በትግራይ ያለፍርድ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች
ቅዳሜ፣ መጋቢት 23 2015
በትግራይ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች፣ በርካቶች እስካሁን ያለፍርድ ታስረው እንደሚገኙ፣ ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቆች ገለፁ። 'ከጠላት ጋር መተባበር' በሚል ክስ፣ ታስረው ከሚገኙ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል ጋዜጠኛ፣ የሕግ ባለሙያ፣ የመንግስት ሰራተኞ የነበሩ ይገኙበታል። በየፊናቸው 'ጠላት' ተባብለው የነበሩት ህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ከደም አፋሳሹ ጦርነት በኃላ የሰላም ስምምነት ላይ የደረሱ ቢሆንም፣ በትግራይ በዚሁ ሰበብ የታሰሩት ግን እስከአሁን አለመለቀቃቸው እንዳሳሰባቸው ቤተሰቦቻቸው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይ ተቆጣጥሮ ግዚያዊ አስተዳደር አቋቁሞ በነበረበት 2013 ዓ.ም፣ ከግዚያዊ አስተዳደሩ ጋር ተባብረዋል፣ ሰርተዋል፣ ሹመት ተቀብለዋል ተብለው፥ 'ከጠላት ጋር መተባበር' የሚል ክስ ቀርቦላቸው እስር ላይ የሚገኙ የታሳሪ ቤተሰቦች እና ጠበቆች የጉዳዩ ተከሳሾቹ ለረዥም ግዜ ያለፍርድ እስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
'ከጠላት ጋር መተባበር' በሚል ክስ ታስረው ካሉት መካከል የቀድሞ የትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ዳዊት መኮነን ይገኝበታል። የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ሃይሉ ወዳጄ እንደሚሉት፣ ደንበኛቸው ያለክስ ለረዥም ግዜ እስር ላይ ከቆየ በኃላ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይ ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት አብሮ በመስራት፣ 'ከጠላት ጋር መተባበር' የሚል ክስ ቀርቦለት ላለፉት 10 ወራት ያለፍርድ ታስሮ እንደሚገኝ ተናግረዋል። "ዳዊት ታስሮ ያለው በጋዜጠኝነት ስራው ነው" የሚሉት የጋዜጠኛ ዳዊት ጠበቃ፣ መዝገቡ በመጓተቱም ደንበኛቸው እና ቤተሰቡ ላይ ለከፍተኛ ችግር መፈጠሩ አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በ2013 ዓ.ም በነበረው ሁኔታ ከጠላት ጋር መተባበር የሚል ክስ ቀርቦባቸው ከታሰሩት መካከል መንግስት ሰራተኛው አቶ ብርሃነ ገብረመድህን ይገኙበታል። የታሳሪው የቅርብ ቤተሰቦች ለዶቼቬለ እንዳሉት በትግራይ ክልል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ይሰሩ የነበሩት አቶ ብርሃነ ያለፍርድ ከታሰሩ 1 ዓመት ከ2 ወር አልፏቸዋል። ለድህንነታቸው በመስጋት ስማቸው ሊገለፅ ያልፈለጉ የአቶ ብርሃነ የቅርብ ቤተሰብ እንዳሉን እስካሁን ተከሳሹ አቶ ብርሃነ 39 ግዜ ፍርድቤት ቢመላለሱም "በተለያዩ ሰበቦች" ውሳኔ ማግኘት አልቻሉም።
ከነዚህ ውጭ በትግራይ 'ከጠላት ጋር መተባበር' የሚል ክስ ቀርቦላቸው የታሰሩ የመንግስት ሰራተኞች፣ ሹመኞች እና ሌሎች ስለመኖራቸው ከተለያዩ ምንጮች ሰምተናል። 'ጠላት' የተባባሉት ህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ከደም አፋሳሹ ጦርነት በኃላ የሰላም ስምምነት ላይ የደረሱ ቢሆንም፣ በዚሁ ሰበብ የታሰሩት ግን አሁንም አለመለቀቃቸው እንዳሳሰባቸው በመቐለ ቤተሰቦቻቸው ታስረውባቸው ያሉ ዜጎች ተናግረዋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙርያ፣ ቀጥታ ከሚመለከተው የመቐለ ከተማ ፍትህ ፅሕፈት ቤት መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ