1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የብልፅግና ጉባዔ ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ይዞ ይሆን?  

እሑድ፣ መጋቢት 18 2014

„ብልፅግና ከተመሰረተ ሦስት ዓመት ገደማ ቢሆነዉም አባላቱ የመጀመርያ ጉባዔያቸዉን ስላካሄዱ ጥሩ ስሜት አለን። ግን ነገሮች ሊፈፀሙ እንደሆነ ማሳያ ነገሮች መኖር ነበረባቸዉ፤ እነሱን አላየንም። ብልፅግና ጉባዔዉን ከማካሄዱ በፊት «መመረጥ ሀገርን ለመለወጥ» በሚል መርህ ቃል አመራሩ እና መላ አባላቱ ዉይይት አካሂደዋል።“

https://p.dw.com/p/495l5
Logo Äthiopien Erster Kongress der Wohlstandspartei PP
ምስል Prosperity Party Ethiopia

«የአመራር ሰጭነት ግዴታን ለመወጣት ጉባዔዉ ዉሳኔዎችን አስተላልፎአል። ግን ዉሳኔዎቹ የሃገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይቀርፉ ይሆን?»

ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ጉባኤዉን ያካሄደዉ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ብልጽግና  በሃገሪቱ ትኩረት የሚያሻቸዉ ጉዳዩች ላይ ተነጋገሮ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጿል። «ከፈተና ወደ ልዕልና» በሚል  መርህ የተካሄደው  የፓርቲው  ጉባዔ፤ ምርጫ ቦርድ ጉባኤ ያላካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ወር ጌዜ ዉስጥ እንዲያካሂዱ ሲል ቀነ ገደብ ካስቀመጠ በኃላ የተካሄደ ነዉ።  ገዥዉ ብልፅግና ፓርቲ በጉባዔዉ ማጠናቀቂያ ለሃገሪቱ የከፍታ ጉዞ የተመቻቹ ዉሳኔዎችን ማሳለፉን ሲገልፅ ተደምጧል። ፓርቲው ህብረ ብሄራዊ እና የኢትዮጵያን አንድነት መሰረት አድርጎ በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበ እንዲሁም  ሰላምን ለማረጋገጥ ቅድሚያ የሰጠ መሆኑንም በተደጋጋሚ ገልጿል። ፓርቲው ይህን ይበል እንጅ  በጉባዔዉ መጠናቀቅያ የተጠበቀዉን ያህል ችግር ፈች አቅጣጫ ይዞ መዉጣቱን ብዙ ብልጽግና ዎች ይጠራጠራሉ። ፓርቲዉ ጥቂት  ሹማንቶቹን ከመቀየር ባለፈ  በኢትዮጵያ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚፈታና ሀገሪቱ ለገጠማት ፈተና  የሚመጠን መፍትሄ ይዞ  አልወጣም ሲሉም ብዙዎች ይተቹታል።  የገዥዉ ፓርቲ ብልፅግና ጉባዔ እንዴት ይገመገማል? ብልፅግና የኢትዮጲያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይቀርፍ ይሆን?  በዚህ ርዕስ ላይ ሃሳባቸዉን ሊያካፍሉን፤   

አቶ ግዛቸው ገቢሳ- የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህዝብ ግኑኝነት ዘርፍ ሃላፊ)

ትግስት ወርቅነህ -የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ( ኢዜማ)  የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ አቶ ሙላቱ ገመቹ - የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም  አዲሱ ጌታነህ -ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ናቸዉ ። 

ተወያዮች ከሰጥዋቸዉ አስተያየቶች መካከል በጥቂቱ፤

እርሶም አስተያየቶን ፃፉልን!  

„ብልፅግና ከተመሰረተ ሦስት ዓመት ገደማ ቢሆነዉም አባላቱ የመጀመርያ ጉባዔያቸዉን ስላካሄዱ ጥሩ ስሜት አለን። ብልፅግና በጉባዔዉ ማጠናቀቅያ እፈፅማቸዋለሁ ያላቸዉ ነገሮች አሉ፤ በዚህ አጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲፈፅም አንጠብቅበትም።  ግን ነገሮች ሊፈፀሙ እንደሆነ ማሳያ ነገሮች መኖር ነበረባቸዉ፤ እነሱን አላየንም።  ይሉቅንም ሀገራችን ከቀን ወደቀን ወደ ከፋ እና ወደ ተወሳሰበ ሁኔታ እየሄደች ነዉ። በሀገሪቱ ግድያ፤ መፈናቀል፤ የኑሮ ዉድነት ብሎም ስርዓት አልበኝነት እየተስፋፋ ነዉ። ብልጽግና ይህን ለመቅረፍ ይዞት የመጣዉ ነገር ስለመኖሩ ጥርጣሬ አለን። የጉባዔዉ አካሄድ ዴሞክራስያዊ ስርዓትን እንገነባለን ከሚል ድርጅት የማይጠበቅ ሁኔታዎች ታይተዋል፤ ጉባዔዉ ከተጠበቀዉ በላይ የወረደ ነበር። ከብልፅግና ያገኘነዉ ነገር የለም፤ ታሪክ ራሱን ይደግማል በ10ኛዉ አብዮት አካባበር እንዲሁም በንጉሱ ዘመን ሀገሪቱ ላይ ረሀብና ችግር ተከስቶ፤ አዲስ አበባ ላይ የታየዉ አይነት ድግስ ታይቶ ነበር። ብልፅግና ቢሳካለት እንደ ሀገር ይሳካልናል። ሙግታችንም ሀገሪቱ ወደተሻለ መንገድ እንድትሄድ ነዉ።“

„ብልፅግና ጉባዔዉን ከማካሄዱ በፊት «መመረጥ ሀገርን ለመለወጥ» በሚል መርህ ቃል አመራሩ እና መላ አባላቱ ዉይይት አካሂደዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ መፍትሄ ለሚመጣ የሚችለዉ፤ በአንድ ፓርቲ ብቻ ነዉ ብለን አናምናለን ። የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚሉ የፖለቲካ ሃይላት ሁሉ በሀገሪቱ ርምጃ ላይ ድርሻ አላቸዉ። ብልፅግና ፤ ሀገራዊ አንድነትን ፤ በኢኮኖሚ መልሶ መቋቋምን ፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነትን ማስቀጠል የሚለዉንም አይቶአል። ብልፅና ጉባዔዉን መገምገም ያለበት ራሱ ፓርቲዉ ብቻ ነዉ። ፓርቲዉ 11 ሚሊዮን አባላት አሉት። በጉባዔዉ የታየዉ ግብዣ በአባላት መዋጮ የተካሄደ ነዉ። በምርጫ ቦርድ ተመዝግበዉ ሰላማዊ የትግል ሂደቱን የተቀላቀሉ አካላት በህግ የመገዛት አዝማምያ መንፈስ ሊያሳዩ ይገባል። ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ሃይሎች ቀስቃሽ ንግግሮችን፤ ዜጎችን ወደ አልተፈለጉ መንገድ የሚወስዱ ነገሮች ከማንፀባረቅ ሊጠነቀቁ እና ሊቆጠቡ ይገባል። ይህ የኛን ፓርቲ ብልፅግናንም ይመለከታል። የህዝብ ይሁንታን ያገኘዉ ፓርቲ የመንግሥት ገዥ ፓርቲ አመራር ሰጭነትን ድርሻ ለመወጣት ጉባዔዉ ላይ ዉሳኔዎችን አስተላልፎአል። በዉሳኔዎች መሰርት ሊከናወኑ የሚገቡ ዉሳኔዎች ይከናወናሉ። “

ተወያዮች በዉይይቱ ለመሳተፍ ስለቀረቡ በዶቼ ቬለ ስም እናመሰግናለን።

እርሶም የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ዉይይቱን አድምጠዉ አስተያየቶን ይፃፉልን!

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ