መንግሥቶች ተካሂደዋል። በጎርጎሪያኑ 1991 ዓ/ም ከፈረንሳይ ቅኝግዛት ነፃ የወጣችው ቤኒን የፖለቲካ መረጋጋት የሰፈነባት ሀገር ነበረች።
የእስራኤል እና ሃማስ ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት
እስራኤል ከሃማስ ጋር ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እደምትሸጋገር ገለፀች።የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሀገራቸው እና ሃማስ “በቅርቡ ወደ ሁለተኛው የተኩስ አቁም ምእራፍ" ሊሸጋገሩ ይችላሉ።ኔትኒያሁ ይህንን የገለፁት እስራኤልን በመጎብኘት ላይ ካሉት የጀርመን መራሄ መንግስት ፍሬዲሪሽ ሜርዝ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
መራሄ መንግስት ሜርዝ እንዳሉት ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት እና ጋዛን ከወታደራዊ ሀይሎች ነፃ ማድረግን የሚያካትተው ሁለተኛው የተኩስ አቁም ምዕራፍ በዚህ ወር መጨረሻ ሊጀመር ይችላል።
እንደ አሶሸትድ ፕሬስ ዘገባ የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳቡ የመጣው በጋዛ ይገኙ የነበሩ የመጨረሻዎቹን እስራኤላውያን ታጋቾችን ሀማስ ከለቀቀ በኃላ ነው።ሃማስ የ24 ዓመቱን የራን ጊቪሊ አስከሬን እስካሁን አሳልፎ አልሰጠም።የራን ጊቪሊ በጥቅምት 7፣ 2023 በሃማስ መሪነት በተካሄደው ጥቃት የተገደለውን የፖሊስ አባል ነው።
ጀርመን በእስራኤል ታሪካዊ ሃላፊነት አለባት መባሉ
ጀርመን በእስራኤል ታሪካዊ ሃላፊነት አለባት ሲሉ መራሄ መንግስት ፍሬድሪሽ ሜርዝ ገለፁ።ሜርዝ ይህንን ያሉት በእስራኤል ይፋዊ የሆሎኮስት መታሰቢያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኙ ነው።
የጀርመኑ የዜና ወኪል ዲፒኤ እንደዘገበው መራሄ መንግስት ፍሬድሪሽ ሜርዝ እየሩሳሌም የሚገኘውን እና በናዚ አምባገነናዊ አገዛዝ ወቅት የተገደሉትን 6 ሚሊዮን አይሁዶች መታሰቢያ በሆነው ያድ ቫሼምን ሲጎበኙ እንደገለፁት ጀርመን በእስራኤል ላይ ዘላቂ ታሪካዊ ሃላፊነት እንዳለባት አስምረውበታል።
«ጀርመኖች በአይሁድ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ወንጀል በማስታወስ እንኖራለን።» ሲሉ በእብራይስጥ ቋንቋ የተፃፈ ማስታወሻ በዝክረ መዝገቡ ውስጥ ማስቀመጣቸውን ዘገባው አመልክቷል።
እንደዘገበው ሜርዝ የመጀመርያ ጉዟቸውን ቅዳሜ ወደ ዮርዳኖስ ያደረጉ ሲሆን ኦማን በጋዛ የምታደርገውን የሽምግልና ጥረት አድንቀዋል።
በጋዛ ያለው ጦርነት “በተጠናከረበት ወቅት ወደ ስልጣን የመጡት ሜርዝ፤በርሊን በእስራኤል ላይ ከፊል የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ፤ ባለፉት ጥቂት ወራት የጀርመን እና እስራኤል ግንኙነት በመጠኑ ሻክሮ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩ መፈታቱን ዘገባው አመልክቷል።
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት ባለፈው ግንቦት ወር በእስራኤል ጉብኝት አድርገዋል።
ሩሲያ በዩክሬን የአየር ጥቃት መፈፀሟ
ሩሲያ ፤በዩክሬን ክሬሜንቹክ ከተማ የአየር ጥቃት መፈፀሟ ተገለፀ።ጥቃቱ የተፈፀመው በሁለቱ ሀገሮች ሰላም ለማውረድ በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው የሰላም ጥረት በቀጠለበት ወቅት ነው።የሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ማዕከላዊውን የኢንዱስትሪ ከተማ በአንድ ጀምበር መምታቱን ከንቲባው ተናግረዋል።
የዩክሬን አየር ሃይል እና የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ማሌስኪ እንደገለፁት በማዕከላዊ የዩክሬን ክሬመንቹክ ከተማ የሩስያ ሰው አልቫ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ዛሬ ዕሁድ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈፅመዋል።ትናንት ለዛሬ አጥቢያ ሌሊት በደረሰው ጥቃት በከተማዋ የኤሌክትሪክ እና የውሃ መቆራረጥ እያስከተለ መሆኑን ገልፀዋል።ከዋና ከተማዋ ኪየቭ በ259 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ይህቺ ከተማ ዋና የኢንዱስትሪ ማዕከል እና የዩክሬን ትልቁ የነዳጅ ዘይት ፋብሪካዎች ቦታ መሆኗንም ሮይተርስ የዜና ምንጭ አመልክቷል።ጥቃቱ የደረሰው በሁለቱ ሀገሮች ሰላም ለማውረድ ዩናይትድ ስቴትስ መፍትሄ ለመፈለግ ጥረቷን በቀጠለችበት እና የጀርመን፣ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ መሪዎች ነገ ሰኞ ለንደን ውስጥ በመገናኘት በድርድሩ ሂደት ላይ ለመምከር ባቀዱበት ወቅት ነው።
ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ