1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
የፕሬስ ነጻነትኢትዮጵያ

ጋዜጠኛ ዮሐንስ ብርሃነ በአስቸኳይ እንዲፈታ ተጠየቀ

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 15 2018

የትግራይ ቴሌቪዥን የዜና ክፍል ባልደረባ ጋዜጠኛ ዮሐንስ ብርሃነ ኢ- ሕገመንግሥታዊ "አፈና እና እሥር" እንደተፈፀመበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ገለፀ። "ሕገ-ወጥ"ያለውን ይህንን ድርጊት በጥብቅ ያወገዘው ማሕበሩ ጋዜጠኛው በመቀሌ ከተማ "ሲቪል በለበሱ ሰዎች እና ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ ታፍኖ መወሰዱን" ማረጋገጡን ጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/5B0Y4
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር አርማ
ጋዜጠኛ ዮሐንስ ብርሃነ ኢ- ሕገመንግሥታዊ "አፈና እና እሥር" እንደተፈፀመበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ገለፀ።ምስል፦ EMMPA

ጋዜጠኛ ዮሐንስ ብርሃነ በአስቸኳይ እንዲፈታ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ትናንት ባወጣው መግለጫ የትግራይ ቴሌቪዥን ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ዮሐንስ ብርሃነ መጋቢት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. መቀሌ ከተማ ውስጥ መርከብ ከተባለ ምግብ ቤት "ሲቪል በለበሱ ሰዎች እና ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ ታፍኖ መወሰዱን" አረጋግጫለሁ ብሏል።  

ባለሙያው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት በማያውቀው "የግል ማጎሪያ" ባለው ሥፍራ ለ6 ቀናት መቆየቱ እንዳሳሰበውም ማሕበሩ ጠቅሷል። የማሕበሩ ፀሐፊ ዳዊት አስታጥቄ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን አብራርቷል።

የጋዜጠኞች የሙያ ማሕበሩ በዚሁ መግለጫው ጋዜጠኛ ዮሐንስ ብርሃነ በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ጠይቋል።


ችግሩን የሲቪክ ድርጅቶችም ተጋርተውታል


ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተባለው የሲቪክ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል "አፈና እና የዘፈቀደ እሥራት" መደጋገሙን ጠቅሶ ሰዎች ተይዘው የት እንደገቡ የማይታወቅበት ኹኔታ መኖሩን፣ "ገሚሶቻቸው ደግሞ ማን እንደያዛቸውም አይታወቅም" በማለት ከምንም በላይ "ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማፈን" አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ችግር ነው ሲል አሳስቧል። ስሙን መግለጽ ያልፈለገ አንድ ጋዜጠኛም በዚህ ይስማማል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር "የክልሉ መንግሥት በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን ወከባና ሕገ-ወጥ እሥር በአስቸኳይ እንዲያቆም" ሲል ጥሪውን አቅርቧል። በ ትግራይ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው ጋዜጠኞችን የማዋከብ አዝማሚያ መጨመሩን ተጨባጭ መረጃ እንዳለው ይሄው ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ጋዜጠኛ ነግሮናል።


ብሔራዊ ጥቅም እና ጋዜጠኞች እየታዩበት ያለው አዝማሚያ


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በትግራይ ክልል  በጋዜጠኞች ላይ የበረታ ጫና መኖሩን፣ ይህም ምክንያት ሆኖ ሥራ ከመልቀቅ እስከ ወደ አዲስ አበባ መሸሽ መስተዋሉን ያነጋገርናቸው ጉዳዩን የሚከታተሉ ሰዎች ገልፀዋል። በጉዳዩ ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግኹት ጥረት ምላሽ አላገኘም።

ትግራይ ክልል የሚገኙ ጋዜጠኞች ከውጭ ለመጡ የመንግሥት ልዑኮች ጥያቄ ሲያቀርቡ
የካቲት 2017 ዓ ም ትግራይ ክልል የሚገኙ ጋዜጠኞች ከውጭ ለመጡ የመንግሥት ልዑኮች ጥያቄ ሲያቀርቡ ምስል፦ Tigrai Mass Media Agency

ሰሞኑን በ ኢትዮጵያ  መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጋዜጠኞች የልሕቀት ማዕከል የሰለጠኑ ባለሙያዎች መመረቃቸውን ተከትሎ ማብራሪያ የሰጡት የባለሥልጣኑ የቦርድ ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ ጋዜጠኛ "የማንም ተለጣፊ ሳይሆን የብሔራዊ ጥቅም አገልጋይ ነው መሆን ያለበት" ብለዋል። ዘርፉ በዚህ ሂደት "እንቅፋት" እንደሚገጥመው አልሸሸጉም።

ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ "ብሔራዊ ጥቅምን የሚነካ ዘገባ ነው" በሚል ልዩ ልዩ  መገናኛ ዐውታሮች ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው፣ ፈቃዳቸውም ሲነጠቅም በግልጽ  እየተስተዋለ መጥቷል።

 ሰለሞን ሙጬ

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ